በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች የጤና እክል የገጠማቸውን አካል ጉዳተኛ ህጻናት እና አሳዳጊ ወላጆችን የመደገፍ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ የልማት ድርጅት ገለፀ

በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች የጤና እክል የገጠማቸውን አካል ጉዳተኛ ህጻናት እና አሳዳጊ ወላጆችን የመደገፍ ስራ እየሰራ እንደሚገኝ የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ የልማት ድርጅት ገለፀ

አካል ጉዳተኛ ህጻናት በበኩላቸው የተሳሳቱ አመለካከቶችን በማረም እና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ረገድ ድርጅቱ እየሰራቸው ያሉ ተግባራት አበረታች በመሆናቸው ተጠናክረው ሊቀጥሉ እንደሚገባ ተናግረዋል።

የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ የልማት ድርጅት ስራ አስፈጻሚ ቦርድ ሰብሳቢ አቶ ብርሃኑ ጆርጅ በመክፈቻ ንግግራቸው እንዳሉት፤ ድርጅቱ በትምህርት፣ በጤና፣ በግብርና፣ በመንገድ ግንባታና በትራንስፖርት አገልግሎት ዘርፎች ለህብረተሰቡ ከፍተኛ የልማት አገልግሎት በመስጠት አኩሪ ታሪክ ማስመዝገብ ችሏል።

በከተማው ለሚገኙ 50 ለችግር የተጋለጡ አካል ጉዳተኞች እና ወላጆችን በመለየት 5 መቶ ሺ ብር ድጋፍ መደረጉን ተናግረዋል።

አካል ጉዳተኞች በኢኮኖሚ ራሳቸውን እንዲችሉ ከማድረግ ጎን ለጎን አኩል የመማር፣ የመስራትና የመወሰን መብታቸውን በማክበር በልማት ሂደት ውስጥ ንቁ ተሳታፊ እንዲሆኑ ለማድረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አቶ ብርሃኑ አስረድተዋል።

የስራ እድል እንዲያገኙ የሚሰጡ ስልጠናዎች የዛሬን ፍላጎት መሰረት ያደረጉ ብቻ ሳይሆን በዘላቂነት ሕይወታቸውን የሚቀይሩበትን አቅም የሚፈጥር ስለመሆኑም ጠቁመዋል።

የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ የልማት ድርጅት ስራ አስኪያጅ አቶ በቀለ ግርማ በበኩላቸው፤ ድርጅቱ የህዝቡን ሰፊ የመሰረተ ልማት ችግር በመፍታት በርካታ ስኬቶችን ማስመዝገብ ችሏል ብለዋል።

በተፈጥሮና በሰው ሰራሽ አደጋዎች የጤና እክል የገጠማቸው አካል ጉዳተኛ ህጻናት እና አሳዳጊ ወላጆችን የመደገፍ ስራ እየሰራ እንደሚገኝም ገልጸዋል።

የአቅም ማጎልበቻ እና የስራ እድል ፈጠራ ሐሳቦችን በተመለከተ የድርጅቱ ፕሮጀክትና ፕሮግራም ክፍል ኃላፊ አቶ በቀለ መንግስቱ ስልጠና የሰጡ ሲሆን አካል ጉዳተኞች እና ቤተሰቦቻቸውን የኢኮኖሚ አቅም በማሳደግ የተሻለ ሕይወት እንዲመሩ በትኩረት እየተሰራ ነው ብለዋል።

የድርጅቱን አቅም ማሳደግ ማህበረሰቡን ከማጠናከር ባሻገር አካል ጉዳተኞችን በመደገፍ የተሟላ ማህበረሰብ መገንባት ነውም ብለዋል።

የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ የልማት ድርጅት የማህበረሰባችን የጋራ ታሪክ በመሆኑ የዞኑ ተወላጆች፣ በጎ አድራጊዎች፣ የልማት አጋሮች እና መላው ማህበረሰብ ድርጅቱን በእውቀትና በገንዘብ እንዲደግፉም አቶ በቀለ ጥሪ አቅርበዋል።

ድርጅቱ የተለያዩ ችግሮች ቢገጥሙትም የሪፎርም ስራዎች በመስራት የውስጥ አቅሙ እንዲጠናከር ተደርጓል ያሉት ደግሞ የጉራጌ ህዝብ ራስ አገዝ የልማት ድርጅት የሚዲያ እና ህዝብ ግንኙነት ኃላፊ አቶ ወንድሙ ቅባቱ ናቸው።

በማህበረሰቡ የልማት ስራዎች ላይ ድጋፍ በማድረግ እና በቀጥታ ተሳታፊ በመሆን በርካታ ተግባራት እያከናወነ ይገኛልም ብለዋል።

አካል ጉዳተኛ ህጻናትና አሳዳጊ ወላጆች በሰጡት አስተያየት ድርጅቱ እያደረገላቸው ባለው ድጋፍ መደሰታቸውን ገልጸዋል።

በአካል ጉዳተኛ ህጻናት ላይ ያሉ የተሳሳቱ አመለካከቶችን በማረም ግንዛቤ በመፍጠር ወደ ትምህርት ገበታ እንዲመጡ በማድረግ እና አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ረገድ ድርጅቱ እየሰራቸው ያሉ ተግባራት አበረታች በመሆናቸው ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ ገልጸዋል።

ዘጋቢ፡ አስቻለው አማረ – ከወልቂጤ ጣቢያችን