የሶማሊ ላንድ “የተናጠል” ህይወት

በፈረኦን ደበበ

ልዩነት፣ ነጻነት ወይም ሉዓላዊነት የሚሉ ቃላት እዚህም እዚያ መሰማታቸው የተለመደ ሆኗል፤ ከአብረን እንኑር ጥሪዎች ጎን ለጎን፡፡ በተለይ ድህነትና ኋላቀርነቱ ገዝፎ ወንድማማቾችን እርስ በርስ በሚያጋጭበት አካባቢ ስለ ሠላምና አብሮ መኖር ማሰቡ ትልቅ ጠቀሜታ አለው፡፡

አዎን በቅኝ ገዢዎች “የተቀበረው ቦንብ ጊዜውን እየጠበቀ ይፈነዳል” እንደሚባለው ችግሩ ከማንም በተለየ ሶማሊያዊያንን የጎዳቸው ይመስላል፡፡ የቅኝ ግዛት ሥርዓቱ ተወግዶ ነጻነታቸውን ካገኙበት እ.ኤ.አ. ከ1960 ወዲህ እርስ በርስ ግጭት ስለቆዩ፡፡

በቅኝ ገዢዎች የተተከለው የልዩነት አጥር በወንድማማቾች መሀል ለተፈጠረው ጥርጣሬና ያለመተማመን አስተዋጽኦ ሲያደርግ “አብሮነታችሁን ለማጠናከርና ሠላማችሁን ለማረጋገጥ ምን እንርዳችሁ?” ለሚሉ የውጭ ወዳጆችም በር ዘግቷል፡፡

ችግሩ አሁንም እንደ ድሮ ነው፡፡ ለሶማሊያ መከፋፈል ዋና መንስኤ የነበረችው ሶማሊ ላንድ አሁንም የሙጥኝ ባለችበት ስለሆነች፡፡ ከጎሳዎች አሠፋፈር ባለፈ የቋንቋም ሆነ የባህል ልዩነት በሌላት ሀገር-ሶማሊያ፡፡ ጥላቻው ተቀሰቀሰ፡፡ በጣሊያን ሲተዳደር የነበረው ደቡቡ ክፍል ሰሜኑን ጨቁነሀል ተባለ፡፡

በእንዲህ ከነጻነት ማግስት ጀምሮ ግጭቱ ተቀስቅሶ እ.ኤ.አ. እስከ 1991 ቀጠለ፡፡ ጊዜው ኃያላን መንግሥታት የጎራ ክፍፍላቸውን ያጧጧፉበት መሆኑ ሲታይ ስቃዩ እስከ እኛ ሀገር ሁሉ ደረሰ፡፡ ኤርትራ ከሀገራችን እንድትገነጠል ምቹ ሁኔታ ፈጠረ። በብሔረሰብ ማንነት ላይ የተመሠረተው ክልላዊ አስተዳደርም በሀገራችን ህጋዊ ቅርጽ ያዘ፡፡

ኋላ ኋላ በሁሉም የዓለም ክፍሎች እየናኘ የመጣው የብሔረተኝነት ጥያቄ እንዲህ የአፍሪካ ቀንድን ያተራመሰ ሲሆን ጣጣውም በተለያየ መልክ የሚገለጽ ነው፡፡ አንዴ ብቅ ሌላ ጊዜ ጥልቅ የሚሉ ግጭቶችን በሀገራችን ሲቀሰቅስ በሶማሊያ ግን ዘላቂ የሆነ የእርስ በርስ ጥርጣሬን ወለደ፡፡

አዎን ወንድማማቾች ሲለያዩና ቤቱም ወደ መፍረስ ደረጃ ሲደርስ ማንም ደስተኛ አይሆንም፡፡ እስካሁን ሶማሊ ላንድ ዓለም አቀፋዊ ዕውቅና ባታገኝም ወደዚያው እየተንደረደረች ትገኛለች፡፡ ሶማሊያ ደግሞ ዛሬ ምን አሰብሽ? ከማንስ ጋር ምን ተነጋገርሽ? እያለች የጎሪጥ እየተከታተለቻት ነው፡፡ መፍትሄው ግን በእንዲህ ዓይነት ያለመሆኑ ብዙዎችን እያሳሰበ ነው፡፡

ዓለም አቀፍ ቀውስ ቡድን የተባለውን ድርጅት ጨምሮ በርካታ መገናኛ ብዙሀን ተቋማትም የሚያሰሙት ሥጋት ይህንን ነው፡፡ ምናልባት አውቆ የተኛ ቢቀሰቅሱት እንደሚባለው ሆኖ የዓለም አቀፉ ማህበረሰብም ለከንቱ ልፋት እንዳይዳረግ ሥጋት ይጭራል፡፡

መረጃዎች እንደሚጠቁሙት ከሆነ ሁኔታው አሁንም በተካረረበት ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ ዋና ከተማዋን ሀርጌሳ ላይ ያደረገችው ሶማሊ ላንድ የተናጠል ዕድገቷን ለማሳመር ጥረት በማድረግ ላይ ትገኛለች። የደቡቡን ክፍል የሚያስተዳድረው የሶማሊያ መንግሥት ደግሞ ዙሪያ ገባዋን በርቀት እየተቆጣጠረ የበላይነቱን ለማሳየት ይጣጣራል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ፍጥጫ የዓለምን ማህበረሰብ ተስፋ ከቶውንም አላጨናገፈውም፡፡ ከአውሮፓ፣ ከመካከለኛው ምሥራቅም ሆነ ከአፍሪካ “እስቲ ተቀራረቡልን” የሚሉ ምኞቶች እየተጠናከሩ ስለሆነ፡፡ ሶማሊያ ካላት ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ አንጻር ኃያላን መንግሥታትን ጨምሮ፡፡

እንደ ዓለም ቀወስ ቡድን ዘገባ ከሆነ የሶማሊያና የሶማሊ ላንድ ውጥረት በኃይማኖታዊ መርሆዎች ልዩነት ምክንያት ባለፉት ዓመታት ኳታር፣ ኢራንና ቱርክ በአንድ በኩል ሆነው ከሳውዲ አረቢያ፣ ግብጽና ሌሎች ሀገራት ጋር የገቡበትን ፍጥጫ ሁሉ የሚያወሳ ነው፡፡ እነዚህ የአካባቢው ኃያላን እርስ በርስ ከሚያደርጉት ሽኩቻ በይበልጥ ለሶማሊያዊያን አንድነት መቆማቸው የችግሩ ዋነኛ መንስኤ ሶማሊያዊያን እራሳቸው እንደሆነ ያሳብቃል፡፡

ለአካባቢው የጠበቀ ቀረቤታ አላቸው የተባሉ ሌሎች ሀገራት ኢትዮጵያና ቱርክ ሲሆኑ በተለይ ቱርክ በሀገሪቱ የገነባችው ትልቅ ወታደራዊ ሠፈር ይጠቀሳል፡፡ ኢትዮጵያም ከተባበሩት አረብ ኢምሬቶች ጋር በመሆን የበርበራ ወደብን ለማልማት የገባችው ሽርክና አለ፡፡ በሀገራችን ባለፉት ጥቂት ዓመታት ውስጥ ከታየው የለውጥ መንፈስ አንጻርም ሁለቱን ወገኖች ለማቀራረብ ጥረት ተደርጓል ምንም እንኳን አቋማቸውን ማስቀየር ባይቻልም፡፡

ሌላው አወዛጋቢ ጉዳይ የፑንት ላንድ መስቀለኛ አቋም ሲሆን ይህም የሶማሊያ መንግሥት አካል ሆና ሰፊ የሆነ የራስ አስተዳደር መመሥረቷ ነው፡፡ ከቆዳ ስፋትም አንጻር ከሌሎች የፌዴራል መንግሥት ክልሎች ልቃ መገኘቷ ውዝግብ ይፈጥራል የሚል ሥጋት አለ፤ ሀገራዊ አንድነትን የሚያጠናክሩ ዕሴቶች ገና ባልተጠናከሩበት ሀገር፡፡

ከዚህ አንጻር በሰሜን ጫፍ ከምትገኘውና የራሷን ነጻነት ለማወጅ ደፋ ቀና እያለች ካለችው ሶማሊ ላንድ ጋር የገባችው የድንበር ውዝግብም ችግሩን እንዳያባብስ ተሰግቷል፤ የልዩነት አጥሮች እዚህም እዚያ ጎልተው ስለሚታዩ፡፡ ብዙ ሰዎች ባለፈው ዓመት ለሞትና ለመፈናቀል በተዳረጉባቸው አካባቢዎች የሚኖሩ ማህበረሰቦችም ከየትኛው ወገን በሚል ምርጫቸውን አሳውቀዋል፡፡

እስከ ሀገራችን ድረስ ጫናው የታየውን ግጭት ለማስቀረት ሲባል ነው የተለያዩ መንግሥታዊና መንግሥታዊ ያልሆኑ ተቋማት ጥረታቸውን እያደረጉ የሚገኙት፡፡ ሰሞኑን የዩጋንዳው ፕሬዝዳንት ይወሪ ሙሰቨኒ ያስተላለፉት መልዕክትም የዚህ አንድ ማሳያ ነው ምንም እንኳን በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ ሆኖ ቢታይም፡፡

በተለያዩ የውጭ መገናኛ ብዙሀን ፕሬዝዳንቱ የተናገሩት “በመሀላችሁ ሆኜ ላሸማግላችሁ፤ ላስታርቃችሁ“ የሚል ሲሆን ሀሳባቸውም ከማንም ቅን አሳቢ ሊነሳ የሚችል ነው፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ የረጅም ቂምና ቁርሾ ይዘው የቆዩ ሀገራት በክብ ጠረጴዛ ዙሪያ መተቃቀፋቸው የስኬታማ ሽምግልናና ዲፕሎማሲ አንድ ማሳያ ነው፤ ምንም እንኳን ፕሬዝዳንቱ የፍላጎታቸውን ያህል አዎንታዊ ምላሽ ባያገኙም፡፡

ከሶማሊያ መንግሥት በኩል የሚታየውን ቀና አመለካከት ሶማሊላንድ ሁል ጊዜ ውድቅ እንደምታደርገው ሁሉ በአሁኑ ምላሽም የተገለጸው ይህ ነው፡፡ ለመነጋገር ዕቅድ የለኝም በማለት፡፡ ውይይት ቢደረግም ስለ አንድነትና ውህደት ሳይሆን በተለየ መንገድ መሆን እንዳለበትም ነው መግለጫው ያተተው፡፡ “ቀድሞ የተዋሀዱ ህዝቦች በተናጠል ማደግ አለባቸው” በማለት፡፡

ከዚህ አንጻር ከተመለከትን ሁኔታው የሚያሳየው የልዩነትና የተናጠል አቋሞች ከአንድነት ይልቅ ጎልተው መታየታቸውን ነው፡፡ ቀደም ሲል ቅኝ ግዛት በፈጠረው ልዩነት ላይ ባለሥልጣናትም የራሳቸውን ፍላጎት ጨምረውበት፡፡ በአካባቢው ጎልተው የሚታዩ ተፈጥሯዊና ሠው ሠራሽ ችግሮችንም ላለማየት አይናቸውን በመጨፈን፡፡

እንዲህ ጦርነት በሌለበትና ነገር ግን ሥጋት ባልጠፋበት ህይወትን እንዴት መግፋት ይቻላል በሚለው ላይም ባለሙያዎች ሀሳባቸውን እየሰጡ ቆይተዋል። በተለይ የዓለም ቀውስ ቡድን የተባለው ድርጅት ችግሩን በስፋት ሲዘረዝር የተለያዩ አማራጮችን ጠቁሟል፡፡

ከእነዚህ መካከል የምጣኔ ሀብታዊ ውህደትና ጸጥታ ተጠቃሽ ሲሆኑ በአካባቢው ተመርተው ወደ ውጪ የሚላኩ የእንስሳት ምርቶችና የጋራ የሆኑ የገቢ ምንጮችን ያካትታል፡፡ ከሠላምና ጸጥታ አንጻርም እንደ ህገ-ወጥ ንግድ፣ የባህር ላይ ውንብድናና አሸባሪው አልሸባብ የሚያደርሰውን ጥቃት ገልጸዋል፡፡ በእነዚህ መስኮች በትብብር ከሠሩ የጋራ ፍላጎቶቻቸውን ማሳካት እንደሚችሉ በማስታወቅ፡፡

ችግሩን ለመፍታት የአፍሪካ ህብረትን ጨምሮ የሁሉም አካላት ድጋፍም ተጠይቋል፤ ምንም እንኳን ሀገራችን ኢትዮጵያን ጨምሮ ጥረት ያላደረገ ባይኖርም፡፡ ወደፊትም ሀገራችን የበርበራ ወደብን ለማልማት ካላት ፊላጎት አንጻር ጥረቱ ተጠናክሮ መቀጠል የሚችል ነው፡፡