በከተማው ባለቤት ያላቸዉን ዉሾች በመለየት ለተከታታይ ሁለት ቀናት ክትባት መሰጠቱም ተገልጿል።
የእብድ ዉሻ በሽታ በበሽታዉ በተጠቁ እንስሳት ንክሻ አማካኝነት የሚተላለፍ ስለመሆኑ የእንስሳት ጤና ባለሙያዎች ይናገራሉ።
በሽታው ዘጠና ዘጠኝ በመቶ በዉሻ ንክሻ የሚተላለፍ ሲሆን ቅድመ ጥንቃቄ ካልተደረገና ለተነከሱት ሰዎች ክትባት በጊዜ ካልተሰጠ ገዳይ በመሆኑ በየወቅቱ ለውሾች ክትባት በመስጠት ተገቢዉን አገልግሎት ለማግኘት እየተሰራ መሆኑን የማሻ ከተማ አስተዳደር ግብርና፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽህፈት ቤት ሀላፊ ወይዘሮ ወጌ እሸቱ ተናግረዋል።
ከአምስት ወር በፊት በከተማው ዉስጥ አንድ ያበደ ዉሻ አስራ ስምንት ሰዎችን በመንከሱ ምክንያት በአካባቢው ባለዉ የጤና ተቋማት መከላከያ ክትባት ባለመገኘቱ ህብረተሰቡ በመቱ፣ በቦንጋና፣ በሚዛን አማን ሪፈራል ሆስፒታሎች በመሄድ ለኢኮኖሚያዊና ለማህበራዊ ቀዉስ መዳረጋቸውን አውስተዋል።
በዚህ መነሻ ዉሾችን ከመግደል ይልቅ ከ3 መቶ በላይ ባለቤት ያላቸው ዉሾችን በመለየት ክትባት እየተሰጠ መሆኑን የተናገሩት ሀላፊዋ ባለቤት የሌላቸውንና ተልከስካሽ ዉሾችን በተመለከተም የእንስሳት ጤና ጥበቃ አዋጅ መሰረት ትኩረት ተሰጥቶ እንደሚሰራም አብራርተዋል።
የማሻ ወረዳ ግብርና፣ ደን፣ አካባቢ ጥበቃና ህብረት ስራ ጽህፈት ቤት የእንስሳት ጤና ቡድን መሪ የሆኑት አቶ መልካሙ መለሰ በበኩላቸዉ በእብድ ዉሻ ንክሻ ምክንያት ብዙ ሰዎች ህክምና ለማግኘት በተለያዩ ቦታዎች በመዘዋወር ለተለያዩ ወጪዎች ሲዳረጉ መቆየታቸዉን ተናግረዉ አሁን ላይ ክትባት በመስጠት ቅድመ መከላከል ስራ ላይ መሆናቸዉን ገልጸዋል።
እንደ ሀገር የዉሻ በሽታን በ2030 ላይ ለማጥፋት እቅድ ተይዞ እየተሰራ እንደሚገኝም አክለዋል ባለሙያዉ።
ለዉሾች ክትባት መስጠት በአካባቢው አዲስ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ የሚስተዋሉ ዉስንነቶችን ለመቅረፍ ግንዛቤን ከመፍጠር አንጻር በርካታ ስራዎች ከተቋሙ እንደሚጠበቅ ገልጸዉ ህብረተሰቡም ጥንቃቄ እንዲያደርግና ችግሩ ከተከሰተ በፍጥነት ወደ ጤና ተቋማት በመሄድ የህክምና አገልግሎት ማግኘት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
ዘጋቢ፡ ልጃለም ማሞ – ከማሻ ጣቢያችን
More Stories
የቀቤና ልማት ማህበር (ቀልማ) የማህበረሰቡን ሁለትናዊ ተጠቃሚነት ለማሳደግ የያዛቸው ዋና ዋና ግቦች ለማሳካት በሚደረገው ጥረት የበኩላቸውን ድርሻ ለመወጣት መዘጋጀታቸውን አባላቱ ገለጹ
የፀረ ተህዋሲያን መድሃኒቶች መላመድ ለሰው ልጆች ስጋት እየሆነ መምጣቱ ተገለጸ
በሀዲያ ዞን ከ8መቶ 50ሺህ በላይ የተለያዩ የህብረሰብ ክፍሎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ተግባራት መከናወናቸው ተገለፀ