የማንችስተር ዩናይትድ ባለቤቶች ክለቡን ለመሸጥ መወሰናቸው ተገለጸ
የእንግሊዙ ታላቅ ክለብ ማንችስተር ዩናይትድ ባለቤቶች የሆኑት የግሌዘር ቤተሰቦች ክለቡን ሙሉ በሙሉ ለመሸጥ በሚስጥር ሂደት መጀመራቸው ተሰምቷል።
የእግር ኳስ ፋይናንስ ባለሙያው እስቴፋን ቦርሰን በቶክ ስፖርት የሬዲዮ እና ቪዲዮ ፕሮግራም ላይ እንደገለጹት፣ አሜሪካዊያኑ ግሌዘር ቤተሰቦች ማንችስተር ዩናይትድን ለሽያጭ አቅርበውታል።
ግሌዘሮች እ.ኤ.አ. በ2022 ክለቡን ለሽያጭ አቅርበው የነበረ ቢሆንም፣ ሂደቱ የተጠናቀቀው ሰር ጂም ራትክሊፍ የ27.7 በመቶ አነስተኛ ድርሻ በመግዛታቸው ብቻ ነበር።
በየካቲት 2024 የራትክሊፍ የድርሻ ግዢ ሙሉ በሙሉ መጽደቁ ይታወሳል።
እንደ እስቴፋን ቦርሰን ገለጻ፣ የዚህኛው የሽያጭ ሂደት ቀደም ሲል ከነበረው በተለየ መልኩ ለህዝብ ይፋ ሳይደረግ በጥንቃቄ እየተካሄደ ይገኛል።
“በእግር ኳሱ ዓለም ውስጥ ከሚገኝ ከፍተኛ ባለስልጣን እንደተረዳሁት ክለቡን ለመሸጥ የተቀረጸ ሂደት አለ፤ክለቡ ለሽያጭም ቀርቧል ” ያሉት ቦርሰን፣ “ባለፈው ጊዜ ሂደቱን ይፋ ማድረጋቸው መጨረሻው የሚያስኝ አልነበረም። ስለዚህ በዚህኛው ጊዜ በይፋ ሳያወጡት በተለየ መንገድ እየሞከሩ ሊሆን ይችላል፤ ነገር ግን አሁን ክለቡን የሚለቁበት ትክክለኛ ጊዜ መሆኑን አምነውበታል” ብለዋል።
ባለሙያው አክለው እንዳሉት ግሌዘሮች በክለቡ የሽያጭ ዋጋ ላይ አይደራደሩም። ክለቡን መሸጥ የሚችሉት ጥያቄያቸው ሲሟላ ብቻ ሲሆን፣ ማንችስተር ዩናይትድን ለመሸጥ የጠየቁት የገንዘብ መጠን 5 ቢሊዮን ፓውንድ አካባቢ እንደሆነ ተጠቁሟል።
ግሌዘሮች ከፍተኛ ዋጋ የጠየቁበት ዋናው ምክንያት የክለቡ ብራንድ ባለው አስተማማኝ ጥንካሬ እንደሆነ ቦርሰን ያብራራሉ።
“ክለቡ በሜዳ ላይ ውጤታማ ባይሆን እንኳ የንግድ እንቅስቃሴውን እና ገቢ የማስገኘት አቅሙን የሚያሳጣው ነገር የለም የሚል ጽኑ እምነታቸው አላቸው ” ሲሉ ቦርሰን ተናግረዋል።
ይህንን እውነታ የሚያጠናክረው ክለቡ በቅርቡ ይፋ ያደረገው የፋይናንስ ሪፖርት ነው። ማንችስተር ዩናይትድ ባለፈው የውድድር ዘመን በአውሮፓ አህጉራዊ ውድድሮች ባይሳተፍም፣ 677.6 ሚሊዮን ፓውንድ ክብረወሰን የሆነ የተጣራ ገቢ ማግኘቱን ማሳወቁ አይዘነጋም።
በተጨማሪም በሰር ጂም ራትክሊፍ አነሳሽነት ከተደረጉት የሰራተኞች እና የካፒታል ወጪ ቅነሳዎች በኋላ፣ ክለቡ ባለፈው ዓመት ከነበረበት የ18.4 ሚሊዮን ፓውንድ ኪሳራ አሁን 22.6 ሚሊዮን ፓውንድ የክወና ትርፍ ማስመዝገብ ችሏል።
የግሌዘር ቤተሰብ የማንችስተር ዩናይትድ ባለቤትነት ጉዞ የጀመረው እ.ኤ.አ. በ2003 ማልኮም ግሌዘር የመጀመሪያውን ድርሻ በመግዛት ነበር።
በግንቦት 2005 ደግሞ በብድር በተደገፈ ግዢ ሙሉ ድርሻውን ተረከቡ።
ከዚህ ግዢ በፊት ምንም ዓይነት ዕዳ የሌለበት ክለብ የነበረው ዩናይትድ፣ ከዚያ ጊዜ ጀምሮ በትልቅ የዕዳ ጫና ውስጥ እንዲወድቅ መደረጉ ደጋፊዎችን ሲያበሳጭ ቆይቷል።
ከቀናት በፊት ከአስተን ቪላ ጋር በተደረገው ጨዋታም የዩናይት ደጋፊዎች በኦልድ ትራፎርድ ስታዲየም “Stretford End” በተባለው የስታዲየሙ ክፍል አረንጓዴ እና ቢጫ ፊኛዎችን (የክለቡ የቀደመ ታሪካዊ ቀለም እና የተቃውሞ ምልክት) በመልቀቅ ተቃውሟቸውን አሳይተዋል።
ደጋፊዎቹ በመጨረሻም “አዲስ ስታዲየም አንፈልግም፤ የምንፈልገው ባለቤቶቹ እንዲወጡልን ነው” የሚል ትልቅ ባነር በማውጣት ተቃውሟቸውን አጠናክረው ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ማንችስተር ዩናይትድ ሚካኤል ካርሪክን በሞሪሲዮ ፖቼቲኖ ለመተካት ከጫፍ መድረሱ ተገለፀ
ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ያደነቋቸው ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ወደ ዩናይትድ ሊመጡ?
51 ቀይ ካርዶች የተመዘዙበት ጨዋታ