ጌዴኦው -መስቃን

ጌዴኦው -መስቃን

በጌቱ ሻንቆ

አሁን ከቀኑ አራት ሠዓት አቅራቢያ ነው። ከቡታጅራ ሀዋሳ ማቅናት የጀመረው “ኤፍ ኤስ አር” የህዝብ ማመላለሻ መኪና ውስጥ ነን ። የመኪናው መጨረሻ ወንበር ላይ ተቀምጠናል ። እኔ ከተቀመጥኩበት የመኪናው ተቃራኒ ጥግ ሁለት ልጆች ተቀምጠዋል። አንደኛው የ17 ዓመት ወጣት ነው። ሁለተኛው በግምት የ13 ዓመት ልጅ ነው። ሁለቱም ሀሳብ እየተለዋወጡ ነው።

የ13 ዓመቱ ልጅ ” በእኔ ቋንቋ አንድ ‘ቁና’ ነው”

የ17 ዓመቱ ወጣት ፣ ” በእኔ ቋንቋ’ አት ‘ ነው”

“በእኔ ቋንቋ አንድ ‘ቁና’ ነው ” ፣ ያለው የ13 ዓመት ግድም ልጅ ለስራ ቡታጅራ አካባቢ ሄዶ ወደ ትውልድ ቀዬው በመመለስ ላይ ያለ የሲዳማ ልጅ ነው-ሰዎችዬ። እሱ ወደ አካባቢው ካቀና በኋላ የኖረው ክስታኔ ቤተ ጉራጌ ቤት ውስጥ ይመስላል። የዘዬ ልዩነቱ በዚህ ምክንያት የተፈጠረ ነው።

በእርግጥ መስቃንኛ ለቁስ “አት” የሚለውን ቃል ተጠቅሞም ሠውን በቁጥር ለመግለፅ ሲፈልግ ግን “ቁና” ይላል። በክስታንኛ ግን ሁሉም “ቁና” ናቸው።

እንዴት ነው ነገሩ? ማለቴ አልቀረም። ድንገት ስልክ ተደወለ። ስልክ የተደወለው ወደ 17 ዓመቱ ወጣት ወደያዘው ተንቀሳቃሽ የእጅ ስልክ ነበር። ኣኻ! ልጁ ወደ ተንቀሳቃሽ ስልኩ ስልክ ከደወለለት ሠው ጋር በመሥቃንኛ እያወራ ነው። አቀላጥፎ ነው የሚናገረው። ትኩረቴን ሳበው።

ወደ ጥያቄ ገባሁ።

“ስምህ ማነው?”

“መሀመድ ጀማል”

“የት ነው የምትኖረው?”

“ዳና “

“ዳና” ከቡታጅራ በስተምዕራብ አቅጣጫ ወደ ወልቂጤ በሚወስደው መንገድ ላይ ከቆቶ ጊዮርጊስ በስተደቡብ አቅጣጫ የሚገኝ ተራራማ መንደር ነው።

መሠል ከፍታማ ስፍራዎች በዚህ ስያሜ የሚጠሩ አሉ።

“ዳና በብዛት በሀገራችን ጎንደር እና ወሎ አካባቢ አለ፡፡ ዳና የእውቀት ስፍራ ወይም ሃሪማ ይሉታል ደረሶች እዛው ኑሯቸውን መስርተው እውቀት የሚቀስሙበት ነው።” ፣ ብሎኛል አንድ ወዳጄ።

እስልምና ሀይማኖትን ለማስፋፋት አካባቢው ላይ ሼህ ኢሳ የሚባሉ ሰው፣ ወደ ሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ሄደው አስተምህሮቱን ተቀብለው ከመጡ ወዲህ፣ ስፍራው ላይ ከትመው ነበር። እናም “ዳና ” የሚለው መጠሪያ ከዚህ ሀሳብ ጋር አብሮ የሚሄድ ይመስላል ።

“መሀመድ ጀማል” የመጀመሪያ ስሙ አልመሰለኝም ። እንግዲህ ጥያቄያችን ቀጥሏል።

” መሀመድ ጀማል የመጀመሪያ ስምህ ነው? ማለቴ እናትና አባትህ ያወጡልህ?”

“አይደለም አክሊሉ ነበር ስሜ? “

“እንዴት ተቀየረ? “

“ሰልሜ ነው”

“ዳና ላይ ምን ትሰራለህ? “

“ዳና ከመጣሁ አምስት ዓመቴ ነው ። እርሻ አለኝ። አርሻለሁ። ጤፍ በቆሎ…”

“መሬት አለህ?”

“መሬት የለኝም። መሬቱ የአባቴ ነው። የጋሽ ጀማል ሙጎሮ። እሱ ጋ ነው የምኖረው። ልጆች አሉት ጋሽ ጀማል። አንደኛው አስተማሪ ነው። ሌሎቹ ግን ውጭ ሀገር ነው የሚኖሩት ። እኔ አባቴን፣ ጋሽ ጀማልና ሚስቱን፣ እናትና አባቴን እንከባከባለሁ።”

“አረብ አገር ካሉት የጋሽ ጀማል ልጆች ጋር ትገናኛለህ?”

“አዎ። ስልክ ይደውላሉ”

ትንሽ ግልፅ ያልሆኑ ነገሮች አሉ። “መሀመድ ጀማል” የጋሽ ጀማል የስጋ ልጅ ነው ወይስ አይደለም?

“መሀመድ መሥቃን ነህ?”

“አይደለሁም ። ጌዴኦ ነኝ”

አስገራሚ ነገር ነው። መሀመድ ጀማል (አክሊሉ) እንዴት ወደ ዳና መጣ?

“ይዞኝ የመጣው ኢላሉ ነው። የዳና መንደር ልጅ ነው። የምኖርበት አካባቢ ጌዴኦ ውስጥ ከገደብ አልፎ ጎቲቲ የሚባል ስፍራ ነበር። ኢላሉ እዛ ሱቅ ነበረው። እሱጋ እሰራ ነበር። አንድ ዕለት አገር ቤት እንሂድ የሚል ሀሳብ አመጣ። ተስማማሁ። ይዞኝ ወደ ዳና መጣ። እሱ ተመልሶ ሲሄድ እኔ ዳና ቀረሁ። ጋሼ ጋ”

” አሁን የት እየሄድክ ነው?”

“ጎቲቲ ወላጅ ቤተሠቦቼን ጥየቃ። እመለሳለሁ። እንጨት ተሠጥቶኛል። ምስማርና ቆርቆሮ አሟልቼ ቤት ልሰራ ነው። አባቴ ፣ ጋሽ ጀማል ቤት የምሰራበት መሬት ሰጥቶኛል”

“አግብተሃል? “

ሳቅ ። “ገና ልጅ ነኝኮ። 17 ዓመቴ ነው።”

“አታገባም?”

“ጊዜው ሲደርስ አገባለሁ። አይቀርም።”

“ማንን ነው የምታገባው?”

“መሥቃኗን”

“የአንድ ማህበረሰብ የአኗኗር ዘይቤ ምን ያህል የአንድን ከተለየ ማንነት የመጣን ግለሰብ እንደሚቀይር እንዲሁም ብሔርን ብቻ የተለየ የማንነት መገለጫ አድርገው ለሚወስዱ አስተማሪ ነው” ይላል – ይህን ታሪክ ያጫወትኩት ሰው።

መሀመድ ጀማል (አክሊሉ)- ጌዴኦው መስቃን።