የዘመኑ ታላቁ ፍጻሜ
የእግር ኳሱ ንጉስ ሊዮኔል ሜሲ በአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን ማልያ ያደረገው የመጨረሻ ጨዋታ በታላቅ ስሜት፣ በእንባ እና በድል ታጅቦ ተጠናቋል።
በኤል ሞኑሜንታል ስታዲየም የተካሄደው ይህ ታሪካዊ የስንብት ቀን አጠቃላይ አርጀንቲናን በእንባ ያራጨ ነበር።
ዕለቱ በአርጀንቲና እግር ኳስ ታሪክ ውስጥ የማይረሳ፣ በታላቅ ስሜት የተሞላ እና የሀገሪቱን ሕዝብ በደስታና በሐዘን ስሜት ያዋሃደ ታሪካዊ ቀን ሆኖ አልፏል።
የ8 ጊዜ የባሎንዲኦር አሸናፊው ሊዮኔል መሲ በአርጀንቲና ብሔራዊ ቡድን (አልቢሴሌስተ) ማልያ ከቤኒን ጋር ያደረገውን የመጨረሻ ጨዋታ 3ለ0 በማሸነፍ በድል አድራጊነት አጠናቋል።
ቤኒንን ከፍ ያለ ብቃት ባሳየችበት ጨዋታ 3 ለ 0 በሆነ ውጤት ባሸነፈበት በዚህ ምሽት፣ ሊዮ አንድ ጎል ከመቆጠሩም በላይ ሁለት ግብ የሆኑ ግሩም ኳሶችን አመቻችቶ በማቀበል የምሽቱ ኮከብ ሆኗል።
የዕለቱ መርሃ ግብር ከቀኑ ጀምሮ በከፍተኛ ስሜት የታጀበ ነበር።
የአርጀንቲናዊያን ቴሌቪዥኖች የሊዮን የመጨረሻ ቀን ጉዞ ማሰራጨት ሲጀምሩ መላው ሀገር በሐዘንና በኩራት ስሜት ተውጧል። መሲ ከኢሴይዛ የልምምድ ማዕከል ወደ ሞኑሜንታል ስታዲየም በሚወስደው አውቶቡስ ላይ በነበረበት ሰዓት የመጀመሪያ እንባዎቹ አምልጠውታል።
በመቶ ሺዎች የሚቆጠሩ አርጀንቲናዊያን በጎዳናዎች ላይ በመሰለፍ የፍቅርና የምስጋና መግለጫዎችን ሰጥተውታል።
በሞኑሜንታል ስታዲየም ከ 85 ሺህ በላይ ተመልካቾች፣ ሚስቱ አንቶኔላ፣ ሦስቱ ልጆቹ እንዲሁም እናቱ ሴሊያ በስታዲየም በመገኘት ሽኝቱን አድምቀውለታል።
የፎክላንድ ጦርነት አርበኛ በሆነው ፋቢዮ ሳንታና በተቀኘው የብሔራዊ መዝሙር ወቅት መሲ በደረሰበት ከፍተኛ ስሜት የተነሳ መዝሙሩን መቀጠል አቅቶት ዝምታን መርጧል።
ሊዮ እንባውን ለመቆጣጠር ቢሞክርም፣ መላው የአርጀንቲና ሕዝብ ግን አልቻለም፤ መላው ሀገር በለቅሶና በሀዘን ስሜት ተሞልቶ ነበር።
ጨዋታው ሲጀመርም ሆነ ሲጠናቀቅ ሊዮኔል መሲ የሜዳው ንጉሥ ሆኖ ቆይቷል። ሙሉውን 90 ደቂቃ በመጫወት ያስመዘገበው ግሩም ብቃት፣ «ይህ ተጫዋች አሁንም ለአልቢሴሌስተ ብዙ ማበርከት የሚችለው አቅም አለው» የሚል ግርምት ለተመልካቹ ጥሎ አልፏል።
ጨዋታው በ3-0 አሸናፊነት ሲጠናቀቅ አርጀንቲና በድጋሚ እንባ አነባች፤ ምክንያቱም ከአሁን በኋላ ሊዮን በብሔራዊ ቡድን ማልያ ፈጽሞ ማየት እንደማትችል አውቃለችና።
ጨዋታው ሲያበቃ መሲ ለአድናቂዎቹ ያደረገው ንግግር መላውን ሀገር አንገበገበው፡-
«እርግጠኛ ነኝ ይህ በህይወቴ ውስጥ በጣም አሳዛኝ ቀን ነው፣ እናንተንም ሁላችሁን በእጅጉ እናፍቃችኋለሁ» ነበር ያለው።
በዚህ ልብን በሚነካ ንግግር መላውን ሕዝብ በእንባ ያራሰው ሊዮ፣ በሞኑሜንታል ስታዲየም የመጨረሻውን የድየክብር እጅ ሰላምታ በመስጠት ከብሔራዊ ቡድን ጓደኞቹና ከሕዝቡ ጋር ፍጹም ስንብት አድርጓል።
ሊዮኔል ሜሲ በአርጄንቲና ከዛች ከትንሿ መንደር ሮዛሪዮ ተነስቶ በመላው ዓለም የስፖርት ታሪክ የሰጠው አንዳችም የማይተካ ውለታ የዘላለም ትውስታ ሆኖ ይኖራል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
የሜሲ ታሪካዊ የስንብት ምሽት በቦነስ አይረስ
ከ29 ዓመታት በኋላ ለመጀመሪያ ጊዜ የሚገናኙት ኢትዮጵያ እና ሴኔጋል
ሳዲዮ ማኔ በትውልድ መንደሩ ባምባሊ 20 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ጀመረ