“ትኩረትና እንክብካቤ ለሁሉም ሕፃናት” በሚል መሪ ቃል አለም አቀፉ የህፃናት ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተከበረ

“ትኩረትና እንክብካቤ ለሁሉም ሕፃናት” በሚል መሪ ቃል አለም አቀፉ የህፃናት ቀን በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ተከበረ

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አለም አቀፉ የህፃናት ቀን “ትኩረትና እንክብካቤ ለሁሉም ሕፃናት” በሚል መሪ ቃል በሳውላ ከተማ በድምቀት ተከብሯል።

በዕለቱ ከዞንና ከሪጂዮ ፖሊሲ ከተሞች በተውጣጡ ህጻናት የተሠሩ የፈጠራ ውጤቶች ውድድር ኤግዚቢሽን ተከፍቶ በክብር እንግዶችና ባለድርሻ አካላት ተጎብኝቷል።

ዓለም አቀፍ የሕፃናት ቀን በዓለም አቀፍ ደረጃ ለ37ኛ፣ በኢትዮጵያ ደግሞ ለ21ኛ ጊዜ “ትኩረትና እንክብካቤ ለሁሉም ሕፃናት” በሚል መሪ ቃል በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማህበራዊ ጉዳይ ቢሮ የፍትህ ክላስተር መቀመጫ በሆነችው ሳውላ ከተማ በልዩ ልዩ ዝግጅቶች በድምቀት አክብሯል።

በመድረኩ የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ያስተላለፉት የጎፋ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ በላይነህ ባህሩ እንዳሉት፤ ለህፃናት እንደዚህ ዓይነት ፕሮግራሞችን በማዘጋጀት የልምድ ልውውጥ እንዲያደርጉ ማድረግ ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አለው ብለዋል፡፡

አስተዳዳሪው በንግግራቸው የነገ ሀገር ተረካቢ ትውልዶችን ተንከባክበንና ሥነ-ምግባርን አላብሰን ማሳደግ እና ሀገር ወዳድ እንዲሆኑ ማድረግ የሁላችንም ኃላፊነት መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል በማለት ተናግረዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሴቶችና ማኅበራዊ ጉዳይ ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ አለምነሽ ደመቀ በዓሉን አስመልክቶ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ከበዓሉ አስቀድሞ በክልሉ በሚገኙ 12 ዞኖችና 3 ሪጂዮ ፖሊታን ከተሞች የሕፃናትን መብት፣ ጥበቃ፣ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማሳደግ ሰፊ ንቅናቄ መካሄዱን ገልጸዋል።

ንቅናቄዎቹ የሕፃናትን ትርጉም ያለው ተሳትፎ ማረጋገጥ፣ ምቹና ከጥቃት የፀዳ አካባቢ መፍጠር እንዲሁም ለተጋላጭ ሕፃናት አማራጭ ድጋፍና እንክብካቤ ማስፋፋት በሚሉ አራት ዋና ዋና ግቦች ላይ ያተኮረ እንደነበርም አስታውሰዋል።

በዚህም 1 ሚሊዮን 382 ሺህ 174 ሕፃናት በንቅናቄውና በበዓሉ ዝግጅት ላይ መሳተፋቸውን ጠቅሰው፤ ከ3 ሚሊዮን 815 ሺህ በላይ የማኅበረሰብ ክፍሎች በሕፃናት መብትና ጥበቃ ዙሪያ ግንዛቤ ተፈጥሮላቸዋል ብለዋል።

አያይዘውም 77 አዳዲስ የሕፃናት መብት ኮሚቴዎች መቋቋማቸውንና 281 ነባር ኮሚቴዎች መጠናከራቸውን ገልፀው፤ 2 ሺህ 341 ትምህርት ቤቶች ለሕፃናት ደህንነት የተጠበቀና ከጥቃት ነፃ የሆነ አካባቢ እንዲሆኑ ሥራዎች መከናወናቸውን አስረድተዋል።

ከማኅበረሰቡና ከግል ባለሀብቶች 25 ሚሊዮን ብር ለማሰባሰብ ታቅዶ 13 ሚሊዮን 870 ሺህ 639 ብር በማሰባሰብ 6 ሺህ 30 ተጋላጭ ሕፃናት የትምህርት ቁሳቁስ፣ የአልባሳትና የንጽህና መጠበቂያ ድጋፍ እንዲያገኙ መደረጉን ገልጸዋል።

በተጋላጭ ሕፃናት ድጋፍና እንክብካቤ ረገድም 12 ሕፃናት በሀገር ውስጥ ጉዲፈቻ፣ 50 በአደራ ቤተሰብ እንክብካቤ፣ 514 ጎዳና ላይ ውሎ አዳራቸውን ያደረጉ ሕፃናት ወደ ቤተሰቦቻቸው በመመለስና በማቀላቀል፣ 24 ሺህ 345 በስፖንሰርሺፕ፣ 89 ደግሞ በተቋጥሮ ዝምድና ድጋፍና እንክብካቤ ተጠቃሚ ሆነዋል ብለዋል።

በመድረኩ በክብር እንግድነት የተገኙት ‎የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት የፖለቲካና አቅም ግንባታ ዘርፍ ኃላፊ ቦጋለ ቦሻ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ ህፃናት የነገን ኢትዮጵያ ተስፋ የሚወስኑ በመሆናቸው ተገቢውን እንክብካቤና ጥበቃ ማድረግ እንደሚገባ ጠቁመዋል።

የክልሉ መንግስት በተሟላ አቅም ህዝቡን እያገለገለ ያለበት ወቅት መሆኑን የገለፁት ዶ/ር ቦጋለ፤ ህፃናት የሚያከናውኑት የፈጠራ ስራ ውጤታማ እንዲሆን በማድረግ ኢትዮጵያ የያዘችውን የዲጂታል ኢትዮጵያ 20-30 ራዕይ እውን ማድረግ እንደሚገባ አስረድተዋል።

የህፃናት ፓራለማ አፈ-ጉባኤ ህፃን ቢኒያም ትዕግስቱ እንዳለው፤ መንግስት የህፃናት መብትና ደህንነት ለማስጠበቅ እያደረገ ያለውን ተግባር አድንቆ እነዚህ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ጠይቋል።

በመጨረሻም የደቡብ ኢትዮጵያ ክልላዊ መንግስት ጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንት አቶ ቦጋለ ፈይሳ ተሳታፊ የነበሩ ወንዶችን፤ በሴቶች እና ህፃናት ላይ የሚደርሱ ጥቃቶችን በጋራ ለመከላከል ዘብ ለመቆም ቃል የማስገባት ስነ-ስርዓትና ለተሳታፊና በፈጠራ ስራ የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ የዕውቅና ምስክር ወረቀት እና የዋንጫና የቁሳቁስ ድጋፍ በማድረግ መድረኩ ተጠናቋል።

ዘጋቢ፡ አወል ከድር – ከሳውላ ጣቢያችን