የኢትዮጵያዊያን ብቻ የዘመን ስሌት
በኢያሱ ታዴዎስ
የክረምቱ ወራት ለኢትዮጵያ ጸጋዎቿ ናቸው። ወንዞች እንዳሻቸው ይፈስሱባታል። ከአፍ እስከ ገደፋቸው ጢም ይላሉ። የበጋው ሃሩር አንድዷቸው የተቃጠሉና ወዳለመኖር የመጡ የሚመስሉት እጽዋትም ነፍስ ዘርተው በአዲስ ህይወት ለምልመው ያጌጣሉ።
አበቦች ፍካታቸው ይለያል። ሳሮች ጠዋት አጢዘው ቀትር ላይ ጸሃይ ሞቀው ወደ ምሽት ገደማ ከሰማይ በሚወርድ ጠል ይረሰርሳሉ። እንስሳት ጠግበው በልተው በየመስኩ ይፈነጫሉ። ነፍሳት ይራባሉ፣ በዛ ብለው ከዛፍ ዛፍ እየተሸጋገሩ ምግባቸውን ይቀስማሉ። አዕዋፋት አየሩን እየቀዘፉ ለምግባቸው አደን ይሰማራሉ፤ ሲያሻቸው በነጻነት ሰማዩ ላይ ይበራሉ፤ ሰማዩ ያዘለውን ዝናብ ቁልቁል ሲለቀው ደግሞ ወደ ቀለሱት ጎጆ ያቀኑና በዚያው ይመሸጋሉ።
ሰዎች የሚፈራረቀውን ዝናብ አዘል አየር ተጠቅመው ለመጪው ዓመት የሚሆናቸውን እህል ይንከባከባሉ፣ ውጥናቸውን ወጥነው ለማሳካት ይሰማራሉ። ነገን በተስፋ ተመልክተው ዛሬ ላይ ደፋ ቀና ይላሉ። ለዚህ ነው የክረምቱ ወራት ለኢትዮጵያዊያን ጸጋ ናቸው የሚባለው።
ከሰው ጀምሮ እንስሳው፣ እጽዋቱ ሁሉ ጠግቦ ያድራል። ይለመልማል። ይኸው እኛም ክረምቱን አገባድደን የዘንድሮዋን 2015 ዓ.ም ልንሸኝ ተሰናድተናል። ይህ ጊዜ ሲታሰብ ደግሞ ለኢትዮጵያዊያን የተለየ ትርጉም አለው። ይኸው ነው ከየትኛውም የዓለማችን ሀገራት ልዩ የሚያደርገን።
የትኛውም ሀገር በጊዜ ሰሌዳው ላይ ያላሰፈረው አስራ ሶስተኛ ወር እና አሮጌው ዓመት ተሸኝቶ አዲሱን የምንቀበልበት የራሳችን ቀን። በኢትዮጵያ ምድር የአዲሱ ዓመት ብስራት የሚጀምረው ገና ነሃሴ ወር ላይ ነው። ሀምሌ ላይ በዝናብና በጭጋግ ትርዒቶች ታጅቦ በጨለማ የሚዋጠው ሰማይ ነሃሴ አጋማሽ ላይ ፈገግታውን መለገስ ይጀምራል። አዲስ ጮራ እየፈነጠቀ እንደሆነም ያሳብቃል። ለዚያ ነው የብርሃን ተስፋ ወር የሚባለው።
የሰማዩም ድምቀት ዝናብ ቢፈራረቅበትም ጳጉሜ ላይ እየደመቀ አዳስ ዓመትን ይወልዳል። ታዲያ ይሄ ተፈጥሯዊ ኡደት ለዘመናት በኢትዮጵያ ምድር የታየ ነው። አሁንም ቀጥሏል። ነገም ይቀጥላል።
ይህ ዓለም ኢትዮጵያን የሚያውቃት አንዱ ምልክቷ ነው። የራሷ አስራ ሶስት ወራትና አዲስ ዓመት። ኢትዮጵያን ከሌላው ዓለም የሚለየው የጊዜ ሰሌዳዋ ወይም ደግሞ የዘመን አቆጣጠር የተለያዩ ሳይንሳዊ እና ኃይማታዊ እሳቤዎች ይንጸባረቁበታል፡፡ በርካታ ጸሃፍትም ይህን እሳቤ ተመርኩዘው መጽሃፍትን ጽፈው ለንባብ አብቅተዋል፡፡
ከዚህም መካከል ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ አለቃ አያሌው ታምሩ እና ሌሎች ጸሃፍት ለንባብ ያበቋቸውንና ብዙዎች የሚስማሙበትን በማጠናቀር እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር አዲስ ዓመት፣ በጁሊያን ዘመን አቆጣጠር በነሃሴ (August) 29 ወይም 30 የሚጀምር ሲሆን በጎርጎሮሳዊያን ዘመን አቆጣጠር ደግሞ ከ1901 እስከ 2099 ድረስ በመስከረም (September) 11 ወይም 12 ይጀምራል፡፡
በየአራት ዓመቱ አንድ ቀን ይጨመራል። በአንድ ዓመት ውስጥ አስራ ሁለት ባለሰላሳ ቀናት እና አንድ ባለአምስት ቀናት ያሉባቸው ወራት አሉ፡፡ ከባለአምስት ቀናቱ በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ስድስት ቀን ይኖረዋል፡፡
በኢትዮጵያ ዘመን አቆጣጠር ዓመታት ሁሉ በአራት መደባት ይዞራሉ፡፡ እነዚህም ዓመታት በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በሐዋሪያት ስሞች ዘመነ ማቴዎስ፣ ማርቆስ፣ ሉቃስ እና ዮሃንስ በመባል ይጠራሉ፡፡ ጳጉሜ 6 ቀናትን ሲይዝ ዘመነ ሉቃስ ይባላል፡፡
ይህም 365 ቀናት የሚኖሩት አንዱ ዓመት፣ ዘመነ ሉቃስ ላይ 366 ቀናት ይኖሩታል፡፡ ይህ የዘመን ቀመር የሚሰላበት ባህረ-ሃሳብ ይባላል፡፡ ባህረ-ሃሳብ ቁጥር ያለው ዘመን ማለት ሲሆን ዓመታትን፣ ወራትን፣ ሳምንታትን፣ ዕለታትን፣ ደቂቃን እና ድቁቅ ሰዓታትን በየመጠናቸው የሚገልጽ፣ የሚተነትን ወይም የሚለካ የቤተ ክርስቲያን የቁጥር ትምህርት ነው፡፡
የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠርም የሚመነጨው ከባህረ-ሃሳብ ነው፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በሳይንሳዊ ስሌት የተደገፈ አቆጣጠር መሆኑም እሙን ነው። በመሆኑም አንድ አመት የሚባለው የመሬትና የፀሀይ ኡደት ነው፡፡ መሬት ኡደቷን ለመጨረስ አንድ አመት ወይም 365 ከ1/4 ቀን ይፈጅባታል፡፡
ይህም ስሌት በዘመነ ማቴዎስ 12 ወር፣ 30 ቀን ሌላ የጳጉሜ 5 ቀን ከ6 ሰአት (1/4 ቀን ማለት 6 ሰአት ነው) ሲጨመርበት ነው፡፡ ይህ ስሌት በማርቆስ እና በዮሃንስም ተመሳሳይ ነው፡፡ በሉቃስ ግን ከእያንዳንዱ ያልተቆጠሩ 6 ሰአታት አሉ፡፡ የማቴዎስ 6፣ የማርቆስ 6፣ የሉቃስ ስድስት፣ እና የዮሐንስ 6 ተደምሮ አንድ ቀን ሙሉ ይሆንና ጳጉሜ 6 ቀን ይሆናል ማለት ነው፡፡
በአጠቃላይ የኢትዮጵያዊያን የዘመን ስሌት ጥልቅ የሆነ የራሱ ትንታኔ አለው፡ ፡ ይህም ሳይንሳዊ እና ኃይማኖታዊ ትርጓሜ እንዳለው ይነገራል፡፡ ሳይንሳዊው ስሌት ጠቢባን አባቶች መሬት በጸሃይ ላይ የምታደርገውን ኡደት ተረድተው የጊዜ መለኪያ እና መቁጠሪያ አስ ቀምጠዋል፡፡
በዚህም ስሌት መሰረት ነው እያንዳንዱ የጸሃይ እና ጨረቃ ኡደት ተደምሮ አንድ ዓመት 365 ወይም 366 ቀናት የሚመጣበት ስሌት የሚቀመጠው፡፡ ይህም ስሌት አቆጣጠሩ በሳድሲት፣ ኀምሲት፣ ራብዒት፣ ሣልሲት፣ ካልዒት እና ኬክሮስ ተለክቶ የተደማመረው ውጤቱ ወደ ዓመት ይቀየራል፡፡ በዚህም መሰረት አጠቃላይ ስሌቱ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
1ኛ. ሳድሲት- ይህ ቁጥር 0.00000185 ሰከንድ ነው።
2ኛ. ኀምሲት- ይህ ቁጥር 0.00011 ሰከንድ ነው።
3ኛ. ራብዒት- ይህ ደግሞ 0.0067 ሰከንድ ነው።
4ኛ. ሣልሲት- ይህ ደግሞ 0.4 ሰከንድ ነው።
5ኛ. ካልዒት- ይህ ደግሞ 24 ሰከንድ ነው
6ኛ. ኬክሮስ- ይህ ደግሞ 24 ደቂቃ ነው።
ከዚህም መነሻ 60 ኬክሮስ= 1 ዕለት ወይም 24 ሰዓት ነው። ይህ ደግሞ 1 ሰዓት 2.5 ኬክሮስ ነው ማለት ነው። ጨረቃ በቀን ከፀሐይ 1 ኬክሮስ ከ 52 ካልዒት ከ 31 ሣልሲት በአነሰ ነው።
በቀን 1 ኬክሮስ በ30 ቀን 30 ኬክሮስ ይሆናል። በ2 ወር 60 ኬክሮስ ይሆናል። 60 ኬክሮስ ደግሞ 1 እለት ስለሆነ። በ2 ወር 1 እለት በ12 ወር 6 እለት ታበራለች ማለት ነው።
በ12 ወር ወይም በአንድ አመት 5 ቀንና 15 ኬክሮስ ከ1 ሣልሲት ይሆናል፡፡ የቀረችው 52 ካልዒት × 30 ቀን × 12 ወር= 18720 ካልዒት በአመት ይገኛል።
ይህ ወደ ኬክሮስ ሲለወጥ 312 ኬክሮስ ይመጣል። በመቀጠል 30 ሣልሲት × 30 ቀን × 12 ወር 10800 ሣልሲት ይመጣል፡፡ ይህ ወደ ኬክሮስ ሲቀየር 3 ኬክሮስ ይሆናል።
ይህ ማለት የ52 ካልዒትየ 30+(1) ሳልሲት ጠቅላላ ሲደመር… 312+3=315 ኬክሮስ ይሆናል። ይህ ወደ እለት ሲቀየር 5 ቀን ከ15 ኬክሮስ ይሆናል። ይህ 5 ቀን ተሰብስቦ ጷግሜ ይሆናል።
የተረፈው 15 ኬክሮስ ለ4 አመታት ሲጠራቀም በ4 ዓመት 4×15=60 ኬክሮስ ወይም አንድ እለት ይሆናል። በአራት ዓመት አንድ ጊዜ ጳጉሜ 6 የሚሆነው በዚህ ምክንያት ነው።
አንዱ ሣልሲት ደግሞ በ600 ዓመት 1 ቀን ይሆናል። ይኽውም 1 ሣልሲት×30 ቀን×12 ወር×600 ዓመት 216000 ሣልሲት ይገኛል፡፡ ይህ ወደ ኬክሮስ ሲቀየር 60 ኬክሮስ ይሆናል። 60 ኬክሮስ ደግሞ አንድ ቀን ወይም እለት ነው። ስለዚህም በ600 ዓመት አንድ ጊዜ ጳጉሜ 7 ይሆናል ማለት ነው።
ታዲያ ይህ ስሌት እየተሰላ ነው በዓመት የሚመጣው ውጤት አንድ ዓመት ተብሎ የሚቆጠረው፡፡ በዚህ ስሌት መሰረት የኢትዮጵያ የዘመን አቆጣጠር እውን ሆኗል፡፡ ስሌቱም በእንዲህ ዓይነት መልኩ ይቀጥላል…
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው