ጤፍን ከሰጋቱራ፣ በርበሬን ከሸክላ?

በኢያሱ ታዴዎስ

እኛ ኢትዮጵያዊያን ለበዓላት የተለየ ስፍራ አለን። “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” የሚለው ሀገርኛ ብሂልም ለየትኛውም በዓል የሚሰራ ነው። በዓል ከመጣ የትኛውም ዋጋ ተከፍሎ በልቶ፣ ጠጥቶ ተደስቶ ለማለፍ የማይፈነቀል ድንጋይ የለም። ማጀት ባዶ ቢሆን እንኳን ወደ ብድር ይገባል።

በዓል በባዶ ቤት አይታሰብም። ቄጠማ ካልተጎዘጎዘ፣ እጣኑ ካልጬሰ፣ ድፎው ካልተደፋ፣ የዶሮ ወጡ መዓዛ አካባቢውን ካላወደ፣ ምግቡ መጠጡ በብዛት ካልቀረበ በዓል በዓል አይደለም። ብቻ ለኢትዮጵያዊያን በዓል ብዙ ትርጉም አለው።

ለበዓል ዝግጅት የሚደረገውም ቀኑ ከመድረሱ አስቀድሞ ነው፡፡ ሽርጉድ ይበዛል። ገበያው ይደራል። ነጋዴው ሊነግድ የሸከፈውን ሁሉ ለገበያ ያውላል። ሸማቹም ባለው አቅም ለመሸመት ይጣደፋል። ለዚህ ነው የህዝቡን የበዓል ፍላጎት በመገንዘብ አንዳንድ ነጋዴዎች በራስ ወዳድነት ስሜት ተነድተው ትርፍ ለማግበስበስ ሲሉ ህገወጥ ድርጊት የሚፈጽሙት።

ህገ ወጥ ድርጊቱ ደግሞ ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ እስከመሸጥ ድረስ ጭካኔ የተሞላበት ነው። ይሄ ድርጊት በተለይ በዚህ ወቅት በእጅጉ ተንሰራፍቷል። አንዳንድ ነጋዴዎች ቅቤው ላይ ሙዝ፣ ቫዝሊን ወይም ሞራ እና ለጤና ተስማሚ ያልሆኑ ባዕድ ነገሮች ይቀላቅላሉ።

ጤፍን ደግሞ ከሰጋቱራ፣ አሊያም ከጀሶ ጋር ደባልቀው የሚሸጡም አሉ። በርበሬን ከሸክላ፣ ማርን ከስኳር፣ ስኳርን ከድንጋይ እና ሌሎች የእህል ምርቶችን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅለው የሚሸጡም በርካቶች ናቸው።

ይህ ግን በህጉ ፊት ፈጽሞ የተከለከለ ድርጊት ነው። በኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ጠባቂነት የወጣው የምግብ እና መድሃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 ዓ.ም. ይህን በተመለከተ ደንግጓል።

በዚሁ አዋጅ አንቀጽ 67 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ፡-

“ማንኛውም ደረጃውን ያልጠበቀ ምርት አስመስሎ በማምረት ያከማቸ፣ በጅምላ ያከፋፈለ ወይም በችርቻሮ የሸጠ፣ አሊያም በማንኛውም መንገድ ለህብረተሰቡ ለአገልግሎት ያቀረበ፣ እንዲሰራጭ ያደረገ እንደሆነ ሶስት ዓመት በማይበልጥ ቀላል እስራት እና ከሁለት መቶ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል” ይላል።

በዚሁ አንቀጽ እንደተደነገገው የምርቱ የደረጃ ጉድለት በሰው ጤና ወይም ህይወት ላይ ጉዳት ሊያስከትል የሚችል ከሆነ ከሰባት ዓመት በማይበልጥ ፅኑ እስራትና ከአምስት መቶ ሺህ ብር በማይበልጥ መቀጮ ይቀጣል።

አንቀጽ 67 ንዑስ አንቀጽ 2 (ሀ) ደግሞ ከላይ በተገለጸው ድርጊት ምክንያት በሰው አካል ወይም ጤና ላይ ጉዳት ከደረሰ ከሰባት ዓመት እስከ አስራ አምስት ዓመት ፅኑ እስራት እና ከሀያ ሺህ እስከ ሶስት መቶ ሺህ ብር መቀጮ ይቀጣል ይላል።

አንቀጽ 67 ንዑስ አንቀጽ 2 (ለ) ህገወጥ ድርጊቱ በሰው ላይ ሞት ያስከተለ እንደሆነ ከአስር ዓመት እስከ ሃያ ዓመት ፅኑ እስራት እና ከሰላሳ ሺህ እስከ አራት መቶ ሺህ ብር መቀጮ እንደሚያስቀጣ ያትታል።

ህጉ በዚህን ያህል ደረጃ እርምጃ እንዲወሰድ ቢያዝም ምግብን ከባዕድ ነገር ጋር ቀላቅሎ የሚሸጠው ነጋዴ በሚመለከተው አካል ቁጥጥር ስለማይደረግበት ብዙ ጊዜ በስውር ስራውን ይሰራል። አብዛኛውን ጊዜ በጥቆማ ለህግ አሳልፎ የሚሰጠውም ከህጋዊ አካል ይልቅ ህብረተሰቡ ነው።

ህጉ ግን በዋነኛነት ኃላፊነቱን እንዲወጣ የሚጠይቀው የሚመለከተውን ህጋዊ አካል ነው። በዚሁ የምግብ እና የመድሃኒት አስተዳደር አዋጅ ቁጥር 1112/2011 ዓ.ም አንቀጽ 63 ንዑስ አንቀጽ 8 ላይ፦

“ተከልሷል፣ በማስመሰል ተሰርቷል፣ ህገወጥ ነው ወይም ለህብረተሰቡ ጤና አደገኛ ነው ሊያስብል የሚችል አሳማኝ ምክንያት ሲኖር ማንኛውም ምርት በአስፈጻሚው አካል ወይም የክልሉ ጤና ተቆጣጣሪ የላቦራቶሪ ምርመራ ማድረግ አስፈላጊ ከሆነ ምርመራው እንዲካሄድበት ማዘዝ እና ውጤቱ እስኪታወቅ ድረስ ለተወሰነ ጊዜ እንዲያዝ ወይም እንዲታገድ የማዘዝ ኃላፊነት አለበት” ይላል።

በተጨማሪም አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ 6 ላይ ማንኛውም ምርት በመከለሱ ምክንያት ሞት፣ ህመም፣ የአካል ጉዳት፣ የጤና መታወክ ወይም ሌላ የጤና ችግር ያስከተለ ምርትን ወይም ይዘትን የሚመለከተው ህጋዊ አካል እንደሚለይ፣ በናሙናው ላይ ጥናት እንደሚያደርግ፣ እና ውጤቱን መሰረት በማድረግ አስፈላጊውን ህጋዊ እርምጃ እንደሚወስድ ይደነግጋል።

አንቀጽ 4 ንዑስ አንቀጽ 9 ደግሞ የምግብ ደህንነት ወይም ጥራትን ለመቆጣጠር የህግ አካሉ የድህረ ገበያ ቅኝት እንዲካሄድ ሊያዝ ወይም ሊያካሂድ እንደሚችል ያትታል።

ታዲያ እነዚህ ለህግ አካል የተደነገጉ አዋጆች የምግብ ምርቶች ከባዕድ ነገር ጋር እንዳይደባለቁ ቅድመ ጥንቃቄ እንዲደረግ ያስችላሉ። ህብረተሰቡም በመሰል ህገወጥ ድርጊት እንዳይታለል ይረዳል። ስለሆነም ህገወጥ ድርጊቱ በህብረተሰቡ እና በህግ አካላት በጋራ ትብብር ሊቀረፍ የሚችል ነው።

በበዓላት ወቅት የሚፈጸሙ ህገ ወጥ ድርጊቶች እነዚህ ብቻ አይደሉም። መንገዶች በሰዎችና በተሽከርካሪዎች ይሞላሉ። ነገር ግን አንዳንድ የመኪና አሽከርካሪዎች ለእግረኛ ቅድሚያ ባለመስጠትና በጎዳናዎች ላይ በቸልተኝነት በማሽከርከር በሰውና በንብረት ላይ አደጋ ሲያደርሱ ይስተዋላሉ።

ታዲያ በዚህ ወቅት በእግረኞችም በኩል በሚፈጸም ቸልተኝነት አደጋ ሊከሰት ይችላል፡፡ ይህም ብቻ ሳይሆን እግረኞች ለተሽከርካሪዎች በተፈቀደ መንገድ ላይ መቆም ወይም መጓዝ፣ ባልተፈቀደ መንገድ ላይ ማቋረጥ ለአደጋ ከሚያጋልጡ ምክንያቶች መካከል ይጠቀሳሉ፡፡ ለዚህም የመንገድ ትራንስፖርት መቆጣጠሪያ ህጉ አሽከርካሪውንና እግረኛውን ተጠያቂ ያደርጋል፡፡

የሚንስትሮች ምክር ቤት ያወጣው የመንገድ ትራንስፖርት ትራፊክ መቆጣጠሪያ ደንብ 395/2009 መሰረት ተገቢውን ጥንቃቄ ሳያደርግ መንገድ ያቋረጠ፣ ለተሽከርካሪ በተፈቀደ መንገድ ላይ ያለ በቂ ምክንያት የቆመ ወይም የተጓዘ፣ የእግረኛ መንገድ በሌለበት መንገድ ላይ ቀኝ ጠርዙን ይዞ የተጓዘ፣ እንዲሁም ለእግረኛ ከተከለለ መንገድ ውጪ የተጓዘ እግረኛ 40 ብር እንደሚቀጣ ያስቀምጣል፡፡

እግረኞች የሚቀጡት ቅጣት ቢቀልም በዋነኛነት ቅጣቱ የተቀመጠው ህብረተሰቡን ለማስተማር ስለመሆኑ መገመት አያዳግትም፡፡

ከዚሁ በተጓዳኝ በበዓላት ወቅት የተለመደው ጠጥቶ ማሽከርከር ነው። የመንገድ ደህንነት ትራፊክ መቆጣጠሪያ የጥፋት ዝርዝር ደረጃና የቅጣት መጠን ደንብ ቁጥር 395/2009 የተሻሻለው ላይ ማንኛውም ጠጥቶ ያሽከረከረ 300 ብር ቅጣት እንደሚጣልበት ደንግጓል፡፡

ከዚህ ባሻገር ማንኛውም አሽከርካሪ በፍጥነት በማሽከርከር፣ ወይም ህግ በመጣስ የሰው ሕይወት ማጥፋት አደጋ አድርሶ እንደሆነ ለአንድ ዓመት የአሽከርካሪ ማረጋገጫ ፈቃዱ (መንጃ ፈቃዱ) ይታገዳል፡ ፡ ከባድ የአካል ጉዳት ካደረሰ ደግሞ ለ6 ወር የአሽከርካሪ ማረጋገጫ ፈቃዱ ይታገዳል፡፡

ማንኛውንም ዓይነት ጥፋት በመፈጸም በሰው አካል ላይ ቀላል ጉዳት ያደረሰ አሽከርካሪ በህግ የሚያስጠይቀው እንዳለ ሆኖ 300 ብር እንደሚቀጣ ይደነግጋል፡ ፡ አሽከርካሪው ካለፈው ጥፋቱ ሳይማር ተደጋጋሚ መሰል ጥፋት የሚያደርስ ከሆነ ደግሞ የአሽከርካሪ ማረጋገጫ ፈቃዱ ይታገድና ከአንድ ዓመት በኋላ በባለስልጣኑ የሚሰጠውን የተሃድሶ ስልጠና እንዲወስድ እንደሚደረግ ይደነግጋል፡፡

ታዲያ እነዚህ የህግ ድንጋጌዎች ህብረተሰቡ ከማንኛውም ህገወጥ ተግባር ነጻ እንዲሆን የተደነገጉ ናቸው፡፡

ይሁን እንጂ ህገወጥ ድርጊቶቹ አሁንም መፈጸማቸው አልቀረም፡፡ ስለሆነም ወቅቱ አሮጌውን ሸኝተን አዲሱን ዓመት የምንቀበልበት ነውና ከየትኛውም ህገወጥ ድርጊቶች ራሳችንን ጠብቀን እንድንንቀሳቀስ ከምን ጊዜውም በላይ ኃላፊነታችንን ልንወጣ ይገባል፡፡