“መቻላችንን በተግባር ማረጋገጥ ይኖርብናል”
በደረጀ ጥላሁን
ብልህና ጠንካራ ወጣቶች በልጅነት ዘመናቸው የወደፊት ሕልሞቻቸውን ያስቀምጣሉ፡፡ የተለያዩ የአመራር ቦታዎች ላይ ለመገኘት ማሰብ፣ በትምህርት እንዲሁም በንግድና በሌሎች ዘርፎች ከፍተኛ ደረጃ መድረስ ከህልሞቻቸው መካከል ሊሆኑ ይችላሉ፡፡
ነገር ግን በተለይ ለሴቶች በአፍላ የወጣትነት ዘመን ላይ ሲደረሱ በከፍተኛ ተግዳሮቶች እና ለሴት ልጅ ያለው አመለካከት ዝቅተኛ በሆነ ማኅበረሰባዊ ተጽእኖዎች ምክንያት ወደግባቸው የሚያደርጉት ጉዞ እንቅፋት ሊያጋጥመው ይችላል፡፡
ይሁን እንጂ አላንቀሳቅስ የሚሉ ተግዳሮቶች ብዙ ቢሆኑም ተስፋ ሳይቆርጡ መታገል አለባቸው፡፡ ለዚህም በትምህርት በመታገዝ በውስጣቸው ያለውን ተሰጥኦ በመጠቀም እራሳቸውንም ሆነ ሃገራቸውን ለመቀየር ጠንክረው መማር ዋነኛው መንገዳቸው ሊሆን ይገባል፡፡ የሳምንቱ እቱ መለኛ ዝግጅታችንም በትምህርት ወደግቧ መድረስ የቻለች ወጣት ላይ ትኩረት አድርጓል፡፡ መልካም ንባብ፡፡
ወጣት አበዛሽ አስናቀ ትባላለች። ትውልድና እድገቷ ሀዋሳ ከተማ ነው። የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርቷን ሀዋሳ ከተማ በሚገኘው አድቬንቲስት ት/ቤት እንዲሁም የሁለተኛ ደረጃ ትምህርቷን ታቦር ኢቫንጀሊካል ትምህርት ቤት ተከታትላለች። ከዚያም በሀዋሳ ዩኒቨርስቲ ግብርና ኮሌጅ በምግብ ሳይንስና ፖስት ሃርቨስት ቴክኖሎጂ ትምህርት ዘርፍ የመጀመሪያ ድግሪዋን ሰርታለች፡፡
አሁን ላይ ከሥራዋ ጎን ለጎን በቢዝነስ አድምንስትሬሽን የሁለተኛ ድግሪ ትምህርቷን እየተከታተለች ትገኛለች፡፡ በትምህርቷ ጠንካራና ተወዳዳሪ ስትሆን በዩኒቨርስቲ ቆይታዋ የማእረግ ተመራቂ ነበረች፡፡ ለዚህም የቤተሰቦቿ እገዛ አልተለያትም፡፡ አባቷ ለትምህርቷ አጋዥ የሆኑ መጻህፍትን በመግዛት እናቷ ደግሞ የቤት ውስጥ የሥራ ጫና እንዳይኖርባት በማድረግ ትኩረቷን ትምህርቷ ላይ እንድታደርግ አግዘዋታል፡፡ የመጀመሪያ ሥራዋን በሀዋሳ ኢንዱስትሪ ፓርክ በጋርመንት ኢንዱስትሪ በመርቻንዳይዘር ዘርፍ ለአንድ አመት ከስድስት ወር ያህል ሰርታለች፡፡
ሥራው ጥሩ ቢሆንም በተማረችበት የትምህርት መስክ ብትሰራ ይበልጥ ውጤታማ እንደምትሆን እርግጠኛ በመሆኗ በሞያዋ ለመስራት ከፍተኛ ፍላጎት አደረባት፡፡ እናም ሥራዋን እየሰራች ከተማረችው ሞያ ጋር የሚገናኝ ሥራ ማፈላለግ ጀመረች፡፡ በይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪ ውስጥ የሚገኘው ‹‹ሳንቫዶ›› የአቮካዶ ዘይት የሚያመርት ድርጅት በመስኩ የሰለጠኑ ባላሙያዎችን እንደሚፈልግ መረጃ ደረሳት።
ፍላጎቷን ሊያሳካ የሚችል የሥራ መስክ በመሆኑ የመጠቀጠር ጉጉቷ ጨመረ፡፡ እናም ለመወዳደር የሚያስችላትን አስፈላጊውን የትምህርት መረጃዎች በማሟላት በውድድሩ ተሳተፈች፡፡ ወጣት አበዛሽ ከተማረችው ትምህርት ጋር ቀጥታ ግንኙነት ባለው በዚህ ድርጅት ለመስራት ብቁ ሆና በመመረጥ 2011 ዓ/ም ሥራ ጀመረች፡፡ የምርት ክፍል ተቆጣጣሪ በመሆን ሥራ የጀመረች ሲሆን በሥራዋ ትጋት የተነሳ እድገት ለማግኘት ብዙ ጊዜ አልወሰደባትም፡፡ አሁን ላይ የፕሮዳክሽን እና ቴክኒካል ስራ አስፈፃሚ ሆና ድርጅቱን በማገልገል ላይ ትገኛለች፡፡ ሥራውን በሚገባ ለማከናወን ከተለያዩ አካላት የሞያ እገዛ አግኝታለች፡፡ በእሴት ሰንሰለት ላይ ያሉ ክፍተቶችን ለመሸፈን የሚያስችሉ የተለያዩ ሥልጠናዎችን እንዳገኘችም ገልፃለች፡፡
‹‹በተለይም የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስትቲዩት የደቡብ ማእከል ለምንሰራቸው ሥራዎች እገዛ የሚያደርግልንን ክህሎት እንድንጨብጥ ከፍተኛ ሚና ነበረው›› ስትል ትመሰክራለች፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ለሥራው አስፈላጊ የሆነውን ግብአት በብዛትና በጥራት ለማግኘት እንዲቻል በዚህ ዙሪያ ከሚሰሩ መንግስታዊ ካልሆኑ ድርጅቶች ጋር በመተባበር ይሰራሉ። የተሻሻሉ የአቮካዶ ዝርያዎችን ምርቱን ለሚያቀርቡ አርሶ አደሮች በማስተዋወቅ ከምርቱ የተሻለ እንዲጠቀሙ እየተሰራ እንደሚገኝ ወጣት አበዛሽ አጫውታናለች፡፡ በሀገራችን በተለይ በግብርናው ዘርፍ ሊሰራባቸው የሚገቡ ብዙ ሥራዎች እንዳሉ የምትናገረው አበዛሽ እነዚህን ሀብቶች በማቀነባበር ተጠቃሚ ለመሆን መሥራት ይገባል ባይ ነች፡፡ በተለይ ይርጋለም አካባቢ ያልተነካ በቂ ሀብት መኖሩን ታወሳለች።
አናናስ፣ አፕል የመሳሰሉትን በዘመናዊ መልኩ በማቀነባበር ለውጪ ገበያ ማቅረብ እንደሚቻል ጠቁማለች፡፡ የቡና ምርት ላይ እሴት በመጨመር ለውጪና ለሀገር ውስጥ ገበያ በማቅረብ የተሻለ ጥቅም ማግኘት ይቻላል ስትል ሥራዋን መሠረት ያደረገ ሀሳብ አጋርታናለች፡፡ የግብርና ምርቶችን ማቀነባበር ሥራ ላይ የተሰማራው ድርጅት ከትርፍ ባሻገር በአካባቢው ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ችሏል፡፡ አምራች አርሶ አደሮች ምርታቸውን በዘላቂነት በማቅረብ ተጠቃሚ እንዲሆኑ ያደርጋል፡፡ ከዚህ አኳያ ለዚህ ዘርፍ የሚመለከታቸው አካላት ሁሉ ልዩ ትኩረት ቢሰጡት መልካም መሆኑን ታነሳለች፡፡ ወጣት አበዛሽ እንደምትለው ሴት ልጅ ከወንድ እኩል የመስራት አቅም አላት። ሴቶች አቅም እንደሌላቸው ይነገር የነበረው አመለካከት እየቀነሰ ቢሆንም ሙሉ ለሙሉ ያልተቀረፈ ችግር መሆኑን ታወሳለች፡፡ “የተፈጠረው አስተሳሰብ ትክክል ያልሆነና አሁንም መሰራት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
ሴቶች እንደማንኛውም ሰው እኩል አእምሮ ስላለን ሀገርን ማገልገል እንደምንችል እና የአልችልም ስሜት ተላቀን መቻላችንን ማረጋገጥ ይኖርብናል›› ስትል ሀሳቧን አካፍላናለች፡፡ የ25 አመቷ ወጣት የምትፈልገው እና የምትወደውን ሥራ በመስራቷ ደስተኛ ነች። ሥራውን ከሞያ አጋሮቿ ጋር በመተባበርና በመደጋገፍ ትሰራለች፡፡ ይህም በድርጅቱ ተወዳጅና ታታሪ ሰራተኛ አድርጓታል፡፡ አቶ ዮሴፍ እሸቱ በይርጋለም አግሮ ኢንዱስትሪ ሳንቫዶ የአቮካዶ ዘይት ማምረቻ ድርጅት ውስጥ የምርት ተቆጣጣሪ ናቸው። ከአበዛሽ ጋር አብረው የሚሰሩ ሲሆን በሥራዋ ታታሪ እና ሰርታ የምታሰራ መሆኗን ይመሰክራሉ፡፡ መሪ ከመሆኗ አንፃር ሰራተኛውን በእኩል የምታይና ከሁሉም ጋር ተግባብታ ለስራው ስኬታማነት ተግታ የምትሰራ ነች ሲሉ ይመሰክራሉ፡፡ ለቤተሰቡ አምስተኛ ልጅ የሆነችው አበዛሽ ሁለት ወንድሞቿና ሶስት እህቶቿ ሥራ ላይ ናቸው፡፡ አበዛሽ ያለመችው በህክምና ዶክተር ለመሆን ቢሆንም በተመደበችበትና በተማረችው ትምህርት ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማት ተናግራለች፡፡
ለሥራዋ እገዛ የሚያደርግላትን የተለያዩ አጫጭር ኮርስችን በኦን ላይን እየተማረች ሲሆን ለወደፊቱም ከሞያዋ ጋር ተዛማጅ ትምህርቷን በመማር የተሻለ ደረጃ ለመድረስ እቅድ አላት፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለይ በሴቶችና ወጣቶች ላይ ትኩረት በማድረግ ለመስራት የረጅም ጊዜ እቅድ እንዳላት አጫውታናለች፡፡ ወጣት ሴቶች አዲስ ነገርን መፍራት እንደሌለባቸው እና ያልተሳካላቸው ነገር ቢኖርም እንኳን እንደገና በሌላ መንገድ ለማሳካት መጣር እንዳለባቸው ትመክራለች።
“ህይወት አንድ መስመር ብቻ ሳይሆን በርካታ አቅጣጫዎች እንዳሏትም መታወቅ አለበት” የሕይወት መመሪያዋ ነው። በመሆኑም ወጣቶች በተለይ ደግሞ ሴቶች ጊዜያቸውን በአግባቡ በመጠቀምና በስነምግባር በመታነጽ ስኬታማ ለመሆን መትጋት ይጠበቅባቸዋል መልእክቷ ነው፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው