በክልሉ የጸረ ሙስና ትግልን በማጠናከር ፍትሐዊ የሐብት ተጠቃሚነትን ለማረጋገጠ እየሠራ መሆኑን የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ገለጸ
“ስውር ትስስሮችን በማጋለጥ የሙስና ወለድ ወንጀሎችን እናጋልጥ” በሚል መሪ ቃል በክልሉ በሁሉም አካባቢዎች የዘንድሮው ጸረ ሙስና ቀን እንደሚከበር ታውቋል።
ቀኑን አስመልክቶ የክልሉ ሥነ ምግባርና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አለማየሁ ባውዲ መግለጫ ሰጥተዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሥነ ምግባር እና ጸረ ሙስና ኮሚሽን ኮሚሽነር አቶ አለማየሁ ባውዲ የዘንድሮውን የጸረ ሙስና ቀንን አስመልክቶ በሰጡት መግለጫ፤ የመደመር መንግሥት ለመሥራት ለሕዝቡ ከገባው ቃል አንዱ ሙስናና ብልሹ አሠራርን በመታገል ፍትሐዊ የሐብት ተጠቃሚነትን ማረጋገጥ መሆኑን ገልጸው፡፡
ሙስናና ብልሹ አሰራር የሀገር ሀብት የሚያባክን የሕዝብን እምነት የሚያሳጣ የፍትህ ስርዓትን በማዳከም የሀገር ሕልውና አደጋ ላይ የሚጥል በመሆኑ ለጸረ ሙስና ትግል ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ አሳስበዋል።
በክልሉ ሙስና እና ብልሹ አሠራሮችን ለመግታት ኮሚሽኑ ሙስናን የሚጠየፍና ለሀገር ተቆርቋሪ ዜጋን ለመቅረጽ ከትምህርት እና ሐይማኖት ተቋማት ጋር በትኩረት መሥራት መጀመሩን ያብራሩት ኮሚሽነር አቶ አለማየሁ፤ የስብዕና ግንባታ ሥራ ተጠናክሮ እንዲቀጥል አሳስበዋል።
የዘንድሮ የዓለም አቀፍ የጸረ ሙስና ቀን ከሕዳር 1 ጀምሮ በትምህርት ቤቶች፣ በወረዳዎች፣ በዞኖች እና በክልል ተቋማት በተለያዩ ሁነቶች እንደሚከበር ያብራሩት ኮሚሽነሩ፤ በዚህም ስለ ሙስና አስከፊነት ሰፊ የግንዛቤ ማስጨበጫ ተሰጥቶበት ለትግሉ መጠናከር የጋራ መግባባት ይፈጠራል ብለዋል።
በሙስናና ብልሹ አሠራር ምክንያት የሚባክነውን ሐብት ለታለመለት ዓላማ ለማዋል መንግሥት በትኩረት እየሠራ መሆኑን አቶ አለማየሁ ገልጸው፤ አጥፊዎች ላይ ተገቢውን ርምጃ ለመውሰድ ከፍትህ ተቋማት ጋር የመግባቢያ ሰነድ በመፈራረም በቀጣይ የተጠናከረ ክትትል እንደሚደረግ አብራርተዋል።
በክልሉ በተያዘው ወር የአመራሩ የሐብት ምዝገባ የሚከናወንበት መሆኑን የገለጹት ኮሚሽነሩ፤ አመራሩ ተግባሩን በትኩረት እንዲመራው አሳስበዋል።
የዘንድሮው የጸረ ሙስና ቀን “ስውር ትስስሮችን በማጋለጥ ሙስና ወለድ ወንጀሎችን እናጋልጥ” በሚል መሪ ቃል በአገራችን ለ23ኛ እንዲሁም በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ለ4ኛ ጊዜ እንደሚከበር ታውቋል።
ዘጋቢ: ወ/ገብርኤል ላቀው – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን

More Stories
በወላይታ ዞን ካዎ ኮይሻ ወረዳ በጤና ተቋም ለወላድ እናቶች እየተሰጠ ያለው አገልግሎት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ተጠቃሚ እናቶች ተናገሩ
ሊቨርፑል ወደ አሸናፊነት ሲመለስ ቼልሲ ሽንፈት አስተናገደ
የትምህርት ስርዓቱን የሚጎዱ የመልካም አስተዳደር ችግሮች በመስበር ትውልድን የመቅረፅ ስራ በአግባቡ መፈፀም ይገባል – የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ገዛኸኝ ጋሞ