ማንችስተር ከቶተንሃም ተጠባቂው ፍልሚያ ሲያደርጉ፤ አርሰናል እና ቸልሲ ድልን ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባሉ
በእንግሊዝ ፕሪሚየር ሊግ የ6ኛ ሳምንት መርሐ ግብር ዛሬ ማራኪ እና ትኩረት የሚስቡ ስድስት ጨዋታዎች ይደረጋሉ።
ሊጉ ለሀገራት ጨዋታዎች ከመቋረጡ በፊት ነጥብ ጥለው የነበሩ ትልልቅ ክለቦች ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ ተብሎ ይጠበቃል።
የዕለቱ ዋነኛ ተጠባቂ መርሃ ግብር ምሽት 1 ሰዓት 30 በኦልድትራፎርድ ሜዳ በአሰልጣኝ ማይክል ካሪክ የሚመራው ማንችስተር ዩናይትድ ከ ቶተንሃም ሆትስፐር ጋር የሚያደርጉት ወሳኝ ጨዋታ ነው።
በአዲሱ የውድድር ዓመት ጅማሮ ላይ ከባድ ፈተና ውስጥ ያሉት ቀያይ ሰይጣኖቹ እስካሁን ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች ማሸነፍ የቻለው በአንዱ ብቻ ነው። በሁለቱ ሽንፈት ያስተናገዱ ሲሆን፣ በሁለቱ ደግሞ አቻ ተለያይተዋል።
ከተከታታይ ሦስት ድል አልባ ጉዞዎች በኋላ በሜዳቸው የመጀመሪያውን ሦስት ነጥብ ለማግኘት ይፋለማሉ።
በተመሳሳይ በአሰልጣኝ ሮቤርቶ ዲዘርቢ የሚመራው የሰሜን ለንደኑ ክለብ ቶተንሃም ሆትስፐርም አስቸጋሪ ጅማሮ አጋጥሞታል።
እስካሁን ካደረጓቸው አምስት ጨዋታዎች በሶስቱ ተሸንፎ በሁለቱ አቻ በመለያየት የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ፍለጋ ወደ ሜዳ ይገባል።
ሁለቱ ቡድኖች በሁሉም ውድድሮች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች ቶተንሃም በሶስቱ በማሸነፍ የበላይነት ሲኖረው፣ ዩናይትድ አንዱን አሸንፎ በቀሪው አቻ ተለያይተዋል።
ከዚህ ጨዋታ አስቀድሞ ቀን 8 ሰዓት 30 ላይ አርሰናል በሜዳው ኢምሬትስ ከሊድስ ዩናይትድ ጋር ይጫወታል።
ሊጉ ለሀገራት ጨዋታ ከመቋረጡ አስቀድሞ በብራይተን ያልተጠበቀ ሽንፈት ያስተናገደው አርሰናል፣ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ወደ ሜዳ ይገባል።
መድፈኞቹ ማሸነፍ ከቻሉ ነጥባቸውን ወደ 15 ከፍ በማድረግ የሊጉ መሪ ማንችስተር ሲቲ እሁድ ጨዋታውን እስከሚያደርግ ድረስ በነጥብ የሚስተካከሉ ይሆናል።
ተጋጣሚያቸው ሊድስ ዩናይትድ በበኩሉ በሊጉ እስካሁን አንድም ጨዋታ ካልተሸነፉ ቡድኖች አንዱ ሲሆን፣ ሁለቱን አሸንፎ በሶስቱ አቻ በመለያየት የያዘውን ያለመሸነፍ ጉዞ ለማስቀጠል ይፋለማል።
ይሁን እንጂ ሁለቱ ቡድኖች እርስ በርስ ካደረጓቸው ያለፉት አምስት ጨዋታዎች አርሰናል አምስቱንም በማሸነፍ ፍጹም የበላይነት አለው።
አመሻሽ 11 ሰዓት ላይ ከሚደረጉ ተጠባቂ ጨዋታዎች መካከል ቸልሲ በሜዳው ስታምፎርድ ብሪጅ ቦርንማውዝን የሚያስተናግድበት ጨዋታ ይጠቀሳል።
ባለፉት ሶስት ተከታታይ የሊጉ ጨዋታዎች ድል ያልቀናቸው ሰማያዊዎቹ አሁን ላይ ወደ አሸናፊነት ለመመለስ ጠንካራ ፉክክር ያደርጋሉ።
ተጋጣሚው ቦርንማውዝም የውድድር ዓመቱን የመጀመሪያ ድል ለማግኘት ጥረት የሚያደርግበት ከባድ ጨዋታ ይጠብቀዋል።
አስቶንቪላ ከ ብሬንትፎርድ (በቪላ ፓርክ)፣ ኢፕስዊች ታውን ከ ፉልሃም (በፖርትማን ሮድ) እንዲሁም ሰንደርላንድ ከ ብራይተን (በስታዲየም ኦፍ ላይት) በተመሳሳይ 11 ሰዓት ላይ የሚገናኙበት ሌሎች የዛሬ መርሐግብሮች ናቸው።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የዘመኑ ታላቁ ፍጻሜ
የሜሲ ታሪካዊ የስንብት ምሽት በቦነስ አይረስ
ከ29 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙት ኢትዮጵያ እና ሴኔጋል