በኢትዮጵያ ተወዳጁ ቅመም

በኢትዮጵያ ተወዳጁ ቅመም

በኢትዮጵያ የሚገኝ ሀገር በቀልና ዘርፈ ብዙ ጥቅም ያለው የቅመማ ቅመም ተክል ነው፡፡ በልዩ መዓዛው ይታወቃል፡፡ በሀገራችን አብዛኛው ምግብ ሲበስል ጥቅም ላይ የሚውል ቀዳሚው የቅመም ዓይነት ነው፡፡ ከምግብ ባለፈ የምንጠጣው ቡናና ሻይ፣ አልፎም ለወፍጮ የሚውሉ እህሎች ላይም ይጨመራል፡፡

ከዚህም አልፎ ለምግብ መፈጨት፣ ለሆድ ሕመም፣ ለማቅለሽለሽ እና ለሌሎችም ከጤና ጋር የተገናኙ ጉዳዮች ፍቱን እንደሆነ በጤና ባለሙያዎች ይነገራል፡፡ ጸረ- ተህዋሲያን ባህሪ ስላለው ጀርሞችን የመግደል አቅም እንዳለው ሳይንስ ያስቀምጣል፡፡

ብቻ የምንበላው ወይም የምንጠጣው ምግብና መጠጥ ላይ በግብዓትነት የሚጨመር ቅመም ነው፡፡ በግብርናው ዘርፍ በዝንጅብል ቤተሰብ ይመደባል፡፡

አስተዳደጉም እርጥበት፣ ጥላ እና ለም አፈር በሚኖርበት አካባቢ በዘር የሚባዛ ነው፡፡ ከባህር ጠለል በላይ ከ1 ሺህ 500 እስከ 2 ሺህ 200 ሜትር ከፍታ ባላቸው እርጥበት አዘል አካባቢዎች እና በትላልቅ ዛፎች ስር ወይም በግቢ ውስጥ በቀላሉ ያድጋል፡፡

ነገር ግን ቀጥተኛ የፀሐይ ብርሃን ከሚበዛበት ይልቅ ጥላ ያለው እና እርጥበት አዘል አካባቢ ለዕድገት ይመቸዋል፡፡

ተክሉን በችግኝ ወይም ስር አሊያም በዘር መትከል ይቻላል፡፡ የተክሉ ትልቁ ቁመት 2 ሜትር ነው፡፡ የተክሉ ፍሬ ሙሉ በሙሉ ቀይ ሲሆንና ግንዱ መድረቅ ሲጀምር ነው የሚሰበሰበው፡፡ አንዴ ከተተከለ ለበርካታ ዓመታት ምርት የሚሰጥ ውጤታማ ተክል ነው፡፡ ተተክሎ ለምርት ለመድረስ ደግሞ ከሁለት እስከ ሶስት ዓመት ሊፈጅ ይችላል፡፡

ይህም በዓለም አቀፍ ገበያ ላይ እጅግ ተፈላጊው ቅመም አድርጎታል፡፡ በሀገራችን ኢትዮጵያም እንዲሁ ተፈላጊ ቅመም ነው ኮረሪማ፡፡ ዋጋውም ውድ ከሚባሉት ቀመሞች መካከል ይመደባል፡፡

በውጭ ሀገራት “የኢትዮጵያ ካርዳሞም” (Ethiopian Cardamom) ወይም “የኢትዮጵያ ኮራሪማ” በመባል ይታወቃል፡፡ በእርግጥ የኢትዮጵያው ከሌሎቹ የኮረሪማ ዓይነቶች ለየት እንደሚል ይነገራል፡፡ የኢትዮጵያ ስም የተሰጠው ኮረሪማ ግን በሀገራችን በስፋት የሚመረት የቅመም ዓይነት ነው፡፡

ከፍተኛ ዝናብና እርጥበት ባላቸው የደቡብ እና ደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ክፍል በብዛት ይመረታል፡፡ በተለይም በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል ካፋ፣ ቤንች ሸኮ፣ ሸካ፣ ዳውሮ፣ ኮንታ እና በምዕራብ ኦሞ አካባቢዎች ላይ ምርቱ በብዛት ይገኛል፡፡

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ደግሞ በጎፋ፣ ደቡብ ኦሞ፣ ጋሞ፣ ወላይታ፣ ባስኬቶ፣ ጌዴኦ ፣ ኣሪ እና ኮሬ ዞኖች ኮረሪማ ይመረታል፡፡ በሌሎቹም በማዕከላዊ ኢትዮጵያ፣ ኦሮሚያ ፣ አማራ፣ ጋምቤላ እና ሲዳማ ክልሎች እንዲሁ ምርቱ አለ፡፡

ታዲያ ይኸው ምርት ኢትዮጵያ ወደ ውጭ ከምትልካቸው ቅመማ ቅመሞች መካከል ዋነኛው ሲሆን ጥናቶች እንደሚያመለክቱት በዓመት በአማካይ 200 ሜትሪክ ቶን ኮረሪማ ወደ ውጭ ትልካለች፡፡

በኮረሪማ ምርት ለብቻው ምን ያህል ገቢ እንደተገኘ መረጃዎች ባይኖሩም የኢትዮጵያ ቡናና ሻይ ባለሥልጣን መረጃ እንደሚያመለክተው በ2018 ዓ.ም ቡናን ሳያካትት ከኮረሪማ፣ ቅርንፉድ፣ ዝንጅብል ከመሳሰሉ ቅመማ ቅመሞች ወጪ ንግድ 17 ሚሊየን ዶላር ገቢ ተገኝቷል፡፡

ኢትዮጵያ ኮረሪማን በስፋት ብታመርትም ከወጪ ንግድ ብዙ ገቢ ያለማግኘቷ ምክንያት ምርቱ በአብዛኛው ለሀገር ውስጥ ፍጆታ ስለሚውል መሆኑ ይጠቀሳል፡፡

ዘጋቢ፡ ኢያሱ ታዴዎስ