“ድጋሚ የመለያ ምት ዕድል ባገኝ ለመምታት ዝግጁ ነኝ”ጋብርኤል ማጋሌሽ
የአርሰናሉ የመሐል ተከላካይ ጋብርኤል ጋብርኤል ማጋሌሽ ባለፈው የውድድር ዘመን በቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ያጋጠመውን የመለያ ፍፁም ቅጣት ምት ስህተት ወደ ጎን በመተው፣ ወደፊት በተመሳሳይ አጋጣሚ ድጋሚ የመለያ ምት ለመምታት ሙሉ በሙሉ ዝግጁ መሆኑን ገልጿል።
ብራዚላዊው ተከላካይ ባለፈው የውድድር ዓመት በሀንጋሪ ቡዳፔስት በፑሽካሽ አሬና ስታዲዬም በተካሄደው የአውሮፓ ቻምፒየንስ ሊግ ፍፃሜ ጨዋታ አርሰናል በፓሪስ ሴንት ዠርመን በመለያ ምት ሲሸነፍ ወሳኟን የመለያ ፍፁም ቅጣት ምት ሳይጠቀም መቅረቱ ይታወሳል።
ከዚያ አጋጣሚ ወዲህ ለመድፈኞቹ ፍፁም ቅጣት ምት ሳይመታ የቆየው ጋብርኤል፣ ቡድኑ በሚፈልገው ጊዜ ሁሉ ኃላፊነቱን ለመውሰድ ወደ ኋላ እንደማይል አረጋግጧል።
ማግሀሌስ አርሰናል በነገው ዕለት በሜዳው የማጋሌሽ የቀድሞ ክለቡ ከነበረው ሊል ጋር ከሚያደርገው የቻምፒየንስ ሊግ ጨዋታ አስቀድሞ በሰጠው አስተያየት“በፍፃሜ ጨዋታ ማንኛውም ነገር ሊከሰት ይችላል፤ በወቅቱ ጥሩ ተፎካክረን ነበር። ድጋሚ የመለያ ፍፁም ቅጣት ምት የመምታት ዕድል ባገኝ አሁንም ለመምታት ዝግጁ ነኝ” ሲል ተናግሯል።
“ከወቅቱ አጋጣሚ በኋላ የቡድን አጋሮቼ ከፍተኛ ድጋፍ አድርገውልኛል” ያለው ተጫዋቹ “በወቅቱ ማዘኔ አይቀርም፤ ምክንያቱም ማንም ሰው ፍፁም ቅጣት ምት መሳት አይፈልግም። ነገር ግን ከስህተቴ ተምሬበታለሁ፤ አሁንም ዕድሉን ካገኘሁ ለመምታት ዝግጁ ነኝ” ሲል ገልጿል።
ጋብርኤል አክሎም የአርሰናልን የዚህ ውድድር ዘመን ጉዞ አስመልክቶ ሲናገር “በያዝነው የውድድር ዘመን በሁሉም ውድድሮች ጠንካራ ጅምር አድርገናል። በዚህ ዓመት ምን ማሳካት እንደምንፈልግ እናውቃለን፤ ሁሉም ተጫዋች ዝግጁ ነው፤ ለምንጫወትባቸው ዋንጫዎች ሁሉ እንታገላለን” ብሏል።
የሰሜን ለንደኑ ክለብ አርሰናል በአውሮፓ ሻምፒዮንስሊግ ሁለተኛ የሊግ ፌዝ ጨዋታ ነገ ምሽት 4 ሰዓት ላይ ከፈረንሳዩ ክለብ ሊል ጋር በኤምሬትስ ስታዲየም ይጫወታል።
ዘጋቢ፡ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ቀይ ቀበሮዎቹ ቡሩንዲን 3ለ0 አሸነፈ
ወጣቶች ባላቸው እውቀት፣ እምቅ ችሎታና አቅም በተሰማሩበት ስራ መስክ ጠንክረው ከሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ ተናገሩ
ማንችስተር ከቶተንሃም ተጠባቂው ፍልሚያ ሲያደርጉ፤ አርሰናል እና ቸልሲ ድልን ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ