የመስቀል እና የደመራ በዓልን ስናከብር ኢየሱስ ክርስቶሰ በመስቀል ላይ የከፈለውን የደም ዋጋ በማሰብ ሊሆን ይገባል ሲሉ የወላይታ ዞን የኃይማኖት አባቶች አሳሰቡ

የኃይማኖት አባቶቹ በጋራ በሰጡት አስተያየት፥ መስቀል ክርስቶስ ስለሰው ልጆች ኃጢያት ብሎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለም ሕዝቦች በሙሉ ፍቅሩን የገለጸበት ታላቅ ኃይማኖታዊ በዓል ስለመሆኑ ተናገረዋል።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን መስቀልና የደመራ በዓልን በተለያዩ ሃይማኖታዊ ሥርዓቶች እንደምታከብርና ይህ በዓል ለቤተክርስቲያኗ ክብሯ እንደሆነ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የወላይታ ሀገረ ስብከት ሥራ አስኪያጅ የሆኑት መልዓከሠላም ቄሲስ ቦክቻ ኢንጋ ተናግረዋል፡፡

በዓሉን ስናከብር ኢየሱስ ክርስቶሰ ስለእኛ በመስቀል ላይ የከፈለውን የደም ዋጋ በማሰብ የተቀደሰና የመልካምነት ተግባራትን በማከናወን እንዲሁም የተቸገሩትን በመርዳት ማክበር አለብን ብለዋል።

በመጨረሻም ሀገራችን ኢትዮጵያ ሠላም የምትሆንበትና የጦርነት ድምጽ የማይሰማበት መልካም ዓመት ይሆን ዘንድ መልካም ምኞታቸውን የገለፁት መልዓከሠላም ቄሲስ ቦክቻ፤ “መልካም በዓል ይሁንልን” ብለዋል።

በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን የወላይታ ሀገረ-ስብከት የብፁዕ ጳጳሱ እንደራሴ የሆኑት አባ ዓለማዬሁ ወልደየሱስ በበኩላቸው፤ መስቀል በኢትዮጵያ ካቶሊካዊት ቤተክርስቲያን ትልቅ ስፍራ የሚሰጥበት ኃይማኖታዊ በዓል ሲሆን ኢየሱስ ክርስቶስ በመሰቀል ላይ ራሱን መስዋዕት አድርጎ በመስጠት ከአባቱ ጋር ያስታረቀበት የፍቅር መገለጫ በዓል መሆኑን አብራርተዋል።

መስቀል ቤዛችን ነው፣ መስቀል ኃይላችን ነው፣ መስቀል አስታራቂያችን ነው ያሉት አባ ዓለማዬሁ፤ ከጥላቻና መገፋፋት በመውጣት ክርስቶስ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ያስተማረንን ፍጹም ፍቅር በሕይወታችን ተግባራዊ በማድረግ ለሌሎች ቸርነትና መልካም ነገርን ሁሉ ማድረግ አለብን ብለዋል።

የተቸገሩ ወገኖችን መርዳትና የመተጋገዝ ባህል በበዓላት ወቅት ብቻ ሳይሆን የሁልጊዜ ልማዳችን ሊሆን እንደሚገባም ተናግረዋል።

የኃይማኖት አባቶቹ በጋራ በሰጡት አስተያየት፥ መስቀል ክርስቶስ ስለሰው ልጆች ኃጢያት ብሎ በመስቀል ላይ ተሰቅሎ ለዓለም ህዝቦች በሙሉ ፍቅሩን የገለጸበት ታላቅ ኃይማኖታዊ በዓል ነው በማለት፣ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች “እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ!” ሲሉ የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ ፍቃዱ ማቴዎስ – ከዋካ ጣቢያችን