የሚገነቡ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

የሚገነቡ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቁ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑ ተገለጸ

ሀዋሳ፡ ሐምሌ 01/2017 ዓ.ም (ደሬቴድ) በሕዝብ የነቃ ተሳትፎ የሚገነቡ የልማት ሥራዎች በተያዘላቸው የጊዜ ገደብ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል ጥረት እየተደረገ መሆኑን የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳደር ገለጸ፡፡

ከ385 ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የዳዉሮ ብሔር የባህልና ታሪክ ምርምር ማዕከል የአዳራሽ የግንባታ ሥራ ዳግም ለማስጀመር የሚያስችል ስምምነት ላይ መደረሱ ተገልጿል።

የግንባታው ሂደት መቋረጡ በኅብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታን ሲፈጥር መቆየቱ ተጠቁሟል።

ከጥቂት ዓመታት በፊት የዳዉሮ ብሔር የባህልና ታሪክ ምርምር ማዕከል የግንባታ ሂደት ተጀምሮ ሳይጠናቀቅ ቆይቷል።

ከዚህ ቀደም ግንባታውን ሲሰራ የነበረው ተቋራጭ በውሉ መሠረት በተባለው ጊዜ ሳያጠናቅቅ በማዘግየቱ፣ የግንባታውን ሕግ እና ሥርዓት ያልተከተለ የዋጋ ጭማሪ በማድረጉ ምክንያት እንዲሁም በገዛ ፍቃዱ ውሉን ለማቋረጡ መነሻ ሃሳብ በማቅረቡ ምክንያት እንደሆነም ተገልጿል።

ይሁን እንጂ ዳግም የማስጀመሪያ ሥራ ከዚህ ቀደም የተደረገ ሲሆን ድጋሚ ከተቋረጠ ሰባት ወራትን በማስቆጠሩ በነዋሪዎች ዘንድ ቅሬታ መፍጠሩን ተገልጿል።

በኅብረተሰብ የነቃ ተሳትፎ የሚገነባ በመሆኑ የግንባታው ሂደት በመቋረጡ ምክንያት በኅብረተሰቡ ዘንድ ቅሬታን ሲፈጥር ነበር።

የምርምር ማዕከሉ ግንባታ በሕዝቡ ተሳትፎና ድጋፍ እየተገነባ እንዳለ ከነዋሪዎቹ መካከል አቶ ተረፈ ገብሬና አቶ አየለ አባ የተናገሩ ሲሆን ዳግም መጀመሩ ደስታን እንደሰጣቸው ገልጸዋል።

ማዕከሉ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያለው በመሆኑ የተጀመረው እስኪጠናቀቅ ድረስ የድርሻቸውን እንደሚወጡም ተናግረዋል።

በማስጀመሪያው ዕለት የዞኑ ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ እንደገለፁት የዳዉሮ ዞን ባህልና ታሪክ ምርምር ማዕከል የአዳራሽ ግንባታ ከዚህ ቀደም በታወር ኮንስትራክሽን የሕንጻ ተቋራጭ ግንባታው ሲካሄድ እንደነበር አስታውሰው፥ አሁን ላይ ግን፣ የመንግሥት ልማት ድርጅት ከሆነው ኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ኮርፖሬሽን በአሰራሩ መሠረት ወቅቱን የጠበቀ የመሃንድስ ግምት መነሻ ተደርጎ በ385 ሚሊዮን 509 ሺህ 26 ብር መነሻ ዋጋ በአንድ ዓመት ውስጥ ግንባታውን እንዲያጠናቅቅ የሚያስችል የውል ስምምነት እንዲደረግ የጋራ መግባባት ላይ ተደርሷል።

የተቋረጠውን ግንባታ ዳግም ለማስጀመር እንዲቻል በተለይም የቦርዱ የበላይ ጠባቂና የቦርዱ አባላት ላቅ ያለ አስተዋጽኦ ማበርከታቸውንም ገልጸዋል።

የኦሮሚያ ኮንስትራክሽን ድርጅት የዳዉሮ አካባቢ ፕሮጀክቶች ሥራ አስኪያጅ ኢንጂነር ለማወርቅ ጌታቸው በበኩላቸው እስካሁን በጥሩ የአፈጻጸም ሂደት ላይ የሚገኘው ድርጅታቸው በተያዘለት የጊዜ ገደብ ባጠረ ጊዜ ለማጠናቀቅ ጥረት ይደረጋልም ብለዋል።

ድርጅታቸው የሁለቱን ክልሎችን የሕዝብ ትስስር ለማጠናከር እንዲቻል በተቀናጀ ጥረት ግንባታውን እንደሚያካሂድ ተገልጿል።

የሕዝቡና የመንግሥት ቁርጠኛ ድጋፍና ክትትል ለግንባታው ሂደት ወሳኝ እንደሆነም ተናግረዋል።

የግንባታው ሂደት ዳግም እንዲጀመርም የበኩላቸውን አስተዋጽኦ ሲያበረክቱ ለነበሩ ሁሉ የዞኑ አስተዳደር በዳዉሮ ሕዝብ ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ መሳይ መሰለ – ከዋካ ጣቢያችን