የንጋት እንግዳችን አቶ ብርሃኑ አየለ ይባላሉ፡፡ በሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ በተለያዩ ኃላፊነት ቦታዎችና በመምህርነት ለ37 ዓመታት አገልግለዋል፡፡ በአዲሱ ዓመት በሀገሪቱ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን ከመንግስት እና ከህዝብም ምን ይጠበቃል? በሚሉ እና ሌሎች ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
በገነት ደጉ
ንጋት፡- በቅድሚያ የንጋት እንግዳ ለመሆን ፈቃደኛ ስለሆኑ በጋዜጣው ዝግጅት ክፍል ስም ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ብርሃኑ፡- እኔም እድሉ ስለተሰጠኝ ከልብ አመሰግናለሁ፡፡
ንጋት፡- ትውልድ እና እድገትዎን ያስተዋውቁን?
አቶ ብርሃኑ፡- ተወልጄ ያደኩት በ1956 ዓ.ም በቀድሞው ከፋ ክፍለ ሀገር ከፋ አውራጃ በጊንቦ ወረዳ ልዩ ስሙ ጋዋ ገርባ ቀበሌ ገበሬ ማህበር ውስጥ ነው፡፡
የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቴን ጊንቦ 1ኛ እና መለስተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ተምሬ የ2ኛ ደረጃ ትምህርቴን ደግሞ ቦንጋ ሸታ ከፍተኛ 2ኛ ደረጃ ትምህር ቤት ብሻ ወልደ ዮሐንስ ተብሎ በሚጠራው ትምህርት ቤት አጠናቅቄአለሁ፡፡
በወቅቱ ጥሩ ውጤት በማምጣት በባህርዳር መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ከ1975 እስከ 1978 ዓ.ም ተምሬ የመጀመሪያ ድግሪዬን በፔዳጎጂ (የማስተማር ስነ-ዘዴ) የትምህርት ክፍል ተመርቄአለሁ፡፡
በቀድሞው ሲዳሞ ክፍለ ሀገር ተመድቤ ያቤሎ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሁለት ዓመታት አገልግያለሁ፡፡
ከሁለት ዓመት ቆይታ በኋላ አለታ ወንዶ ከፍተኛ ሁለተኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ለሁለት ወር አገልግዬ በዝውውር ሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ የቀድሞው ሀዋሳ መምህራን ትምህርት ተቋም ከ1981 ዓ.ም ጀምሮ ለአራት ዓመታት ያህል በጂኦግራፊ የትምህርት ክፍል ካስተማርኩ በኋላ ከ1985 እስከ 1988ዓ.ም በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የሁለተኛ ድግሪ ለአራት ተከታታይ ዓመታት በመከታተል በስነ-ልቦና የትምህርት ክፍል ተመርቄያለሁ፡፡
ብዙ ጊዜያትን የቆየሁት በአስተዳደር ስራዎች ነው፡፡ የደቡብ ብሔር ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል ከመባሉ በፊት በትምህርት ቢሮ ውስጥ የትምህርት በሬድዮ እና የትምህርት መሳሪያዎች ክፍል ኃላፊ በመሆን ሰርቻለሁ።
በሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ 4 ዓመት በዲንነት ወደ 12 ዓመት ደግሞ በተማሪዎች ዲንነት (አካዳሚክ ዲን) በመሆን በታታሪነት እና በታማኝነት አገልግያለሁ፡፡
የሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ሲከፈት ከመምህራን ማሰልጠኛነት ወደ መምህራን ትምህርት ኮሌጅነት ካደጉት መካካል አንዱ ነበር፡፡
በወቅቱ የመምህራን ኮሌጅ የነበረው ኮተቤ ብቻ ነበር፡፡ ከሁሉም አካባቢ አዲስ አበባ በመሄድ ነበር ዲፕሎማቸውን መምህራኖች የሚማሩት፡፡
በ1988 ዓ.ም ሙሉ እውቅና አግኝቶ ከመምህራን ማሰልጠኛነት ወደ መምህራን ትምህርት ኮሌጅነት በክረምት መርሃ ግብር ለመጀመሪያ ጊዜ የመማር ማስተማሩን ስራ ጀመረ፡፡
በመምህርነት፣ በአስተዳደር ስራዎችና በትምህርት ቢሮ ውስጥ በኃላፊነት ለ37 ዓመታት ያህል ሳገለግል 35ቱን ዓመት በሀዋሳ መምህራን ትምህርት ኮሌጅ ብቻ ነበር ያገለገልኩት፡፡
ንጋት፡- በአዲስ ዓመት አዲስ ነገር ለመስራት ምን መደረግ አለበት?
አቶ ብርሃኑ፡- አዲስ ዓመት እሳቤ ነው። አዲስ ዓመት ይመጣል ብለን እንደሰታለን። አዲስ ዓመት በአልባሌ እንዳያልፍ ማቀድን ይጠይቃል፡፡ እያንዳንዱ ግለሰብ፣ ድርጅት፣ በማህበርና በመንግስት ደረጃ ታቅዶ ስራዎች የሚከወኑበት ጊዜ ነው፡፡
ይህም እቅድ በሀሳብ ደረጃ ሊሆን ይችላል። ነገር ግን በወረቀት ቢሆን የተሻለ ነው፡፡ ሀሳብ እንዳይዋልል እና ሰዎች ለሚሰሩት ነገር ልጓም እንዲኖራቸው ማለት ነው፡፡ እቅዶችም በጊዜ እና በበጀት ተደግፈው ሊታቀዱና ዓላማ እና ግብ ሊኖራቸውም ግድ ይላል፡፡
በምንሄድበት መንገድ እንቅፋቶች ይኖራሉ፡፡ እነዚህን እንቅፋቶች እንዴትም ተሻግረን ግባችንን መጨበጥ አለብን የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ይህም ሁሉ ኖሮ ከባቢ የምንለው ደግሞ መኖር ወሳኝ ነው፡፡ ከባቢ ከሌለ እቅዳችንን ማሳካት አንችልምና፡፡
ንጋት፡- አምና የነበሩ ችግሮችን ቀርፈን በ2016 ዓ.ም እንደ ሀገር ምን መሰራት አለበት ይላሉ?
አቶ ብርሃኑ፡- ከስነ-ልቦናው ወጣ በማለት ጂኦግራፊንም እንዳስተማረ ሰው የእኛ ሀገር ችግር እንደ ተአምር እናያለን እንጂ ነባር ችግር ነው፡፡
ችግራችን የነበረ ነው፡፡ በዚህም 5 እና 6 ዓመታት የመጣ አይደለም ብሎ መደምደም ይቻላል፡፡
ከአክሱም ዘመነ መንግስት ጀምሮ ረሀብ፣ ጦርነት፣ በሽታ፣ መፈናቀል፣ የኑሮ ውድነትና ልምላሜም መስፋት መጥበብም ነበረ፡፡ በተለያየ ማዕቀፍ ካላየን ውስን ያደርገናል፡፡ እና ችግሮች ነበሩ፡፡ ትልቁ ችግራችን የሰላም እጦት ነበር፡፡
የተለያዩ ችግሮች የሚነሱት ከሰላም እጦት ነው፡፡ ማንኛውም ችግር መነሻው ከሰላም እጦት የሚነሳ ነው፡፡
በእኛ ሀገር ከወታደር ሲቀጥል ያልተመቸው ገበሬ ነው፡፡ ይህንንም ገበሬ አፈናቅለን ኑሮ ውድ ነው ስንል ሊከብደን አይገባም ወይ?
አርሶ ህዝብን የሚያበላ ገበሬን አባረንና አፈናቅለን ለእሱ ደግሞ ለምጽዋት ስንጨነቅ ኑሮ ባይወደድ ይገርማል፡፡
ሌላው በሀገራችን ስንት ሰው ነው የሚሰራው? ሁሉም ሰው መስራት አለበት የሚል እሳቤ አለኝ፡፡
የዓለም ባንክ በቅርብ ጊዜ ባወጣው መረጃ ያየሁት በሀገራችን 127 ሚሊየን ህዝብ እንዳለ ያትታል፡፡ ታዲያ ከዚህም ውስጥ ስንቱ ነው የሚሰራው? ስንል ማንኛውንም ስራ ማለት ነው፡፡
ለስራ አቅም ያለው ማንኛውም ሰው መስራት አለበት፡፡ ሁሉም ሰው በማይሰራበት ሀገር ተቀምጠን ኑሮ ውድ ነው ማለት ከባድ ነው፡፡
በአዲሱ ዓመት ፈጣሪ ልቦናችንን መልሶ ሀገራችን ሰላም ከሆነች የተመቻቸ ነገር ሊኖር ይችላል፡፡ ነገር ግን ሰው እየተታኮሰ እና እየተረባበሸ ህዝብ መረጋጋት አይችልም፡፡ ሰላም ካለ ሁሉም ነገር አለ፡፡ ሰላም ከሌለ ግን ምንም ነገር ሊኖር አይችልም፡፡
በአሁኑ ጊዜ ዓለም በተጠላለፈ መረብ ውስጥ ነው ያለው፡፡ የአንዱ ሰላም ማጣት ሌላውን ሰው በአንድና በሌላ መንገድ ያናጋል።
አሁን በሀገራችን ብቻ ሳይሆን በሁሉም ዓለማት የሚሆነው ነገር እየጎዳን እና ኑሮአችንን እያናጋ ነው፡፡ ሰዎች ብርቅዬ ፍጡራን ናቸው፡፡ ሰዎችን ሳይሆን ሀሳባቸውን ነው መጥላት ያለብን፡፡
በሀገራችን ያለው ጦርነት ብቻ ሳይሆን በተለያዩ ዓለማት ውስጥ ያለው ጦርነት ነው የጎዳን፡፡ ሰላም ለምን አጣን? ባለፍናቸው ሁሉ ያለፉትን ነገስታት ጠንካራ ነገራቸውን ትተን ስንኮንናቸው እንታያለን፡፡
ቀዳማዊ ሀይለስላሴ ለ40 ዓመታት መርተዋል፡፡ እርሱንም መጥፎ ብለን ነው የመጣነው፡፡
በዚህ አምስት ዓመታት ግን ብዙ መከራ ደርሶብናል፡፡ ይህም መከራ ለምን መጣ ብለን ቆም ብለን እንመልከት? ሁል ጊዜ ከመንግስት ነው ብለን እንወነጅላለን፡፡ እኔ እና እናንተ አልተሳተፍንበትም ወይ? ህዝቡ አላጨበጨም፤ አልደገፈም ወይ?
ሰዎች ባሉበት ደጋፊም ተቃዋሚም ይኖራል፡፡ ይህም ኖርማል ነው፡፡ ተፈጥሮአዊም ነው፡፡ ስለዚህ እያንዳንዳችን እራሳችንን መፈተሸ አለብን፡፡
ንጋት፡- በሀገራችን ሰላም እንዲመጣ መንግስትም ህዝብም ምን መስራት አለበት?
አቶ ብርሃኑ፡- እቅዳችን እንዲሳካና 2016 ጥሩ ዓመት እንዲሆን ከፈለግን እያንዳንዱ ግለሰብ እራሱን መፈተሽ አለበት፡፡
ሁሉም ተሳስሮ እና ተሳስቦ ነው እንጀራ በልተን የምናድረው፡፡ ለሰላሙ የእኔ አስተዋጽኦ አለ ወይ? ብሎ ከምን ጊዜውም በላይ እራስን ቆም ብለን ማየትና መፈተሸ አለብን፡፡
በእኛ ባህል የገደለ ጀግና ነው፡፡ በእኔ እሳቤ የገደለ ጀግና አይደለም፡፡ ባይሆን ያዳነ ነው ጀግና የሚል ጽኑ እምነት አለኝ፡፡ ብርቅዬን ፍጡር መኖርን እየጓጓ መግደል ግፍ ነው፡፡ አሁን ላይ የሰፋ አዕምሮና ቴክኖሎጂ ባለበት የድሮን እያሰብን ያለ መርህ ነው የምንጓዘው፡፡ ሰላም እንዲኖር ሁሉም ሰው ፈርሃ እግዚአብሔር በውስጡ መኖር አለበት የሚል እምነት አለኝ፡፡
ሀገርን ፈልገን አይደለም ያገኘነው፡፡ በሀገራችን በየቦታው የሀሳብ ውስንነት አለ፡፡ ይህንን አስወግደን ጠንክረን መስራት አለብን።
ንጋት፡- በእርስዎ እሳቤ የዘንድሮውን አዲስ ዓመት እንዴት ማክበር አለብን?
አቶ ብርሃኑ፡- በስነ-ልቦና ተመራማሪዎች መካከል አንድ አሜሪካዊ ቢኤፍ እስኪነር በማንኛውም ነፍስ ያለ ነገር መኖር ይፈልጋል ይላል፡፡ ለመኖር የሚመቸውን ይመርጣል። ሰው ቤቱን ዘግቶ በዓልን የሚውለው ስጋት አለው፡፡ ዛሬ ላይ ሰው ጥላውን የማያምንበት ዘመን ላይ ደርሰናል፡፡
ሌላው ዘመን ያመጣው ድህነት አለ፡፡ ኑሮ እንደ ድሮ አይደለም፡፡ ውድ ነው፡፡ ሰው ለራሱ መኖር ያልቻለበት ጊዜ ቢኖር አሁን ነው፡፡
ሌላው በእናቶቻችንና በአባቶቻችን ትናንት አንዱ ቤት ባይኖር ከሌላው ቤት ተበልቶ ይታደራል፡፡ አሁን ላይ ይህ የለም፡፡ ሰው ተጨካክኗል፡፡ ይህም በሀብት እጥረትና ግለኝነት ጎልቶ ይታያል፡፡
ዓለም ውድድር ላይ ስለሆነ ነገ እኔ እወድቃለሁ ብሎ ስለሚያስብ እራሱ ገንዘቡን በባንክ አጠራቅሞ ውድድር ውስጥ መግባት ይፈልጋል እንጂ ቢኖረውም የመስጠትና የመሰጠት ባህላችን ተሸርሽሯል፡፡ ተግባሩ በዘመናዊነት ለበጎ አድራጎት በመስጠት የእድገት ደረጃውንም ቀይሯል፡፡
ንጋት፡- ወጣቶች ለሀገር ምን መሰራት አለባቸው ይላሉ?
አቶ ብርሃኑ፡- እኛ ወጣቶችን እንወቅሳለን እንጂ አሁን ላይ የሚገርሙ ወጣቶች መጥተዋል፡፡ ተአምር ሊሰሩ የሚችሉ ወጣቶች ናቸው የመጡት፡፡ ጭቆና እና ጫናን የማይፈልጉ፣ ፈጣን አዕምሮ ያላቸው ወጣቶች ናቸው በገጠርም በከተማም የተፈጠሩት፡፡
ነገር ግን እነዚህ ወጣቶችን የሚመጥን ድጋፍ አልመጣም፡፡ የነገ ሀገር ተረካቢ ስለሆኑ ነገሮችን መመርመር አለባቸው፡፡ በስነ- ልቦና ውስጥ እውቀት፣ ስሜትና ተግባር ወይም ክህሎት የተነጣጠሉ አይደሉም ይላል፡፡ ነገር ግን ስሜት ግለኛ ነው፡፡ ቶሎ ይጋሽብና ብዙ ጥፋቶችን ሊያጠፋ ይችላል፡፡ በዚህም እውቀት ካልቀደመ ስሜት ከቀደመ በጣም አደገኛ ነው፡፡
በዚህም ወጣቱ ስሜቱን ተቆጣጥሮ በየጊዜው እውቀት ማግኘት አለበት፡፡ አንዳንድ ጊዜ ትልቅ ችግር ተፈጥሮ ደንግጠን ስንወጣ ችግር የለውም ቀላል ነው በማለት ሰዎችን ያረጋጋሉ፡፡ ይህም ጉብዝናና የእድገት ደረጃ ነው፡፡
በአሁኑ ሰዓት አብዛኛው ወጣት በጥሩ አካሄድ ላይ ነው፡፡ ጥቂቱ ነው በሰው እና በመንግስት ትከሻ ላይ ያለው ብሎ መናገር ይቻላል፡፡ በሀገር ጉዳይ ላይ ተሳትፎአቸውን በማሳደግ ሀገርን ከችግር ማውጣት ይጠበቅባቸዋል፡፡
ንጋት፡- አብሮነታችን ሳይሸረሸር በዓልን እንዴት እናክብር?
አቶ ብርሃኑ፡- ይህንንም በሁለት ጎን ነው የማየው፡፡ አቅመ ደካሞች ጠዋሪ ያጡት እና መስራት እየቻለ ገንዘብ አምጣ የሚሉ፣ አምጣ ብለው የሚወስዱ አሉ፡፡ አሁን ላይ ያሉ የጎዳና ልጆች ያስፈራሉ፡፡ ለማኝ ይበዛል፡፡ ከዛሬ 10 እና 15 ዓመት በኋላ ከተማው ምን ይሆናል የሚለው ስጋት አለኝ፡፡
ሰዎች ከስራ ባህላቸው ርቀዋል፤ መስራትም አይፈልጉም፡፡ በዚህም ላይ መንግስት መስራት አለበት፡፡ መርዳት ያለብን ሽማግሌዎች የደከሙ እና ወደ ቤት የተመለሱትን ዘመድና ጠዋሪ ቀባሪ ያጡትን አብረን በመረዳዳትና ማዕድ በማጋራት ማሳለፍ አለብን እላለሁ፡፡
ንጋት፡- በሀገራችን እየጐላ የመጣውን አጓጉል የምዕራባዊያንን ባህልና አስተሳሰብ እንዴት እንቅረፍ?
አቶ ብርሃኑ፡- የምዕራባዊያን እሳቤ ጥሩም መጥፎም ስላለ ሊጎዳን የሚችለውን በመተው ጠቃሚ የሆኑትን መውሰድ ግድ ይላል፡፡ ሁሉም መጥፎ ብለን ግን መደምደም የለብንም፡፡
በተለይም ፀያፍ የሆኑትን እንደ ግብረሰዶም የመሳሰሉትን የሀይማኖት አባቶች ተግተው እየሰሩ ነው፡፡ ሰዎች ባለማወቅ ነው የሚገቡት፡፡ በተለይም ሀሺሽ፣ ግብረ ሰዶማዊነት፣ ቦዘኔነትና ዋልጌነት የተያያዙ ናቸው፡፡ አንዴ መረቡ ውስጥ ካስገቡ በኋላ ከመረቡ መውጣት ከባድ ነው፡፡ እዛ ከገባ ዜጋው ከሰረ ማለት ነው፡፡ መልሶ ለመውጣት ጊዜ ይፈልጋል፡፡
ንጋት፡- የሚያስተላልፉት መልዕክት ካልዎት?
አቶ ብርሃኑ፡- የማስተላልፈው መልዕክት ፈርሃ እግዚአብሔር በልባችን ይኑር፡፡ ፈርሃ እግዚአብሔር የሌለው ሰው ከአራዊት የተለየ አይደለም፡፡ ሁላችንም ወደ ልቦናችን እንመለስ፡፡ አስተሳሰባችንን እንቀይር። ስለዚህ ጦርነትን የሚቀሰቅሱ ነገሮችን በመተው ፍትህ ስርዓት መጠናከር አለበት። ወንጀል የሰራ ሰው በህግ መጠየቅ አለበት፡፡
ለኢትዮጵያ ህዝብ መነጋገር ከምንም በላይ ዕድል ይሰጣልም፡፡ እየመረረንም መወያየትን መማር አለብን የሰው ጠላት የለም፡፡ የሀሳብ እንጂ፡፡
በመጨረሻም ለመላው የኢትዮጵያ ህዝብ መልካም በዓልን እመኛለው፡፡ ሀገራችን ሰላሟ ይብዛ በማለት መልዕክቴን እቋጫለሁ፡፡
ንጋት፡- በድጋሚ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ብርሃኑ፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡
More Stories
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው
“የችግር ቀናቶቼን አልረሳቸውም” – ወጣት አያኖ ብርሃኑ