በጎፋ ዞን ያለውን ዕምቅ የማዕድን ሀብት በማልማት ከዘርፉ ተጠቃሚ ለመሆን በትኩረት መስራት እንደሚገባ የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ ገለጹ

የዞኑ ውሃ መስኖና ማዕድን ልማት መምሪያ የ2015 በጀት ዓመት አፈጻጸም ግምገማና የ2016 በጀት ዓመት ዕቅድ ላይ የምክክር መድረክ አካሂዷል።

በመድረኩ ላይ የተገኙት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ደዊት ፋንታዬ በንጹህ መጠጥ ውሃ አቅርቦት ዘርፍ የሚስተዋለውን የጥራትና የተደራሽነት ችግር ለመፍታት ከህብረተሰቡና ከአጋር ድርጅቶች ጋር በመተባበር በትኩረት መስራት እንደሚገባ ገልጸዋል።

አክለውም ማዕድን እንደ ዞን ብዙ ያልተሰራበት ነገር ግን ብዙ አቅም ያለው ዘርፍ ሲሆን በዘርፋ ያለውን ተጠቃሚነት ለማሳደግ የማዕድን ቦታዎችን መለየት፣ ሳይንሳዊ ጥናት ማካሄድ፣ የአመራረት ሂደትን ማሻሻል እና ገበያ መፍጠር ላይ ትኩረት እንደሚሰጥ አስታውቀዋል።

የዞኑ መንግስት ዋና ተጠሪ አቶ መስፍን ስለሺ በበኩላቸው ገበያን ለማረጋጋትና የኑሮ ውድነትን ለመቅረፍ ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ወሳኝ በመሆኑ የመስኖ አማራጮችን በአግባቡ መጠቀም ይገባል ብለዋል።

የመስኖው ዘርፍ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ ተስፋ የተጣለበት ዘርፍ መሆኑንም አንስተዋል።

የዞኑ ውሃ መስኖና ማዕድን መምሪያ ኃላፊ አቶ ቴዎድሮስ ተሾመ በዞኑ ከ1 ሺህ በላይ የውሃ ተቋማት ቢኖሩም የንጹህ መጠጥ ውሃ ሽፋን በገጠር 37 ነጥብ 2 በመቶ ሲሆን በከተማ ደግሞ 39 ነጥብ 5 በመቶ ብቻ መሆኑን ገልጸዋል።

በዞኑ ካለው ጠቅላላ ሕዝብ መካከል 62 ነጥብ 2 ሕዝብ ጥራቱን ያልጠበቀ ወንዝ፣ ኩሬና ምንጭ ውሃ በመጠጣት ላይ ስለመገኘታቸው ነው የገለጹት።

በዞኑ 18 ሺህ ሄክታር በላይ የማምረት አቅም ያላቸው የመስኖ አውታሮች ጥናታቸው አልቆ ወደ ስራ ለመግባት የተዘጋጁ ቢሆንም በአሁኑ ሰዓት አልቆ አገልግሎት እየሰጠ ያለው የመስኖ አቅም 3 ሺህ 601 ሄክታር ሲሆን እየለማ ያለው ደግሞ 1 ሺህ 624 ሄክታር ብቻ መሆኑን አስረድተዋል።

ስለዚህ ያለንን አቅም በአግባቡ በመለየት በ2016 ዓ.ም በመደበኛ መስኖ እና በጋ ስንዴ በተገቢው ማልማት እንደሚገባ አመላክተዋል።

በማዕድኑ ዘርፍ ዞኑ እምቅ አቅም ያለው ሲሆን የግንባታና የኢንዱስትሪ ማዕድናት፣ የድንጋይ ከሰል፣ ብረትና የጌጣገጥ ማዕድናት በስፋት እንደሚገኝ በጥናት ተረጋግጧል ብለዋል።

ሆኖም እነዚህ ማዕድናት በኋላቀር የአመራረት ዘይቤ እየተመረቱ በመሆናቸው ዞኑ ማግኘት ያለበትን ገቢ በአግባቡ እያገኘ ባለመሆኑ ባለድርሻ አካላት በቀጣይ በዘርፉ ትኩረት ሰጥተው መሰራት እንዳለበት አሳስበዋል።

በመድረኩ የመምሪያው የ2015 በጀት ዓመት አፈፃፀም እና የ2016 ዓ.ም በጀት ዓመት ዕቅድ በምክትል መምሪያ ኃላፊው አቶ መንግሥቱ ሙንኣ ቀርቦ ውይይት ተካሂዷል።

የውይይቱ ተሳታፊዎች በሰጡት አስተያየት የንጹህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን የመስኖ አማራጮችና የማዕድን ሀብት በማልማትና በማስተዳደር ረገድ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመፍታት ቁርጠኛ መሆናቸውን አረጋግጠዋል።

ዘጋቢ፡ አይናለም ሰለሞን – ከሳውላ ጣቢያችን