የጓሮ አትክልትና የተለያዩ ሰብሎችን በማልማት የምግብ ዋስትናን ማረጋገጥ መቻላቸውን በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሶያሜ ቀበሌ አርሶአደሮች ተናገሩ

ሀዋሳ፡ ታኅሣሥ 08/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) የጓሮ አትክልትና የተለያዩ ሰብሎችን በመስኖ ማልማት ከጀመሩ ወዲህ ከነበረባቸው የኢኮኖሚ ጥገኝነት በመላቀቅ የምግብ ዋስትና ማረጋገጥ መቻላቸውን በጠምባሮ ልዩ ወረዳ የሶያሜ ቀበሌ አርሶአደሮች ገለጹ።

በልዩ ወረዳው በበጋ መስኖ ከ3ሺ 420 ሄክታር በላይ ማሳ በተለያዩ ሰብሎችና የጓሮ አትክልት ለማልማት ወደ ተግባር መገባቱን የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታውቋል።

በአሁኑ ወቅት በሶያሜ ቀበሌ በበጋ መስኖ የተለያዩ የውኃ አማራጮችን በመጠቀም 362 ሄክታር ማሳ በጓሮ አትክልትና በተለያዩ ሰብሎች ለመሸፈን እየተሰራ ሲሆን፥ ቀደም ሲል በዝናብ ጥገኛ የነበረውን የአካባቢውን አርሶአደር የስራ ባህል ከመቀየር ባሻገር ከምግብ ዋስትና ችግሮች ለመላቀቅ አመራጭ የሌለው መፍትሔ ሆኗል።

የአካባቢው አርሶ-አደር በሳታሜ እና ሻጳሞ ወንዝ ላይ የተዘረጋውን ዘመናዊ የመስኖ ካናል በመጠቀምና የጮሬ ምንጭ በመጥለፍ በተሰማሩት የበጋ መስኖ ልማት ተጠቃሚ መሆናቸውን ካነጋገርናቸው የሶያሜ ቀበሌ ለሜጃ ጎጥ ነዋሪዎች መካከል አርሶአደር ደሳለች ቸርነት፣ አድማሱ ሞሎሮ እና ዘለቀ አበበ ተናግረዋል።

ከአራት ዓመት በፊት በኢኮኖሚ ጥገኛ መሆናቸውንና ሁሉም የለሜጃ ጎጥ አርሶአደር እርዳታ ጠባቂ ከሆነበት በመስኖ ልማት ከተሰማራ ወዲህ፥ በዓመት ሁለት ጊዜና ከዚያ በላይ በማምረት ከምግብ ፍጆታ ባሻገር ለገበያ በማቅረብ የኢኮኖሚ አቅማቸውን እያሳደጉ እንደሚገኙ አርሶአደሮቹ ጠቁመዋል።

ባለፈው ዓመት በበጋ መስኖ ካለሙት የጓሮ አትክልት ከ80ሺ ብር በላይ ገቢ ማግኘታቸውን የተናገሩት አርሶአደር ደሳለች ቸርነት እና አድማሱ ሞሎሮ፥ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ደግሞ ድንች፣ ስኳር ድንችና ስንዴን በማልማት ከ160ሺ ብር በላይ ገቢ ለማግኘት ያቀዱትን ውጥን ለማሳካት ባለሙያውና አመራሩ ድጋፉን አጠናክሮ መቀጠሉን ተናግረዋል።

በሶያሜ ቀበሌ አርሶአደሩን የመስኖ ልማት ተጠቃሚ ለማድረግ በሶስት ጎጥ 362 ሄክታር በጓሮ አትክልትና በተለያዩ ሰብሎች በበጋ መስኖ ከማልማት በተጨማሪ 1020 ኤክስቴንሽን ተጠቃሚ ማፍራት መቻሉን የቀበሌው ግብርና ልማት ጽ/ቤት ኃላፉ አቶ ታደለ ላንገና ተናግረዋል።

የቀበሌው አርሶአደር በተሰማራበት የመስኖ ልማት ይበልጥ ተጠቃሚ እንዲሆን የግብርና ባለሙያው የሚያደርገውን የሙያና ክሂሎት ስልጠናና ድጋፍ እንደማይለየው የጠቆሙት አቶ ታደለ በሂደቱም ከምግብ ፍጆታ አልፈው ለገበያ በማምረት ከነበረባቸው የኢኮኖሚ ጥገኝነት የተላቀቁ አያሌ አርሶአደሮችን ማፍራት መቻሉንም አመላክተዋል።

የመኸር እርሻ መጠናቀቁን ተከትሎ አርሶአደሩ ወደ በጋ መስኖ ልማት እንዲገባ በተደረገው የንቅናቄ ስራ በአሁኑ ወቅት 3ሺ 4 መቶ 22 ሄክታር ማሳ በበጋ መስኖ በጓሮ አትክልት፣ በስራስርና በጥራጥሬ ሰብሎች ለመሸፈን ታቅዶ እየተሰራ መሆኑን የጠምባሮ ልዩ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት ምክትል ኃላፊና የእርሻ ዘርፍ ኃላፊ አቶ መብራቱ አበራ ገልፀዋል።

በልዩ ወረዳው አራት ቀበሌያት ዘመናዊ የመስኖ ካናሎች ተገንብተው የአርሶአደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በሚደረገው ጥረት ከፍተኛ አስተዋጽኦ በማበርከት ላይ መሆናቸውን የተናገሩት አቶ መብራቱ፤ በበጋ መስኖ እየለማ ከሚገኘው እርሻ 7መቶ 87ሺ ኩንታል ለማምረት እየተሰራ እንደሚገኝም ኃላፊው ጠቁመዋል።

ዘጋቢ: ጡሚሶ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን