ቼልሲ አሌክስ ስኮትን ለማስፈረም ያለው ፍላጎት አሁንም ቀጥሏል

ቼልሲ አሌክስ ስኮትን ለማስፈረም ያለው ፍላጎት አሁንም ቀጥሏል

የምዕራብ ለንደኑ ክለብ ቼልሲ ባለፈው ክረምት ያቀረበው የዝውውር ጥያቄ ውድቅ ቢደረግበትም፣ የቦርንማውዙን አማካይ አሌክስ ስኮትን ለማስፈረም አሁንም ከፍተኛ ፍላጎት እንዳለው ተገልጿል።

የ23 ዓመቱ እንግሊዛዊ አማካይ በቦርንማውዝ ቤት ያለው ኮንትራት 18 ወራት ብቻ የቀሩት ሲሆን፤ ተጫዋቹ አዲስ ውል የመፈረም ምንም አይነት እቅድ የለውም።

ይህንን ተከትሎ ቼልሲዎች ለተጫዋቹ ፊርማ ከሌሎች ክለቦች ጋር ከባድ ፉክክር ሊገጥማቸው እንደሚችል ስጋት አድሮባቸዋል፤ በመሆኑም ዝውውሩን ለማጠናቀቅ እስከ መጪው ክረምት መጠበቅ ሊኖርባቸው እንደሚችል ያምናሉ።

ዘ አትሌቲክ እንደዘገበው፤ ቦርንማውዝ ለአሌክስ ስኮት የ100 ሚሊዮን ፓውንድ የዝውውር ዋጋ ቆርጦለታል።

ክለቡ በወቅቱ በፕሪሚየር ሊጉ የደረጃ ሰንጠረዥ ግርጌ አካባቢ የነበረ በመሆኑ፤ በጥር ወር የዝውውር መስኮት ተጫዋቹን የሚለቀው ከመውረድ ስጋት ነጻ መሆኑን ካረጋገጠ ብቻ እንደሆነ አቋም ይዞ ነበር።

አሁን ላይ ግን በሜዳ ላይ ያለው እውነታ ሙሉ በሙሉ ተቀይሯል።

ቦርንማውዝ ከወራጅ ቀጠናው ስጋት ወጥቶ በደረጃ ሰንጠረዡ ከቼልሲ በላይ (5ኛ ደረጃ ላይ) በመቀመጥ እየተፎካከረ ይገኛል።

ይህ አስደናቂ ግስጋሴ ቦርንማውዝ በውድድር ዓመቱ አጋማሽ ላይ ቁልፍ ተጫዋቹን አሳልፎ እንዲሰጥ ማሳመንን እጅግ ፈታኝ ያደርገዋል።

በተጨማሪም አሌክስ ስኮት በቅርቡ ባጋጠመው የጭን ጉዳት ምክንያት ከሜዳ ርቆ መቆየቱ ይታወሳል፤ ሆኖም ከጉዳቱ አገግሞ ወደ ጨዋታ እየተመለሰ ባለበት በዚህ ወቅት፤ ቼልሲዎች በጥር ወር ዝውውሩን ለመፈጸም የሚያደርጉት ጥረት ከፍተኛ ገንዘብ እና ትዕግስት የሚጠይቅ ሆኗል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ