ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ያደነቋቸው ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ወደ ዩናይትድ ሊመጡ?

ሰር አሌክስ ፈርጉሰን ያደነቋቸው ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ወደ ዩናይትድ ሊመጡ?

ማንቸስተር ዩናይትድ የ2026/27 የውድድር ዘመንን በከፍተኛ ውድቀት በመጀመሩና በገጠመው የውጤት ቀውስ ምክንያት አሰልጣኝ ሚካኤል ካሪክን ከኃላፊነታቸው ለማሰናበት በዝግጅት ላይ ይገኛል።

ክለቡ በአሁኑ ወቅት ወደ ታችኛው የሊግ ዕርከን የመውረድ ስጋት ውስጥ የሚገኝ ሲሆን፣ የክለቡ አመራሮች አዲስ አሰልጣኝ ለመቅጠር የሚያደርጉት ፍለጋ ያልተጠበቀ አቅጣጫ ይዟል።

ቀደም ሲል የቀድሞው የኒውካስል አሰልጣኝ ኤዲ ሃው እና የቀድሞው የጀርመን ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኝ ጁሊያን ናጌልስማን ዋና እጩዎች ተደርገው ቢገለጹም፣ በአሁኑ ወቅት ግን የአሜሪካ ብሔራዊ ቡድን አሰልጣኙ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ ማንቸስተር ዩናይትድን ለመረከብ በግንባር ቀደምትነት ላይ እንደሚገኙ ተዘግቧል።

ይህ የፖቼቲኖ ስም ከማንቸስተር ዩናይትድ ጋር መያያዝ ግን ለቀያይ ሰይጣኖች ደጋፊዎች አዲስ አይደለም፤ ይልቁንም ረጅም ዘመናት የቆየ “ያልተሳካ የፍቅር ታሪክ” ነው።

ከዚህ በፊት እ.ኤ.አ በ2021 ኦሌ ጉናር ሶልሻየር ከዩናይትድ ሀላፊነት ከተሰናበተ በኋላ ፖቼቲኖ (በወቅቱ የፒኤስጂ አሰልጣኝ ነበሩ) ዩናይትድን ለመረከብ ከፍተኛ ፍላጎት የነበራቸው ሲሆን፣ የክለቡ ስኬታማው አሰልጣኝ ሰር አሌክስ ፈርጉሰንም አርጀንቲናዊውን አሰልጣኝ ወደ ኦልድ ትራፎርድ ለማምጣት በንቃት ተንቀሳቅሰው ነበር።

ፈርጉሰን እና ፖቼቲኖ በፕሪሚየር ሊጉ በታሪክ የተገናኙት አንድ ጊዜ ብቻ ነው እሱም በፈረንጆቹ 2013 ዩናይትድ ሳውዝሃምፕተንን 2-1 ባሸነፈበት ጨዋታ።

በወቅቱ ፈርጉሰን ቡድናቸው በፖቼቲኖው ሳውዝሃምፕተን ሙሉ በሙሉ ብልጫ ተወስዶበት እንደነበር በግልጽ አምነው ነበር።

በኋላም ፖቼቲኖ ቶተንሃምን ይዘው በቻምፒዮንስ ሊጉ ለፍፃሜ ሲደርሱና ለሊጉ ዋንጫ ሲፎካከሩ ፈርጉሰን አድናቆታቸውን አልሸሸጉም።

እ.ኤ.አ በ2016 ፈርጉሰን ስለ ፖቼቲኖ ሲናገሩ“አሰልጣኙ ድንቅ ነው። ቡድኑ የሚጫወትበት መንገድ ለሰራው ስራ ታላቅ ምስክር ነው። ከሁሉም በላይ ደግሞ የወጣት እና እንግሊዛውያን ተጫዋቾችን አቅም የመጠቀም ጥበቡ የሚደነቅ ነው፤ ወጣቶች ላይ እምነት ከጣልክ በጭራሽ አያሳፍሩህም“ ብለው ነበር።

በተጨማሪም የብሪታንያው የፓርላማ አባል ዴቪድ ላሚ እ.ኤ.አ በ2016 በሰጡት አስተያየት፣ ፈርጉሰን በግል ጨዋታቸው ወቅት “በእኔ እይታ በፕሪሚየር ሊጉ ውስጥ ምርጡ አሰልጣኝ እሱ (ፖቼቲኖ) ነው“ ብለው እንደነገሯቸው ይፋ አድርገው ነበር።

እ.ኤ.አ በግንቦት 2016 ሁለቱ አሰልጣኞች በጋራ ምሳ የተመገቡ ሲሆን፣ ፖቼቲኖ ‘Brave New World’ በተሰኘው መጽሐፋቸው ላይ ያንን አጋጣሚ ሲያስታውሱ “ከእሱ ጋር ያሳለፍኳቸውን ሰዓታት እያንዳንዱን ዝርዝር ሁኔታ አሁንም አስታውሰዋለሁ። ለኔ ሕልሜ እውን የሆነበት ቅጽበት ነበር፤ የፈርጉሰን ግርማ ሞገስና ጠንካራ ስብዕና ማንም ሰውን የሚማርክ ነው“ ሲሉም ፅፈውታል።

ምንም እንኳን ሰር አሌክስ ፈርጉሰን በአሁኑ ወቅት በማንችስተር ዩናይትድ በደመወዝ ከሚሠሩ ሠራተኞች መካከል ባይሆኑም፣ የክለቡ የክብር ዳይሬክተር በመሆን እያገለገሉ ይገኛሉ።

የክለቡ አመራሮች አዲስ አሰልጣኝ ከመቅጠራቸው በፊት የፈርጉሰንን ምክር የሚቀበሉ ከሆነ፣ ማውሪሲዮ ፖቼቲኖ በስኮትላንዳዊው አሰልጣኝ ዘንድ ትልቅ አመኔታ ያላቸው መሆኑ ለአርጀንቲናዊው አሰልጣኝ ወደ ኦልድ ትራፎርድ ማምራት ትልቅ ድጋፍ ይሆንላቸዋል ተብሎ ይጠበቃል።

ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ