ወጣቶች ባላቸው እውቀት፣ እምቅ ችሎታና አቅም በተሰማሩበት ስራ መስክ ጠንክረው ከሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ ተናገሩ

ወጣቶች ባላቸው እውቀት፣ እምቅ ችሎታና አቅም በተሰማሩበት ስራ መስክ ጠንክረው ከሰሩ ውጤታማ እንደሚሆኑ የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ ተናገሩ
‎
‎አለም አቀፍ የኤም ኤም ኤ Mixide Marshal Art (MMA) እና በኢትዮ ፋይት የፍልሚያ መድረክ አሸናፊ የሆነዉ ቢንያም ሽብሬ ወደ ዳዉሮ ዞን ሲገባ ደማቅ አቀባበል ተደረገለት፡፡
‎
ቢንያም ወደ ዞኑ ሲገባ ከፍተኛ የመንግስት አመራሮችን ጨምሮ በርካታ የዞኑ የማህበረሰብ ክፍሎች በተሽከርካሪዎች በማጀብ በደማቅ ሁኔታ ተቀብለውታል።
‎
‎በአቀባበል ስነ-ስርዓቱ ላይ ተገኝተው ንግግር ያደረጉት የዳውሮ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ዳዊት ገበየሁ፤ ሁነቱ ለዞኑ ታሪካዊ መሆኑን አንስተው የኢትዮጵያን ስምና ዝናን በዓለም መድረክ በማርሻል አርትና በሌሎች ተያያዥ የስፖርት ጥበቦች ያስጠራውን ይኸን ወጣት እንኳን ደህና መጣህ ብለዉታል።
‎
‎አቶ ዳዊት አክለውም፤ ከሜዲስን እስከ ህክምና፣ ከሳይንስ እስከ ፍልስፍና፣ ከጦር ሜዳ እስከ ስፖርት ሜዳ ለሀገራችን በርካታ ጀግኖችን የዳውሮ ምድር ወልዳ መስጠቷን ተናግረው አሁን እያንዳንዱ ወጣት የቢንያምን የስኬት ጉዞ መከተል አለበት ሲሉም አሳስበዋል።
‎
‎ወጣቱ ጥበብና ጉልበቱን የሚጠቀም ከሆነ ሀገር የመለወጥ ትልቅ አቅም ስላለው በተሰማራበት መስክ ሁሉ መትጋት እንዳለበት አቶ ዳዊት አጽንኦት ሰጥተዋል።
‎
‎ወደ ቤተሰብ አካባቢው የመጣው ቢንያምም በዳውሮ ማህበረሰብ የተደረገለት ደማቅ አቀባበል ካሰበው በላይ እንደሆነ ተናግሮ በሁኔታው እጅግ መደሰቱን በመግለፅ ለዚህም አመስግኗል።
‎
‎ቢንያም ስፖርት ሠላም እንደሆነ ለወጣቶቹ ተናግሮ፣ በቀጣይ ይኸን የኤም ኤም ኤ የስፖርት ጥበብ በዞኑ የሚገኙትን ወጣቶች በማሰልጠን ውጤታማ ለማያደርግ ቃል ገብቷል።
‎
‎አቀባበል ካዳረጉለት የማህረሰብ ክፍሎች አንዳንዶቹ በሰጡት አስተያየት፤ ቢንያም በማርሻል አርትና ተጓዳኝ የስፖርት ጥበብ ስራዎች ጠንክሮ በመስራት ከትውልድ አካባቢው አልፎ የኢትዮጵያን ስም በከፍታ ያስጠራ በመሆኑ እጅግ ተደስተናል በማለት ለዚህም የሚመጥነውን አቀባበል አድርገናል ሲሉ ተናግረዋል።
‎
‎በአቀባበል ስነ-ስርአቱ ላይ በዳውሮ እጅግ የሚታወቀው የቅቤ ስጦታ ለቢንያም ተሰጥቶታል።

ዘገባው የዋካ ጣቢያችን ነው