“አትችይም የሚሉትን አሸንፌአለሁ”

“አትችይም የሚሉትን አሸንፌአለሁ”

በደረሰ አስፋው

የሞቀውና የደመቀው ቤተሰብ ሞት በሚሉት ጠላት ተፈተነ፡፡ በፍቅር የጸናው አብሮነት ንፋስ ገባበት፡፡ በወላጅ አባት የተከሰተው ሞት ብዙም ሳይቆይ እናቷንም ወሰደ፡፡ ሲሳይ ታደሰና ሌሎች 6 ወንድሞቿ ለችግር ተዳረጉ፡፡ አካል ጉዳተኛ ለሆነችው ባለታሪካችን ደግሞ ችግሩ የተለየ መልክ ነበረው፡፡ ደጋፊዋ የነበሩት እናቷ ከጎኗ በመለየታቸው ችግሩ ድርብ ሆነባት፡፡ ያም ሆኖ መፍትሄው በሀዘን መቆዘም አለመሆኑን ተገነዘበች፡፡ የጀመረችው ትምህርት እውን ይሆን ዘንድ የራሷ የገቢ ምንጭ ፈጠረች። የጸጉር ስራ፡፡

የጸጉር ስራዋን ገቢ ከመጀመሪያ ደረጃ እስከ ዩኒቨርስቲ መግቢያ ድረስ ለሁለገብ አገልግሎቶች በመጠቀም ለዛሬው ህይወቷ መሰረት ሆነ፡፡ ለቀለብ ቢሆን ለልብስ፤ ለትምህርት ቁሳቁስና ለሌሎች አገልግሎቶች ይሄው ከጸጉር ስራ የምታገኘው ገቢ ነው። ስለሁኔታው ስትገልጽም “በዚህ አልከፋኝም፤ ራዕዬን እውን አደርግ ዘንድ አገዘኝ እንጂ” ስትል ነው የተናገረችው፡፡

ባለታሪካችን ሲሳይ ታደሰ የተወለደችው በሲዳማ ክልል፣ ይርጋለም ከተማ ነው፡፡ ሲሳይ ይህን ዓለም ስትቀላቀል ጤናማ አካል ነበራት። በዚህ ግን አልቀጠለም፡፡ በአጋጣሚ በደረሰባት ጉዳት ከጓደኞቿ ጋር ቦርቃ ከተጫወተችበት መንደር በድንገት የመገለል እጣ ፈንታ ገጠማት፡፡ ድንገት ወድቃ እግሯ ላይ ጉዳት ደረሰ፡፡ አንድ እግሯ መንቀሳቀስ ተሳነው፡፡ በወቅቱ ወደ ሁነኛ ወጌሻም ሆነ ህክምና አልወሰዷትም፡፡

ችግሩ እየከፋ ሄዶ በ10 ዓመቷ ለአካል ጉዳት ተጋለጠች፡፡ ያጋጠማት ችግር ለብዙ ዓመታት በጉልበቷ በመዳህ ለመሄድ አስገደዳት፡፡ ቢዘገይም ለህክምና ወደ ሻሸመኔ በመውሰድ የቀዶ ህክምና አግኝታ ብሬስ ተገጠመላት፡፡ በዚህ ቆማ ለመሄድ ዕድል አገኘች፡፡ ይህም የመማር እድሏን አመቻቸላት፡፡

የመማር ጊዜዋ በችግር ቢባክንም በ12 ዓመቷ ትምህርት ቤት ገባች፡፡ ከነበራት የመማር ፍላጎት የተነሳ የ2 ሰዓት የእግር ጉዞ በመሄድ ነበር ትምህርቷን የተከታተለችው። ለአካል ጉዳተኞች ምቹ ባልሆነ መንገድ ከአስቸጋሪ ሁኔታ ጋር እየታገለች ትምህርቷን ትከታተል ነበር፡፡ ክራንቿ አለያም በእግሯ ላይ የተገጠመላት “ብሬስ” ሲሰበር እንኳ በእንብርክክ በመሄድ ይለውጠኛል የምትለውን ትምህርት አልዘነጋችውም፡፡ ይበልጥ አነሳሳት እንጂ፡፡

በጋን አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ተምራ ከ9ኛ እስከ 12ኛ ክፍል ደግሞ በይርጋለም 2ኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተከታትላለች፡፡ የመሰናዶ ትምህርት መግቢያ ጥሩ ውጤት እንዳመጣች ሁሉ የዩኒቨርስቲ መግቢያ ፈተናንም ጥሩ ውጤት በማምጣት ወደ ከፍተኛ የትምህርት ተቋም መግባት ቻለች፡፡

መጀመሪያ ላይ ወደ ጎንደር ዩኒቨርስቲ ተመደበች፡፡ ይሁን እንጂ ካለባት የአቅም ውስንነት የተነሳ ሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የመማር እድል አገኘች፡፡ ተግዳሮት ያልተለየው የሲሳይ ህይወት በሌላ ችግርም መፈተኑ አልቀረም፡፡

ከላይ በመግቢያችን ላይ የነገርናችሁ የእናቷ ሞት በዚህ ጊዜ ነበር የተከሰተው። እናቷን በመኪና አደጋ በማጣቷ ተምራ ለመድረስ የነበራት እቅድ ፈተና ላይ የወደቀው። አካል ጉዳተኛ መሆኗ ደግሞ ችግሯን አገዘፈው፡፡ እናቷን ማጣቷ ከፈጠረባት ሀዘን በተጨማሪ ችግርም ተጫናት፡፡ ሌላ የሚረዳት አለያም ድጋፍ የሚያደርግላት አካል አልነበረም።

በመኖሪያ አካባቢዋ የጸጉር ስራ ላይ ለመሰማራት የተገደደችውም በዚህ ምክንያት ነው፡፡ ስለ ሁኔታው ስትገልጽ፡-

“እወጣዋለሁ ብዬ ያላሰብኩትን ችግር ተጋፍጫለሁ፡፡ ዛሬ ላይ ወደ ኋላ መለስ ብዬ ሳስበው ልዩ ስሜትን ይፈጥርብኛል። ቤተሰብ ከማጣት ሌላ የአካል ጉዳተኛ መሆኔም ችግር ነበር፡፡ ማህበረሰቡ ለአካል ጉዳተኞች የሚሰጠው አመለካከት በራሱ ችግር ነው። እየቻልኩ አትችይም የሚሉትም እንዲሁ ለእኔ ፈተና ነበሩ፡፡ ይሁን እንጂ ተስፋ አልቆረጥኩም” ነው ያለችው፡፡

በ2006 ዓ.ም በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ትምህርቷን መከታተል የጀመረችው ሲሳይ በሶሾሎጂ ትምህርት የመጀመሪያ ዲግሪ ይዛለች፡፡ በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ የነበራት ቆይታ ግን ጥሩ እንደነበር አንስታለች። በዩኒቨርስቲው ውስጥ አይነስውራንና ሌሎች አካል ጉዳተኞችን ለመደገፍ ሲባል ከዩኒቨርስቲው የሚሰጣትን አነስተኛ ክፍያ ለሚያስፈልጋት ወጪዎች ትጠቀም ነበር፡፡

“በህይወት ውስጥ አካል ጉዳተኛም ሆነ ሌላው ጉዳት አልባ ሰው በተግዳሮት የተሞላ እንደሆነ እገነዘባለሁ፡፡ ተግዳሮቱን መቀበሉ ግን እንደሰው ይለያያል፡፡ የሚያጋጥሙኝን ተግዳሮቶች በጥሩ ጎን ነው የምቀበላቸው፡፡ መድረስ ያለብኝን ነበር የማየው እንጂ ችግርን አልነበረም፡፡ የሚገጥሙኝ የህይወት ፈተናዎች አርቄ እንዳስብ አድርገውኛል፡፡ ይህም ለውጤት አብቅቶኛል፡፡ እንዲያውም አካል ጉዳተኛ ሆነው ሲለምኑ ሳይ አስተምሬ አልፍ ነበር፡፡ አካል ጉዳተኞች ከሰሩ ለመለወጥ የሚገድባቸው ሀይል ባለመኖሩ ሰርተው እንዲለወጡ አነሳሳቸው ነበር” ብላለች፡፡

ሲሳይ ከ2013 ዓ.ም ጀምሮ በስራ ላይ ነች፡፡ በሀዋሳ ከተማ ምስራቅ ክፍለ ከተማ ሴቶችና ህጻናት የሴቶች አደራጅ ባለሙያ በመሆን እያገለገለች ነው፡፡ ባለትዳርና የአንድ ልጅ እናት የሆነችው ሲሳይ ከባለቤቷ ጋር ህይወታቸውን በመደጋገፍ ይመራሉ፡፡

በልጅነቷ የምትመኘው ብዙ ቢሆንም ከዚያ ጥቂቱን ማግኘቷን ነው ያጫወተችን። ይሁን እንጂ አሁንም በየመንገዱና በቤት ውስጥ ተደብቀው ያሉ አካል ጉዳተኞች እንዲሁም ጧሪና ደጋፊ የሌላቸውን አረጋዊያንን ለመደገፍ የነበራት ህልም ገና ነውና፡፡ ይህንንንም ለማድረግ ጥረት እንደምታደርግ ነው የተናገረችው፡፡

አካል ጉዳተኛ መሆን ለልመና የሚዳርግ አለመሆኑን የምትናገረው ባለታሪካችን ከመለመን ይልቅ ሰርቶ ማግኘት እርካታን የሚፈጥር መሆኑን በመጠቆም “አካል ጉዳተኛ ነህ፤ እጅ እግር የለህም እንዴ” የሚባለው አባባል ትክክል አይደለም ባይ ነች፡፡ የአካል መጎዳት ሳይሆን ዋናው አስተሳሰብ በመሆኑ መሰል አባባሎች ሊታረሙ ይገባል ስትል ትሞግታለች፡፡

ሲሳይ አካል ጉዳተኛ የሆነች ሴት ጓደኛ አላት፡፡ በትርፍ ጊዜዋ ከዋና ስራዋ በተጨማሪ ምግብ ቤት ከፍታ ትሰራለች፡፡ ጓደኛዋ በእጇ ተደግፋ እንደምትሄድ ነው የገለጸችው፡፡ በስራ ግን ታታሪና ለብዙዎች ምሳሌ የምትሆን ናት፡፡ ሲሳይ በልመና የተሰማሩትን አካል ጉዳተኞች እሷ ዘንድ በመውሰድ ልምዷን እንድታጋራቸው በማድረግ በርካቶች እንዲለወጡ ማድረጓን ነው የተናገረችው፡ ፡ አካል ጉዳተኛ አግብቶ መውለድ፣ ሰርቶ መለወጥ ስለሚችል አካል ጉዳተኞች መቻላቸውን በተግባር እያሳዩ ነው ስትልም ነው የምትሞግተው፡፡

ሲሳይ አካል ጉዳተኛ እንደመሆኗ ትዳሯ ተፈትኖ እንደነበርም ነው የተናገረችው። “ሰው ጠፍቶ ነው አካል ጉዳተኛ ለማግባት የፈለከው” በሚል ባለቤቷ ላይ ከሌሎች ተጽእኖ ይደርስበት እንደነበር ትናገራለች። እንዲያውም የወለደች እለት ልጇን ሊያዩ የመጡ እንደነበርም ነው ታስታውሳለች፡፡ ይሁን እንጂ እሷና የትዳር አጋሯ ፈተናዎችን በፅናት በማለፍ በፍቅርና በመተጋገዝ ህይወታቸውን እየመሩ ነው፡፡

ወደፊት ሲሳይ አካል ጉዳተኞች ከልመና ወጥተው ሰርተው መለወጥ እንዲችሉ የማድረግ ራዕይ አላት፡፡ አካል ጉዳተኞች የሚለወጡበትን መንገድ ማመቻቸት ህልሟ ነው፡፡ ደጋፊ ያጡ የእድሜ ባለጸጋዎችን የመደገፍ ስራ መስራት ምኞቷ እንደሆንም ነው የተናገረችው፡፡

አካል ጉዳተኞች ከመሰረተ ልማት ችግር የተነሳ እየተፈተኑ እንደሆነም አንስታለች፡፡ አንዳንድ ግለሰቦች በህዝብ ትራንስፖርት አገልግሎት አካባቢ ሲያዩን ከመርዳት ይልቅ ለአንቺ አይመችም በማለት ተጽእኖ እንደሚፈጥሩ ነው የተናገረችው፡፡ በመስሪያ ቤቷ አካል ጉዳተኛን ታሳቢ ያደረገ ትራንስፖርት አለመኖሩንም ገልጻለች፡፡

መንግስት ለአካል ጉዳተኞች ድጋፍ ሊያደርግ ይገባል፡፡ ማህበረሰቡም አካል ጉዳተኞች መስራት እንደሚችሉ በመረዳት ድጋፍ ሊያደርጉላቸው እንደሚገባ ነው አስተያየቷን የሰጠችው፡፡ ተምረው በስራ ቅጥር ላይ አትችይም/አትችልም/ እየተባሉ ለእንግልት የተዳረጉ ስላሉ እልባት ሊሰጣቸው ይገባል፡፡ ይህ አይነቱ የተሳሳተ እሳቤ አካል ጉዳተኞች ጎዳና ላይ እንዲወጡ የሚገፋፋ በመሆኑ ሊታረም ይገባል ትላለች፡፡

የስራ ባልደረባዋ የሆነችው ወጣት ሄለን በበኩሏ “ሲሳይ ለኛም አርዓያ የሆነች ታታሪ ሰራተኛ ነች” ስትል ነው የተናገረችው፡፡ በስራ አጋጣሚ ከተገናኙ በኋላ ከሷ የተማረችው በርካታ ነገር እንዳለ በመጠቆም፡፡ አካል ጉዳተኛ በመሆኗ የበደለችው ስራ እንደሌለና እንዲያውም ለሌሎች ምሳሌ መሆኗን ነው የተናገረችው፡፡ “ከእሷ ብዙ ነገር ተምሬያለሁ። እውቀቷን ታጋራለች፡፡ አይችሉም የሚለውን አስተሳሰብም የቀየረች ናት” ስትል ነው ምስክርነቱን ሰጥታለች፡፡