የጳጉሜ ኃይማኖታዊና ሳይንሳዊ ትርጓሚዎች

በገነት ደጉ

ጳጉሜ በነሐሴ እና በመስከረም ወራት መካከል የሚገኝ ጊዜ ነው፡፡ ከአስራ ሶስቱ የኢትዮጵያ ወራት መካከል የመጨረሻው ነው።

ወሩ አምስት ቀናት ሲኖሩት በአራት ዓመት አንድ ጊዜ 6 ይሆናል። የአዲስ ዓመት መቀበያና የአሮጌው ዓመት መገባደጃ የሆነ አጭር ወር፡፡

እኛም ጳጉሜ ወር አቆጣጠር ምን ይመስላል? ከሌሎቹ ወራት ለየት የሚያደርገው ምክንያትስ ምንድነው? በሚሉና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከመንፈሳዊ አባቶችና ከተመራማሪዎች ጋር ያደረግነውን ቆይታ እንደሚከተለው አቅርበናል፡፡

በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የሀዋሳ ደብረ ኢየሱስ ባለወልድ ቤተ-ክርስቲያን አስተዳዳሪ መጋቢ ምስጢር ኢሳያስ ገብረመድህን፣ ጳጉሜ መሸጋገሪያ ወይም መግቢያ የሚል ስያሜ እንዳለው እና ከኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ጋር ትልቅ ቁርኝት እንዳለው ነው የገለፁልን፡፡

ከ12ቱ የዓመቱ ወራት የተቀናነሱ ደቂቃዎች እና ሰዓታት ተደምረው 13ኛ ወር ጳጉሜ የሚል ስያሜ እንደተሰጠም ነው የሚናገሩት።

ኢትዮጵያ በአለም ብቸኛዋ የ13 ወራት ባለቤት መሆኗን የሚያነሱት አስተዳዳሪው ይህ ወር በኢትዮጵያውያን ዘንድ የምህረት ወር ተብሎ እንደሚታመን ጠቁመዋል፡፡ ለዚህም ነው ወደ አዲስ ዓመት መግቢያና አሮጌውን የምንተውበት (መሸጋገርያ) በማለት የሚጠራው ሲሉ ያስረዳሉ።

ጳጉሜ “ተረፈ ወር” ወይም ”ተረፈ ዓመት” ተብሎ በእምነቱ ተከታዮች ዘንድ የሚታወቅ መሆኑን የሚናገሩት መጋቢው አሮጌው ዓመት አልቆ አዲሱ ዓመት የሚገባበት ነው ብለዋል፡፡ በአራት ዓመታት አንዴ ስድስት ቀን እና በ600 ዓመት አንዴ 7 ቀን እንደሚሆንም በመግለጽ፡፡

ከእያንዳንዱ ዓመታት የሚተርፉ ሰዓታት መኖራቸውን የሚናገሩት መጋቢ ምስጢር ከዘመን እየተረፉ የመጡ ቀናት ጳጉሜ እንደሚሆኑ ነው የሚያስረዱት፡፡

ጳጉሜ በ600 ዓመታት ደግሞ ሰባት እንደሚሆን የሚናገሩት መጋቢው በዘንድሮ ዓመት ጳጉሜ ስድስት ሆኖ እንደሚውል ገልፀዋል፡፡ ከዚህ ቀደም ደቂቃ ሰከንድ የሚባሉት ባልነበሩ ጊዜም የቤተክርስቲያኑ አቆጣጠር እንደነበር አስታውሰው ይህም ከተጀመረ 200 ዓመታት ማለፉን ነው የተናገሩት፡፡

በኢትዮጵያዊያ አቆጣጠር 1ሺህ 800 ያህል ዘመናትን እንዳስቆጠረ የሚናገሩት አስተዳዳሪው ከሰከንድና ማይክሮ ሰከንድ ጀምሮ እንደሚቆጠር ነው የገለፁት፡፡

አምስቱ ቀናት እራሳቸው ተረፈ ዓመት እንደሆኑ የሚናገሩት አስተዳዳሪው ከሰዓት ሽርፍራፊ ተጠራቅመው በዓመት የሚመጡ ናቸው ብለዋል፡፡ ሌላ ወራት ግን እንዳልሆኑና ከነበሩ ወራት የተረፉ መሆናቸውን በመግለጽ፡፡

በቤተክርስቲያኗ አቆጣጠር ስልሳ ሳድሲት አንድ ሃምስት፣ ስልሳ ሃምሲት አንድ ራብዒ፣ ስልሳ ራብዒ አንድ ሳልስት እንዲሁም ስልሳ ሳልሲት ደግሞ አንድ ኬክሮስ እንደምትወልድም ነው ያብራሩት፡፡

እነዚህ ሽርፍራፊዎች ተጠረቃቅመው ሰዓት ወይም ቀንን ሲፈጥሩ የእነዚህ ትራፊዎች ጳጉሜን እንደሚወልዱ ነው መጋቢው ምስጥር ኢሳያስ የገለፁልን፡፡

በዚህ ጳጉሜ የዓመቱ መጨረሻ መሆኑን ተናግርው በተለያዩ አባቶች ዘንድም መግቢያ፣ መካተቻ ወይም መገባደጃ የሚል ስያሜ እንዳለው ነው ያስረዱት፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የአንትሮ ፖሎጂ እና ማህበራዊ ሳይንስ መምህርና ተመራማሪ ዶክተር ሳሙኤል ጂሎ በበኩላቸው በፈረንጆቹ አቆጣጠር ወራቶች 28፣ 29 እና 31 የሚሆኑበት አጋጣሚ እንዳለ፣ የእኛ ሁሉም ወራት ግን 30 ቀናት ብቻ እንዳላቸው ጠቁመዋል፡፡ በዓመት ያሉ ቀናትም 365 ወይም 365 ተኩል ይሆናሉ ብለዋል፡፡ አንዳንድ ጊዜ ሽርፍራፊ እና ትርፍ ቀናቶች እንደሚፈጠሩ በማመልከት፡፡

እነዚህ ሽርፍራፊዎች ከፀሐና ጨረቃ እንቅስቃሴ ጋር የሚሄዱና 30 ያላቸው 12 ወራት ሲሆኑ ቀሪዎች ሽርፍራፊዎች ተጠራቅመው አምስት ወይም ስድስት ቀናት ይሆናሉ ብለዋል፡፡

በሳይንሳዊ አቆጣጠር የኢትዮጵያ የፀሐይን እንቅስቃሴ የሚከተል ሲሆን ይህም ሶላር ካሌንደር የሚባል ስያሜ እንዳለው ነው የገለፁት፡፡

ጳጉሜ ኢትዮጵያን የ13 ወር ፀጋ ያላት ሀገር እንዳሰኛት የሚናገሩት ዶክተር ሳሙኤል የሀገር በቀል እውቀት ያለው ፋይዳ የጎላ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

የዘመን አቆጣጠር በሀገራችን ሀይማኖታዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳው ትልቅ ነው ያሉት ዶክተር ሳሙኤል የኢትዮጵያ አቆጣጠር እራሱ ጥበብም እውቀትም ነው በማለት ነው የተናሩት፡፡

በሀገራችን ወራቶች ሳይዛነፉ የሚቆጠሩ ሲሆን የሚናገሩት ባለሙያው በተለይም ከኦርቶዶክስ ሀይማኖት ጋር ተያይዞ ያለው ፋይዳው ከአጿማት ጋር ያለው ቁርኝት ቀላል የሚባል አይደለም ይላሉ፡፡

ብዙ ሀገሮች ካላንደር ቢኖራቸውም ከኢኮኖሚው እና ከሀይማኖት ጋር አቆራኝተው እንደማይመሩ ነው ዶክተር ሳሙኤል የሚናገሩት፡፡ ይህም ኢትዮጵያን ለየት እንደሚያደርጋት ያስረዳሉ፡፡

በመንፈሳዊ አባቶች የተሰላው ስሌት ሳይንሳዊ መሰረት እንዳለው የሚያምኑት ዶክተሩ መነሻ ከፀሐይ እንቅስቃሴ ጋር እንደሚያያዝ ጠቁመዋል፡፡

የሀይማኖት አባቶች ሳይንሳዊ ይዘቱን ሳይለቅ ሀይማኖቱንና ባህሉን አጣጥመው እንደሚቆጥሩና ለዚህም ጥሩ ማሳያ ሊሆን የሚችለው ከፀሐይ እንቅስቃሴ ጋር መቆራኘቱ እንደሆነ ተናግረዋል፡፡

በሀገራችን ሰርተን ክፍያ የምናገኝበት የስራ ወራት 12 በመሆናቸው 13ኛዋ ወር ትባል እንጂ በማንኛውም ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊ እና ፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎች ክፍያ የለውም ብለዋል፡፡

ዶክተር ሳሙኤል እንደሚሉት ለየት የሚያደርጋት የአሮጌው መጨረሻ፣ የአዲሱ መግቢያ መሆኑ ሲሆን የሀይማኖት ተቋማት ወስደው ለተለያዩ አውዶች መጠቀማቸውም ለየት ከሚያደርገው ባህሪያት መካከል ተጠቃሽ ነው በማለት አብራርተዋል፡፡

በሀዋሳ ዩኒቨርሲቲ የማህበራዊ ሳይንስ ትምህርት ክፍል የባህል፣ ታሪክ እና አንትሮፖሎጂ ተመራማሪ ረዳት ፕሮፌሰር አማሎ ቶጋ በአንፃሩ የዘመን አቆጣጠር በሁለት ይከፈላል ሲሉ ማብራሪያቸውን ይጀምራሉ፡፡ እነሱም መነሻ የሚያደርጉት መሬት በፀሐይ ዙሪያ የምታደርገው ጉዞ እና ጨረቃ በመሬት ዙሪያ የምታደርገው ዙረት ወይም እንቅስቃሴ እንደሆነ ይገልፃሉ፡፡

መሬት በፀሐይ ዙሪያ ስትሽከረከር የሚጠቀሙት ካላንደር ሶላር ሲሆን ጨረቃ በፀሐይ ዙሪያ ስትሽከረከር ደግሞ ሉናአር ካላንደር እንደሚባል ተናግረው ኢትዮጵያ የምትከተለው ሶላር ካላንደርን እንደሆነ ነው የጠቆሙት፡፡

ግሪጎሪያን ካለንደር የሚጠቀሙት ሀገራት የ12 ወራት ሲኖራቸው የእኛ ደግሞ 13 ወራት አሉት፡፡ ምክንያቱም የግርጎሪያን ወደ አራት ወራት 30 ቀናት ይኖራቸውና ሌሎቹ 31 ቀናት ናቸው ሲሉም ያብራራሉ፡፡

የሀገራችን 12 ወራት እያንዳንዳቸው እኩል 30 ቀናት ሲኖራቸው ሌሎች ቀሪ ጊዜያት በመጨረሻ ላይ 5፤ በአራት ዓመት አንዴ 6 እና ከ600 ዓመታት በኋላ 7 የሚሆንበት አጋጣሚዎች እንዳሉ ጠቁመዋል፡፡

በተለይ በኦርቶዶክስ ሀይማኖት ተከታዮች ዘንድ ብዙ ክዋኔዎች የሚደረጉበት፣ የሚፆሙበትና ፀበል የሚጠመቁበት እንዲሁም ሌሎች ክዋኔዎች የሚፈፀሙበት የአሮጌው ዓመት መጨረሻ ብሎም ሁሉንም በአዲስ ነገር ለመተካት ርብርብ የሚደረግበት በመሆኑ ደስታ ይፈጥራል፡፡