በመሐሪ አድነው
ይህ ጉባኤ በታሪኩ፣ በይዘቱና በኩነቶችም የተለየ ጉባኤ እንደሆነ የክልሉ ምክር ቤት ዋና አፈጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ሰርሞሎ በመግለፅ ነበር የጉባኤው መከፈትን ያበሰሩት፡፡
በንግግራቸው በክልሉ የአደረጃጀት ጥያቄ፣ የግጭት፣ የእርስ በርስ ጥርጣሬ፣ የሴራ ፖለቲካ እንዲሁም የመልካም አስተዳደርና ልማት ሳንካ ሆኖ ሰቅዞ ይዞ የቆየ አጀንዳ እንደነበር ጠቁመዋል። ያም ቢሆን ምስጋና መልካምነትና በጐነትን ከእውነት ጋር አሰናስሎ ለያዘው ህዝባችን ይሁንና ከተነገረውና ከተተረከው ከጥላቻ ይልቅ አንድነትንና አብሮነትን አስበልጦ በመጓዙ ተገቢ ምላሽ አግኝቷል፡፡
በዚህም በየደረጃው ሠፊ ውይይትና ምክክር ተደርጐበት በህገ መንግስታዊ አግባብና የህዝቦችን የጋራ እሴትን ታሳቢ ባደረገ መንገድ እንዲፈታ ለማድረግ ለተያዘው እቅድ በጐ ምላሽ መስጠት ተችሏል ብለዋል፡፡ በዚህም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ህዝበ ውሳኔ በስድስት ዞኖችና በአምስት ልዩ ወረዳዎች ታሪካዊ፣ የዴሞክራሲ ልምምድ ማሳያና የተቋማት የተለጠጠ ነፃነት ማጐልበቻ በሆነ መልክ ተፈፅሟል፡፡
የውጤቱ ዝርዝር ሪፖርት ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ቀርቦ ውሳኔ ባገኘበትና አዲስ የኢፌድሪ 12ኛ ክልል ውልደትንና ነባሩ ክልል ሪፎርም በሚደረግበት ጊዜ የሚካሄድ ጉባኤ ነው ብለዋል፡፡ ህዝባችን አግዞን ሁሉን በትዕግስት፣ በጥበብና በብልሃት አልፈን በውይይት፣ በጥናት ላይ በተመሠረተ አካሄድ ከህዝባችን ጋር ተግባብተን በመሥራትና በእያንዳንዱ ምዕራፍ ህገ መንግስታዊነቱን በማረጋገጥ የአደረጃጀት ጥያቄዎችን መመለስ ችለናል።
በዚህ ምክር ቤት 3ኛ ክልል በማዋለድ የሥልጣን ርክክብ ለማድረግ እንዲሁም ነባሩ ክልልም የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሰጠው ውሳኔ መሠረት ተፈፃሚ ለማድረግ እየተሠናዳን እንገኛለን ብለዋል ዋና አፈ ጉባኤዋ፡፡
በቀጣይ ትኩረት ማግኘት ያለበት አብይ ጉዳይ የህዝቦች ትስስር ከአደረጃጀት በላይ መሆኑን መረዳት ነው ያሉት ወ/ሮ ፋጤ ለዘላቂ ሠላምና ዴሞክራሲ፣ ወንድማማችነትና ለጋራ እድገት እጅ ለእጅ ተያይዘን በመሥራት አብሮነትን ከወትሮው በተሻለ ለማጠናከር ዝግጁ መሆን እንደሚያስፈልግ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር አቶ እርስቱ ይርዳው በ2015 በጀት ዓመት በክልሉ በኢኮኖሚ፣ ማህበራዊና መሠረተ ልማት እንዲሁም በሠላምና መልካም አስተዳደር ግንባታ ለማከናወን ታቅደው የተከናወኑ ተግባራት አፈፃፀም ጠቅለል ባለ መልኩ አቅርበዋል፡፡ በበጀት አመቱ በግብርናው ዘርፍ የክልሉን ብዝሃ የግብርና ልማት ፀጋዎች አስፍቶ ለመጠቀም ታቅዶ ወደ ትግበራ በተገባው መሠረት የበልግና የመኸር እርሻ፣ የበጋ መስኖ፣ የእንስሳት ዘርፍ ልማትና የሌማት ትሩፋት ፣ የአረንጓዴ አሻራና የአካባቢ ልማትና ጥበቃ ሥራ በርካታ ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
በ2015/16 የበልግ አዝዕርት፣ ሆርቲካልቸር፣ በፍራፍሬ እና በእንሰት ሰብሎች 1 ሚሊዮን 044 ሺህ 888 ሄክታር መሬት በማልማት 102 ሚሊዮን 489 ሺህ 692 ኩንታል ለማምረት ታቅዶ ወደ ተግባር ተገብቷል፡፡ በዚህም በአዝዕርትና ሆርቲልቸር ሠብሎች ከተሸፈነው 1 ሚሊዮን 019 ሺህ 115 ሄክታር መሬት ውስጥ 787 ሺህ 814 ሄክታር በመስመርና 231 ሺህ 301 ሄክታር መሬት ያለ መስመር በዘር ተሸፍኗል፡፡ ከለማው እርሻ ውስጥ የአትክልትና የፍራፍሬ ሠብሎች ምርት እየተሠበሠበ ይገኛል፡፡ ሌሎች ሠብሎችም በነበረው ምቹ የዝናብ ሁኔታ በእድገት፣ አበባ በማበብ እና ፍሬ በማፍራት ደረጃ ላይ እንደሚገኝ አቶ እርስቱ በሪፖርታቸው ገልፀዋል፡፡
የህብረት ሥራ ማህበራት አባላቱን ተጠቃሚ ከማድረግ አልፈው ገበያን እንዲያረጋጉ ለማድረግ 283 አዳዲስ መሠረታዊ የህብረት ሥራ ማህበራትን በማደራጀት የአባላት ቁጥር 94 ሺህ 375 ማድረስ ተችሏል፡፡ በማህበራት የሚደረግ ቁጠባንና ካፒታልን በተመለከተ ብር 193 ሚሊዮን 537 ሺህ 293 ለማድረስ ታቅዶ ብር 219 ሚሊዮን 673 ሺህ 897 ማድረስ መቻሉ በሪፖርቱ ተመላክቷል፡፡ ለአየር ንብረት ለውጥ የማይበገር አረንጓዴ ኢኮኖሚ ለመገንባት በተነደፈው የአረንጓዴ አሻራ ኘሮግራም በሁለተኛው ምዕራፍ በ2015 የተከላ ዘመን በጥምር ደን፣ በቀርከሃ፣ በውበት ዛፎች እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባላቸው የፍራፍሬ ዝርያዎች ከ1 ነጥብ 3 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን ለመትከል መታቀዱ ተጠቁሟል።
እስካሁን ድረስም ታሪካዊውን የአንድ ጀምበር ተከላን ጨምሮ ከ1 ቢሊዮን በላይ ችግኞችን መትከል ተችሏል፡፡ በቀሪው ጊዜ የቀሩትን ለመትከል ርብርብ እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። በከተማ ልማት ዘርፍ የከተማ መሬትን አልምቶ ለተለያዩ አገልግሎቶች ከማዋል አንፃር 2 ሺህ 878 ሄክታር የለማ መሬት ለማዘጋጀት ታቅዶ ነበር፡፡ በዚህም ከአንድ ሺህ 153 ሄክታር በላይ መሬት በማዘጋጀት በጨረታና በምደባ ለማስተላለፍ ተችሏል፡፡ በከተሞች የሚታየውን የመኖሪያ ቤት አጥረት ለመቅረፍ በተለያዩ የቤት ልማት አማራጮች 17 ሺህ 937 ቤቶች ተገንብተዋል።
7 ሺህ 431 የመንግስት ቤቶች ይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲያገኙና ለ2 ሺህ 284 የመንግስት ቤቶች የይዞታ ማረጋገጫ ካርታ እንዲያገኙ ማድረግ መቻሉን ሪፖርቱ ያሳያል። መሠረታዊ የፍጆታ ምርቶች አቅርቦትና ሥርጭትን በተመለከተ 67 ሺህ 106.1 ኩንታል ስኳርና 8 ሚሊዮን 578 ሺህ 179 ሊትር የምግብ ዘይት በ6 ሺህ 332 አሠራጮች እንዲሠራጭና በተደረገው ክትትል ቅሬታና አቤቱታ የቀረበባቸው 81 አሠራጮች ከትስስር እንዲወጡ መደረጉን በሪፖርቱ ተመላክቷል። ህብረተሰቡን በመንገድ መሠረተ ልማት ለማስተሳሰር በህብረተሰብ ተሳትፎ በሁሉ አቀፍ ገጠር ተደራሽ መንገድ ልማትና በመደበኛ የመንገድና ድልድይ ጥናትና ዲዛይን ዝግጅት ግንባታና ጥገና ይካሄዳል፡፡ በዚሁ መሠረት በሁሉ አቀፍ ገጠር ተደራሽ መንገድ ልማት የ1 ሺህ 218.6 ኪ.ሜ. መንገድና የ24 ድልድይ ጥናትና ዲዛይን ስራ ተጠናቋል።
በመንገድ ግንባታም የ318.58 ኪ.ሜ. መንገድ ዲችና ካምበር ሥራ፣ የ291.1 ጠጠር የማልበስና መበተን ሥራ ተከናውኗል፡፡ በአጠቃላይ 248 ነጥብ 9 ኪ.ሜ የሚሸፍኑ 40 የመንገድ ኘሮጀክቶችን ግንባታ በማጠናቀቅ ለትራፊክ አገልግሎት ክፍት ማድረግ ተችሏል፡፡ የድልድይ ግንባታን በተመለከተ ከአሥር ሜትር በላይ ስፋት ያላቸው 12 ድልድዮች ግንባታ ሲጠናቀቅ ቀሪዎቹ ድልድዮች በተለያዩ የአፈፃፀም ደረጃ ላይ ይገኛል፡፡ በኢኮኖሚ ዘርፍ በቀረበው ሪፖርት የክልሉን የሃብት ማከፋፈያ ቀመር በማዘጋጀትና በሚመለከታቸው አካላት ታምኖበት በቀመሩ መሠረት ተከናውኗል። ይህም በመስተዳድር ምክር ቤቱ ፀድቆ በየአስተዳደር እርከኑ እንዲሠራጭ በማድረግ ተግባራዊነቱን የመከታተል ሥራ ተከናውኗል። በተዘጋጀ የመንግስት ካፒታል ኘሮጀክቶች መመልመያና መምረጫ መመሪያ መሠረት ከየሴክተር መሥሪያ ቤቱ ከቀረቡ 769 አዲስ የካፒታል ኘሮጀክቶች መካከል ያለውን የበጀት አቅም ታሳቢ በማድረግ መስፈርቱን ያሟሉ 125 በበጀት ተደግፈው ተግባራዊ እየተደረጉ ይገኛሉ፡፡
የትምህርት ተደራሽነትና ፍትሐዊነት ከማረጋገጥ አንፃር በሁሉም ደረጃ ጥልቅና ንጥረ ተሳትፎ ለማሳደግ የሚያስችል ግብ ተቀምጦ ተሠርቷል በማለት ሪፖርቱ ያትታል። የደ/ብ/ብ/ህ/ክ/መንግስት የዋናው ኦዲተር መስሪያ ቤት የክልሉ መንግስት መስሪያ ቤቶች የ2014 በጀት ዓመት የኦዲት አፈፃፀም ለክልሉ ምክር ቤት ቀርቧል፡፡ ልዩ ኦዲትን በተመለከተ በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት በሥሩ ለሚገኙና ለተቋሙ የሚያገለግሉ የቴክኖሎዷ እቃዎች ግዥ ለመፈፀም ባወጣው የጨረታ ማስታወቂያ መሠረት አሸናፊ ከሆኑት ከተለያዩ ተጫራቾች ላይ ግዥ ለመፈፀም በገባው ውል መሠረት አለመፈፀሙ ተጠቁሟል፡፡ በተወሰደው እርምጃም ድርጅቱ ያልተረከባቸውን እቃዎች በሽያጭ ደረሠኝ (Commercial invoice) እና በማሸጊያ ዝርዝር (Packing list) በዝርዝር ተገልፆ ባልቀረቡ እቃዎች የተከፈለ ቀረጥና ታክስ ብር 4 ሚሊዮን 215 ሺህ 391.25 የተከፈለ መሆኑን በኦዲት ወቅት መረጋገጡ በሪፖርት ቀርቧል፡፡
በደቡብ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል እና በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መካከል የሚኖረውን የአስተዳደራዊና ህጋዊ ጉዳዮች የሚመራበትን ሥርዓት ለመወሰን የሚያስችል የውሳኔ ሃሳብ/ሞሽን/ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡ የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በንብረትና እዳ ክፍፍል /እስከ ዞኖችና ልዩ ወረዳዎች/ ፣ በክልል መጠሪያ ስያሜ እንዲሁም ለትርጉም ክፍት ወይም ተጋላጭ የሆኑ ጉዳዮች ስለመኖራቸው የምክር ቤት አባላት ለተነሱ ጥያቄዎች የሞሽን ኘሮጀክት ጽ/ቤት ምክትል ሥራ አስኪያጅ አቶ ኑሪዬ ሱሌ ምላሽ ሠጥተዋል፡፡
በዚህም የደቡብ ብሔሮች ፣ ብሔረሰቦችና ህዝቦች ክልል መንግስት ምክር ቤት በተሻሻለው የክልሉ ህገ መንግስት አንቀፅ 51/3/ /ሀ/ እና በክልሉ ምክር ቤት የአሠራርና የአባላት ስነ ምግባር ደንብ ቁጥር 16/2008 አንቀፅ 40 መሠረት የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ በሙሉ ድምፅ ፀድቆ አዲሱና ነባሩ ክልል የስልጣን ርክክብ ፈፅመው ጉባኤው ተጠናቋል፡፡
More Stories
“እግሬ ተጎዳ እንጂ አእምሮዬ አልተጎዳም”
“በመጀመሪያዎቹ ደረጃ ላይ ያለው ካንሰር በህክምና የሚድን ነው” – ዶክተር እውነቱ ዘለቀ
መሥራት ችግርን የማሸነፊያ መንገድ ነው