በመብራት ሀይል መቆራረጥ ምክንያት ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ተዳርገናል ሲሉ የቡሌ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ

በመብራት ሀይል መቆራረጥ ምክንያት ለኢኮኖሚያዊና ማህበራዊ ችግር ተዳርገናል ሲሉ የቡሌ ወረዳ ነዋሪዎች ተናገሩ

በጌዴኦ ዞን ቡሌ ከተማ በሆቴልና ባልትና ንግድ የተሰማሩት ወ/ሮ አለም ደምሴና ከፋለች ደያሶ እህል ለማስፈጨት ከወፍጮ ቤት መጥተው ሲያስመዝኑ ነበር ያገኘናቸው፡፡ ያስዘመኑት እህል በመብራት መቆራረጥ ምክንያት ከወፍጮ ቋት ሳይወጣ ለቀናት እንደሚያድር ተናግረዋል።

ኑሯቸውን የሚደግሙት በዚሁ ስራ በመሆኑ ችግሩ እንዲፈታ ጠይቀዋል።

ሌላኛው አስተያየት ሰጪ የቡሌ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ከደቡብ፣ ኦሮሚያና ሲዳማ አዋሳኝ ክልሎች የሚመጡ ከፍተኛ ቁጥር ያላቸው ህሙማን እያገለገለ እንደሚገኝ የተናገሩት የሆስፒታሉ ሜዲካል ዳይሬክተር አቶ ታደለ ማሪያም፤ በኦክስጅን የሚሰጥ የህክምና እርዳታ ከመብራት ጋር የተቆራኘ በመሆኑ በሀይል መቆራረጥ ምክንያት የሰው ህይወት እያለፈ እንዳለ ተናግረዋል።

በወረዳው የሚገኙ ሴክተር መስሪያ ቤቶችን በጀት እያንቀሳቀሰ የሚገኘው የወረዳው ፋይናንስ ጽ/ቤት ከ3 ወር በላይ ሪፖርት ባለማድረጋቸው የሰራተኛ ደመወዝ ላይ ችግር እየተፈጠረ እንዳለ የተናገሩት የቡሌ ወረዳ ፋይናንስ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ጥላሁን ገደቾ፤ በኮምፒውተር ሪፖርት የሚደረግበት የቴሌ ሲስተም በመብራት ኃይል መቆራረጥ ምክንያት ሲስተሙም እየተቆራረጠ መቸገራቸውን ገልጸዋል።

ህብረተሰቡም ሆነ ተቋማቱ የሚያነሱት ጥያቄ የኔም ጥያቄ ነው ያሉት የቡሌ ወረዳ አስተዳዳሪ አቶ በራቆ በራሶ የመብራት መቆራረጡ ከፍተኛ ቅሬታ የፈጠረ የመልካም አስተዳደር ችግር መሆኑን ጠቁመዋል።

ችግሩ እንዲፈታ ከማዕከሉ ጋር በተደጋጋሚ በመነጋገር እንዲሁም ለዋናው የወላይታ ዲስትሪክት በደብዳቤ ቢጠይቁም ምላሽ ማግኘት እንዳልተቻለ የገለጹት አስተዳዳሪው ችግሩ ምላሽ እንዲሰጠው ጠይቀዋል።

እኛም በኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ አገልግሎት የቡሌ ማዕከል ደንበኞች አገልግሎት ኃላፊ ለአቶ ጌታሁን አሸንጎ ላነሳነው ጥያቄ በአንድ ማከፋፈያ ስር አምስት ማዕከላት (ወረዳዎች) አንድ ላይ በመሆናቸው በአንዱ ችግር ሌላኛው ተጎጂ የሚሆንበት፣ የማዕከላት የእርስ በርስ ግንኙነት በራሱ ችግር ያለበት በመሆኑ ለመብራት መቆራረጥ ዋነኛ ተግዳሮት መሆኑን ተናግረዋል።

የሌሎች ማዕከላትን ወይም መስመሮችን በመለየትና የት ጋ ችግር እንዳለ የሚጠቁም መሳሪያ በማስቀመጥ የወላይታ ዲስትሪክት እገዛ ቢያደርግ ችግሩ እንደሚፈታ ኃላፊው ገልጸዋል።

ዘጋቢ: ውብሸት ከሣሁን – ከፍስሐገነት ጣቢያችን