“እርካታዬ የሰው ሕይወት ማዳን ነው” – ሲስተር ተዋበች አለሙ

በአብርሃም ማጋ

“የሰው ልጅ ሕይወት ማዳን በሚሊየኖች ከሚቆጠር ገንዘብ በላይ ያረካኛል” በማለት ነው በርዕሱ ላይ የተናሩትን ሃሳብ የሚሰነዝሩት ሲስተሩዋ፡፡ ገንዘብ ሰው ሰራሽ ቁስ ሲሆን የሰው ሕይወት ግን ከሁሉም ነገር በላይ የሆነ የፈጣሪ ጥልቅ ጥበብ ነው በማለት ያክላሉ፡፡

በመሆኑም ሰው የፈጠረውን ነገር ከፈጣሪ ስራ ጋር ማወዳደር ከስብዕና ውጪ ያደርገናልም ይላሉ፡፡ ለዚህም ይሆናል መልካም ስብዕና ተላብሰው በስራቸው ተግተው ደከመኝ፣ ሰለቸኝ፣ እኔን አይመለከተኝም ሳይሉ የእረፍት ጊዜያቸውን ጭምር ሰውተው ሁሌ ሙያቸውን ለነፍስ አድን ስራ የሚያውሉት፡፡

“ለእኔ ስራ ማለት በደሜና በአጥንቴ ውስጥ የተዋሃደ ነው” በማለት የተናገሩትም ይሞታሉ የተባሉ ወላጆችና ህጻናት ሲተርፉላቸው ከፈጣሪ በታች በሙያቸው የሰውን ሕይወት ማትረፍ በመቻላቸው እንደሆነም በደስታ ይናገራሉ፡፡

ሲስተር ተዋበች አለሙ የተወለዱት በቀሞው አጠራር በሲዳሞ ጠቅላይ ግዛት በጌዴኦ አውራጃ ዲላ ከተማ በ1952 ዓ.ም ነው፡፡ አሁን 63ኛ ዕድሜያቸው ላይ ይገኛሉ። ዕድሜያቸው ለትምህርት ሲደርስ በዲላ ከተማ አጼ ዳዊት 1ኛ ደረጃና በመንግስት ሁለተኛ መለስተኛ ደረጃ ት/ቤት ከ1ኛ እስከ 8ኛ ክፍል ድረስ ተምረዋል፡፡

በመቀጠልም ከ9ኛ እስከ 10ኛ ክፍል በይርጋለም ሁለተኛ ከፍተኛ ደረጃ ት/ቤት አጠናቀዋል፡፡ 11ኛ ክፍል ደግሞ በአዲስ አበባ ካቶሊክ ካቴድራል ት/ቤት ከጨረሱ በኋላ 12ኛን ክፍል በሐዋሳ ታቦር ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ት/ቤት ተምረው አጠናቀዋል፡፡

የ12ኛ ክፍል መልቀቂያ ብሄራዊ ፈተና የማለፊያ ውጤት አስመዝግበው አዲስ አበባ ጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ተመድበው ለ3 ዓመታት ተከታለው በነርሲንግ ሙያ በዲፕሎማ ተመርቀዋል፡፡ ከተመረቁ በኋላም በቀድሞው ሲዳሞ ክፍለ ሀገር በነጌሌ ቦረና አውራጃ በሚገኝ ሆስፒታል ተመድበው በሰለጠኑበት ሙያ መስራት ጀመሩ፡፡

ቀደም ሲል ወደ ዚህ ሙያ እንዲገቡ የእሳቸውና የቤተሰባቸው ምኞት እንደነበር ገልጸው ወደ ስራው ሲሰማሩ ሙያውን ወደውት ነበር፡፡ አነስተኛ የሰው ሃይል በነበረበት ሆስፒታል ገብተው ሲሰሩ በልበ ሙሉነትና በወኔ ነበር፡፡

ወቅቱ የኢትዮ- ሶማሊያ ጦርነት ስለነበር በርካታ ቁስለኞች ከሁለቱም ወገኖች ሲመጡ እረፍት በሌለበት ሁኔታ የነፍስ አድን ስራ ያከናውኑ ነበር፡፡ ከፍተኛ የስራ ጫና ቢፈጥርባቸውም ሳይበገሩ ወገባቸውን ጠበቅ አድርገው ደከመኝ ሰለቸኝ ሳይሉ ይሰሩ ነበር። የአካባቢው ነዋሪዎችንም በተመሳሳይ ሁኔታ አገለገሉ፡፡

በመሆኑም የተማሩትን ሙያ ልምድ አካብተውበት በሚያደርጉት እንቅስቃሴ በህብረተሰቡ ዘንድ ተወዳጅነት አግኝተው ለስድስት ዓመታት ካገለገሉ በኋላ ወደ ይርጋለም ከተማ ይዛወራሉ፡፡ በይርጋለም ጤና ጣቢያ ከፍተኛ የሙያ ፍቅራቸውን በማሳየት በተሻለ አፈጻጸም ለ5 ዓመታት ካገለገሉ በኋላ በ1982 ዓ.ም ወደ ሐዋሳ ከተማ ተዛወሩ፡፡

በከተማዋም በጤና አጠባበቅ ጣቢያ ተመድበው ለ5 ዓመታት ከሰሩ በኋላ የሙያ ማሻሻያ ስልጠና እንዲሰለጥኑ ዕድል ተሰጣቸው፡ ፡ ስልጠናውም የማዋለድ ሙያ አገልግሎት ሲሆን አንድ ዓመት ከግማሽ ተከታትለው ተመረቁ፡፡

ቀደም ሲል ማንኛውንም ዓይነት በነርስ ደረጃ የሚሰሩ ስራዎችን ይሰሩ ከነበረበት ወጥተው በማዋለጃ ክፍል ተመደቡ፡፡ ስራውንም በጣም ወደዱት፡፡ በማዋለጃ ክፍል የሚሰጡ አገልግሎቶች እናቶችን ማዋለድ፣ ነፍሰ ጡሮችንና ህጻናትን መመርመርና ማከም ነው፡፡

በዚሁም እሳቸው በክፍሉ ውስጥ ግምባር ቀደምትነት ሚናቸውን በትጋትና በብርታት መጫወት ጀመሩ፡፡ በወቅቱ በጣቢያው ለህክምና አገልግሎቶች የሚውሉ ቁሳቁሶች ምንም የሉም በሚባል ደረጃ ባለመኖራቸው በስራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ መፍጠሩን ያብራራሉ፡፡

ለህጻናት ህክምና ብቻ የተወሰኑ ከዩኒሴፍ ድጋፍ የተገኙ ቁሳቁሶች ቢኖሩም በሌሎቹ ላይ ከፍተኛ ችግር ነበር፡፡ ለአገልግሎቱ የሚውሉ ቁሳቁሶችን ታካሚዎች ከውጭ እንዲገዙ ያደርጋሉ፡፡

የህክምና ቁሳቁሶች በጣቢያው እያለ ከውጭ እንዲገዙ የሚደረጉ መስሎአቸው ቅሬታ የሚያሳድሩ እንዳሉም ገልጸዋል፡፡ ነገር ግን እሳቸው በበኩላቸው ደም እየፈሰሳቸው የሚመጡትን ህጻናት ደም ለማቆም በአስቸኳይ የመጀመሪያ ደረጃ ህክምና ለመስጠት የስራ ልብሳቸውን (ጋወናቸውን) ቀድደው በማሰር እርዳታ ይሰጡ ነበር፡፡

በዚህ ሁኔታ እየሰሩ እያሉ የጤና አጠባበቅ ጣቢያው ወደ አዳሬ ሆስፒታልነት ሲያድግ በመንግስት በኩል የተደረገው እገዛ ከፍተኛ ሲሆን የራሳቸው ሚናም ቀላል እንዳልነበረ ነው የሚናገሩት፡፡

ሲስተር ተዋበች በጣቢያው ሙያቸውን ሳይሰስቱ እናቶችን በማዋለድ፣ ነፍሰ ጡሮችንና ህጻናትን በመመርመርና በማከም በሚሰጡአቸው አገልግሎቶች በህብረተሰቡ ዘንድ ከፍተኛ ዕውቅናና እምነት አትርፈዋል፡፡

“እሳቸው ጋ ብሄድ ያለችግር እወልዳለሁ፤ ልጄን ያድኑልኛል” በማለት ብዙዎች ተስፋ ይጥሉባቸው ነበር፡፡ በዚህ ዙሪያ በርካታ ስራዎችን በመስራት የብዙ ሰዎችን ህይወት ታድገዋል፡፡ ለዚህም ነው “እኔ ሳዋልድ አንድም እናት በወሊድ ምክንያት ሞታብኝ አታውቅም” በማለት ፈጣሪያቸውን የሚያመሰግኑት፡፡

በዚህ መነሻ ከሰጡአቸው አገልግሎቶች የማይረሱትን እንዲነግሩን ጠይቀናቸው ነበር። ሶስት ገጠመኞቻቸውን ነግረውናል፡-

አንዲት እናት እቤቷ ተገላግላ እንግዴ ልጅ በሆድዋ ቆይቶ በባህላዊ ዘዴዎች ቢሞክሩም ለውጥ ሳያመጣ ይቀራል፡፡ በዚሁ እያለች የሰፈሯ ሴቶች ለአራስ ምርቃት መጥተው ኖሮ የተፈጠረው ችግር ይገለጽላቸዋል፡፡

በአስቸኳይ ሐዋሳ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ሲስተር ተዋበች አለሙ ጋር እንዲወስዷት ይመክራሉ፡፡ በተነገራቸው መሰረት ሲያደርሷት ሰውነቷ አባብጦ በሞት አፋፍ ነበረች፡፡ ሲስተር ተዋበች ሁኔታዋን ተመልክተው ወዲያውኑ ተረባርበው ባደረጉላት የህክምና እርዳታ ተገላግላ የሴትየዋ ሕይወት መትረፉን ነግረውናል፡ ፡ ሴትየዋም ለውለታዋ አመስግናቸው ወደ ቤቷ መመለሷን ያስታውሳሉ፡፡ ይህ አንደኛው ገጠመኛቸው ነው፡፡

ሌላው ደግሞ፤ አንዲት እናት አድራሻዋ ጨፌ ኮትጀቤሳ የሚባል ቀበሌ ነዋሪ ነች። ቀበሌው ከሐዋሳ ከተማ በቅርብ ርቀት ላይ ይገኛል፡፡ ሴትየዋ የአሁኑ እርግዝናዋ ሁለተኛዋ ሲሆን አንድም ቀን ቅድመ ወሊድ ምርመራና ክትትል አድርጋ አታውቅም ነበር፡፡

በዚህ ሁኔታ እያለች ህመም ሲሰማት ወደ ግል ህክምና ማዕከል ያደርሱአታል፡፡ ማዕከሉም ምርመራ አድርጎላት የምጥ ስሜት ሳይሆን መንታ ልጆች እንዳረገዘች ገልጾ ምጥ ሲይዛት ሆስፒታል እንድትሄድ መክሮ ይሸኛታል፡፡

መንታ አርግዛለች የሚባለውን ነገር ስትሰማ በእጅጉ ተረበሸች፡፡ ነጋ ጠባ ማልቀስና መጨነቅ የዘወትር ስራዋ ሆነ፡፡ በጭንቀት ተወጥራ እያለች ምጥ ይይዛታል፡፡ ባለቤቷ ሾፌር ስለነበር ሆስፒታል ሊወስዳት ይጭናታል፡፡ የነፍሰ ጡሯ እናት አብረዋት ነበሩና የት ነው የምንሄደው ብላ ባለቤቷን ጠየቁት፡፡

በድንጋጤ ተውጦ የነበረው ባለቤቷም የመንግስት ሆስፒታል ወዳለበት ነው አሏት። ሴትየዋም “ሌላ ቦታ አንሄድም በሐዋሳ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ሲስተር ተዋበች ከዳበሰቻት ልጄ ምንም አትሆንም፤ በሰላም ትገላገላለች፤ መንታ ነው የተባለው ነገርም እውነት ላይሆን ይችላልና እሳቸው ጋ መሄድ ይሻላል” ብለው አስረዱት፡፡

ባለቤቷም ሆስፒታል ታዝዘን እንዴት ወደ ጤና ጣቢያ እንወስዳታለን በማለት ተደነጋገረ፡ ፡ የነፍሰጡሯም እናት “ግድ የለህም ሲስተር ተዋበች አንተ ከምትላቸው ሰዎች የማትተናነስ ናት፡፡ እኔ በደንብ ስለማውቃት እዛው እንሂድ” ብለው አሳምናው ወሰዱት፡፡

እንደደረሱም ሲስተሯ ነፍሰ ጡሯ በመሳሪያ እንድትታይ አደረጉአትና ጽንሱ መንታ አለመሆኑን አረጋገጡ፡፡ መንታ ያስመሰለው ከህጻኑ ጋር ሆድዋን የሞላው ፈሳሽ እንደሆነ ነገሩአቸው፡፡ በዚህም ሌላ ችግር የለም በሰላም ትገላገላለች ብለው አጽናኑአቸው፡፡

የነፍሰጡሯን እናት ከአጠገባቸው አድርገው ካዋለዱ በኋላ ህጻኑን አስታቅፋቸው ያ ሁሉ ጭንቀት ተወግዶ ቤቱ በእልልታ ቀለጠ ሲሉ ሁለተኛ ገጠመኛቸውን አጫውተውኛል።

ሶስተኛው ጉዳይ ደግሞ እሳቸው በማዋለጃ ክፍል ከሚሰሩበት ወጥተው የህጻናት ህክምና ክፍል ሲሄዱ በበሩ ላይ አንዲት እናት ህጻን ልጅ ይዛ እያለቀሰች ስትወጣ አገኙአት። “ምንድነው?” ብለው ሲጠይቋት “ልጄ ስለማይድን ወደ ቤት ውሰጂው ተብዬ ነው” አለቻቸው፡፡ “ለምን?” ብለው ሲጠይቋት “ለህክምና ሳታመጪው አቆይተሽ ታሞ፣ ከሰውነት ተራ ወጥቶ፣ ከስቶና ደቅቆ ሞት አፋፍ ላይ ሲደርስ ያመጣሽውን አናክምም፤ ደግሞም ልጁ አይድንም ብለውኛል” አለቻቸው፡፡

በዚህም መለኛዋ ሲስተር ያደረጉት ነገር ቢኖር ህጻኑን ከእጅዋ ላይ ነጥቀው ማዋለጃ ክፍል ወስደው ጸጉሩን ላጭተው ከመረመሩት በኋላ ጉሉኮስ ሰኩለት፡፡ በተጨማሪም በአፍ የሚሰጥ መድሃኒት ሰጥተውት ክትትል ጀመሩ። ከትንሽ ቆይታ በኋላ ይሞታል የተባው ህጻን አይኑን ገለጥ አደረገ፡፡

በመቀጠልም ሌላ በአፍ የሚሰጥ መድሃኒት ከመድሃኒት ክፍል አምጥተው ሲሰጡት መንቀሳቀስ ጀመረ፡፡ ህጻኑ አቅም ሲያገኝ የመድሃኒቱን አጠቃቀም ለእናቱ ነግረዋት ወደ ቤቷ እንድትወስደውና በየሳምንቱ እየመጣ እንዲታይ አድርገውት ከተከታተሉት በኋላ ሙሉ በሙሉ መዳኑን አጫውተውኛል፡፡

ያ ልጅ አድጎ ትምህርቱን ተምሮ፣ አጠናቅቆና ተመርቆ ስራ ሊቀጠር የህክምና ምርመራ እንዲፈጽም ወደ ሐዋሳ ጤና አጠባበቅ ጣቢያ ይላካል፡፡ በዚሁም አንድ ቀን ከእናቱና ከአባቱ ጋር ሆኖ ወደ ጤና ጣቢያው አምጥተው ሕይወቱን ያዳኑትን ሲስተር ተዋበችን አገናኝተውት ካስተዋወቁት በኋላ ሲስተሯ በመገረም ማመን አቃታቸው፡፡

ነገር ግን ልባቸው በደስታ ተሞላ። በዚሁም የልጁን የህክምና ምርመራ ከሚያደርጉ ሰራተኛ ጋር አገናኝተውት ጨርሶ መሄዱንና ቋሚ የመንግስት ሰራተኛ ለመሆን መብቃቱን ገልጸውልኛል፡፡ በዚህ መነሻ ነው “ለእኛ የሚጠቅመን የሚከፈለን ደመወዝ ሳይሆን ትልቁ እርካታ የሰውን ሕይወት ማዳን ነው” ሲሉ የተናገሩት፡፡

ለስራዎ ስላለዎት ፍቅር ቢገልጹልን ብለን ለጠየቅናቸው ጥያቄ ምላሽ ሲሰጡ “ለእኔ ስራ ማለት በደሜና በአጥንቴ ውስጥ የተዋሃደ ነው” ብለዋል፡፡ ነገር ግን ይህን ሁሉ አስተዋጽኦ አበርክተው ዕውቅና እና የሙያ ማሻሻያ ትምህርት ዕድል አግኝተው አለማወቃቸው በስራቸው ላይ አሉታዊ ተጽዕኖ እንደፈጠረባቸው ይናገራሉ፡፡

በዚህም መነሻ የሚወዱትንና ከደማቸው ጋር የተቀላቀለውን ስራ ለመቀየር ተገድደዋል። የሙያ ማሻሻያ የትምህር ዕድል ሲመጣ “እሷ ከሌለች የህክምና ማዕከሉ ይዘጋል” በሚል አድሎአዊ አስተሳሰብ ለውድድር አያቀርቧቸውም፡፡

ነገር ግን በአድሎ የትምህርት ዕድል ተሰጥቶአቸው ጤና ረዳት የነበሩት ሙሉ ነርስ፣ አሁን ተጨማሪ ዕድል ተሰጥኦቸው ከሙሉ ነርስነት ጤና መኮንን በመሆን በእሳቸው ላይ ሲሾሙ ሲያዩ ሞራላቸው መጎዳቱን ይናገራሉ፡፡

በመሆኑም በጣቢያው የትምህርት እድል ሲያጡ በሐዋሣ ዩኒቨርሲቲ በሳምንታዊ የትምህርት መርሃ ግብር በማህበራዊ ሳይንስ / በሶሺዮሎጂ/ ትምህርት በግላቸው ተምረው በመጀመሪያ ዲግሪ ተመርቀዋል፡፡

በዚሁም በሐዋሣ ዩኒቨርሲቲ በወንዶ ገነት ደን ኮሌጁ በስርዓተ ፆታ ባለሙያነት ተቀጥረው ለ4 ዓመታት ከሠሩ በኋላ በ2008 ዓ.ም የጡረታ መብታቸውን አስከብረዋል፡፡

ሲስተር ተዋበች በሥራ ወቅት አንድ ለህክምና አገልግሎት የሚረዳ መጽሐፍ ከአንዲት ጀርመናዊ ዜጋ መሸለማቸውን ተናግረዋል፡፡

መጽሃፉንም የተሸለሙት በነፍሰ ጡሮች ደም ማነስ ላይ ባለሙያዎችን በማወዳደር በሚያሠሩአቸው ተግባራት ተወዳድረው ላቅ ያለ ውጤት በማምጣታቸው ነበር፡፡

ሲስተር ተዋበች ወደ ትዳር ዓለም የገቡት በ1972 ዓ.ም ሲሆን 3 ወንዶችና አንድ ሴት በድምሩ የ4 ልጆች እናት ናቸው፡፡

ሶስቱ ወንዶች በአሜሪካን ሀገር የነፃ ትምህርት እድል አግኝተው በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቀው ሥራ ይዘው እዛው ሀገር ይኖራሉ። 4ኛው ሴት ልጃቸውም በማርኬቲንግ ማኔጅመንት በሁለተኛ ዲግሪ ተመርቃ በአዲስ አበባ በግል ድርጅት ተቀጥራ ትሠራለች፡፡

ሲስተር ተዋበች 4 የልጅ ልጆችን አይተዋል። አንዱ ከመጀመሪያ ወንድ ልጃቸው ሲሆን ሶስቱ ከሴት ልጃቸው የተወለዱ ናቸው ብለው ገልፀውልኛል፡፡