ደመራ እና መስቀል በዩኔስኮ

ደመራ እና መስቀል በዩኔስኮ

ኢትዮጵያ በተፈጥሮም ሆነ በሰው ሰራሽ ቅርሶች የታደለች ናት፡፡ ከዚህም መነሻ የዓለም የቱሪዝም የስበት ማዕከል ሆናለች፡፡ የውጭ ሀገር ጎብኚዎች ፍሰትም ከዓመት እስከ ዓመት እያሻቀበ ነው፡፡

በዚህም ምክንያት የተባበሩት መንግስታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባህል ድርጅት (UNESCO) ዓይኑን ኢትዮጵያ ላይ አሳርፏል ማለት ይቻላል፡፡

ዩኔስኮ ወደ 12 የሚጠጉ ተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ የኢትዮጵያ ቅርሶችን በልዩነት መዝግቧቸዋል፡፡ ይህም የኢትዮጵያን የተፈጥሮ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ባለጠግነት የሚያሳይ ነው፡፡

ከእነዚህም ቅርሶች መካከል ሰሜን ብሔራዊ ፓርክ፣ የላሊበላ ውቅር አብያተክርስቲያናት፣ የፋሲል ግንብ፣ የአክሱም ሐውልት፣ የታችኛው አዋሽ ሸለቆ፣ የጢያ ትክል ድንጋይ፣ የታችኛው የኦሞ ሸለቆ፣ የሐረር ጀጎል ግንብ እና የኮንሶ አስደናቂ ባህላዊ መልከዓ ምድር ይጠቀሳሉ፡፡

የሚገርመው ግን ኢትዮጵያ በተፈጥሯዊ እና ሰው ሰራሽ ቅርሶች ብቻ የተገደበች አይደለም፡፡ እንደ ዩኔስኮ ያሉ ዓለም አቀፍ ተቋማት የማይዳሰሱ ቅርሶቿንም በመመዝገብ ሀገራችን የቅርሶች መናኸሪያ መሆኗን መስክረዋል፡፡

ከማይዳሰሱ ቅርሶቿ መካከል ደግሞ የኢትዮጵያ መስቀል እና ደመራ፣ የሲዳማ ፊቼ ጫምባላላ፣ የገዳ ስርዓት እና የጥምቀት በዓል ይገኙበታል፡፡ እነዚህ የማይዳሰሱ ቅርሶች ኢትዮጵያ በሕዝቦቿ መካከል ጥብቅ የሆነ ትስስር እንዳለ ማሳያ ናቸው፡፡

ኢትዮጵያ ቀድሞ በዩኔስኮ ከተመዘገቡ የሚዳሰሱ ቅርሶቿ ወዲህ ለመጀመሪያ ጊዜ በማይዳሰስ ቅርስነት ያስመዘገበችው የመስቀል ደመራ በዓልን ነው፡፡ የመስቀል ደመራ በዓል በመስከረም ወር 2008 ዓ.ም ነበር በዩኔስኮ መዝገብ ላይ በማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበው፡፡

ዩኔስኮ በይፋዊ ድረ ገጹ ላይ እንዳሰፈረው በዓሉ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን በየዓመቱ መስከረም 16 እና 17 በድምቀት ይከበራል፡፡ የበዓሉ አከባበር በአዲስ አበባ በራሱ በበዓሉ በተሰየመው መስቀል አደባባይ በደመራ ስነ-ስርዓት እንደሚጀመርም ያትታል፡፡

በደመራው ስነ-ስርዓት ወቅት ደመራውን የማብራት መርሃ ግብር ከመከናወኑ በፊት የዝማሬ፣ ቅዳሴ እና ሌሎች ሁነቶች ይከናወናሉ፡፡ ከዚያም በስተመጨረሻ ፓትሪያርኩ ደመራው ላይ እሳት ይለኩሱና ደመራ የማብራት ስነ-ስርዓት ይከናወናል፡፡

ይህንንም ስነ-ስርዓት የእምነቱ ተከታዮች፣ የሀገር ውስጥና የውጭ ጎብኚዎች ይታደማሉ፡፡ ይኸው የደመራ ስነ-ስርዓት እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን፣ የመስቀል በዓል የሚከበርበትን መስከረም 17 ቀን አስታክኮ መስከረም 16 ቀን በኃይማኖታዊ ክዋኔዎች ታጅቦ የሚከበር በመሆኑ ትልቅ ትኩረት የሚሰጠው ነው፡፡ ስነ-ስርዓቱ ባማረ መልኩ ስለሚከናወን የጎብኚዎችን ቀልብ መሳብ ብቻ ሳይሆን ዩኔስኮ ላይ እንዲሰፍር ምክንያት ሆኗል፡፡

የዘንድሮ ደመራ እና መስቀል በዓል ሲከበርም በዩኔስኮ ከተመዘገበ 10ኛ ዓመቱ በሚገኝበት ወቅት ነው፡፡ በዓሉ በመመዝገቡ ለኢትዮጵያ በተለይም ዓለም አቀፍ እውቅና ከማግኘቱም በላይ የቱሪዝም ፍሰቱ እንዲያሻቅብ አድርጓል፡፡

በኢያሱ ታዴዎስ