የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው

የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ ነው

የግብርና ምርታማነትን በማሳደግ የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ ገለፀዋል።

በጉራጌ ዞን ምሁር አክሊል ወረዳ በክላስተር እየለሙ ያሉ የጤፍ፣ የስንዴ፣ የአቮካዶና ሌሎች የቅመማ ቅመም ምርቶች የመስክ ምልከታ ተካሄዷል።

የጉራጌ ዞን ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና መምሪያ ኃላፊ አቶ አበራ ወንድሙ በመስክ ምልከታው ወቅት እንደገለፁት፤ በዞኑ በዘንድሮ አመት ከ178 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በበቆሎ፣ በጤፍ፣ በስንዴ፣ በባቄላና በገብስ እንዲሁም በሌሎች ሰብሎች መሸፈኑን እና ከ10 ሚሊዮን ኩንታል በላይ ምርት ይገኛል ተብሎ እንደሚጠበቅ ገልፀዋል።

በምሁር አክሊል ወረዳ በኩታ ገጠም እየለሙ ያሉት የስንዴና የጤፍ ማሳዎች በተሞክሮነት የሚወሰዱ ስለመሆናቸው አቶ አበራ አንስተዋል።

በተለይም የግብርና ምርታማነትን በማሳደግና የአርሶ አደሩን የምግብ ዋስትና ለማረጋገጥ በትኩረት እየተሰራ መሆኑን ጠቁመው፤ ወቅቱ ዝናባማ በመሆኑ አርሶ አደሩ የደረሱ ሰብሎች መሰብሰብ ይጠበቅበታል ሲሉም አሳስበዋል።

የጉራጌ ዞን ብልፅግና ፖርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት አቅም ግንባታና የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ ደሳለኝ ፈቀደ በበኩላቸው፤ በወረዳው በመኸር ወቅት እየለሙ ያሉ የጤፍ፣ የስንዴና የጓሮ አትክል ማሳዎች ውጤታማ መሆናቸውን አውስተዋል።

በዞኑ የግብርና ሥራ ምርታማነት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ያወሱት አቶ ደሳለኝ፤ ይህንንም ተግባር አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባ አስረድተዋል።

ወጣቶች ያላቸውን እምቅ አቅም ተጠቅመው ያልታረሱ መሬቶችን አልምተው እንዲጠቀሙ እና በግብርናው ዘርፍ ውጤታማ እንዲሆኑ ለማስቻል አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚደረግም አመላክተዋል።

የምሁር አክሊል ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ መኑር ጀማል እንዳሉት፤ በወረዳው  በጤፍ፣ በገብስ፣ በኑግ እና በሌሎች ሰብሎች ከ9 ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ ለማልማት ታቅዶ ከ8 ሺህ ሄክታር በላይ መልማቱን አስታውቀዋል።

ግንዛቤ ከመፍጠር ጀምሮ አርሶ አደሩን በመደገፍ የማዳበርያና የምርጥ ዘር ግብዓት አቅርቦት በወቅቱ ማዳረስ መቻሉንም ገልጸዋል።

ወጣት አለማየሁ ማዘዝ እና ታደሰ ናማጋ የስንዴ ሰብል በኩታ ገጠም መዝራታቸውን እና የወረዳው መንግስት የሚያደርገው ድጋፍና ክትትል አበረታች በመሆኑ በቀጣይም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አንስተዋል።

ዘጋቢ፡ እርካብነሽ ወ/ማርቆስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን