በበዓል ምክንያት በምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ አቅማቸውን እየፈተነ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ገበያውን እንዲያረጋጋ ያነጋገርናቸው የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ

በበዓል ምክንያት በምርቶች ላይ የታየው የዋጋ ጭማሪ አቅማቸውን እየፈተነ በመሆኑ የሚመለከተው አካል ገበያውን እንዲያረጋጋ ያነጋገርናቸው የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች ጠየቁ

የአርባምንጭ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ በበኩሉ፣ በበዓላት ወቅት ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር የተለያዩ የመፍትሄ ርምጃዎችን እየወሰደ መሆኑን አስታውቋል።

ካነጋገርናቸው የአርባምንጭ ከተማ ነዋሪዎች መካከል ወ/ሮ መክሊት ራሻው እና ወ/ሮ ጽዮን ኦሎሎ በሰጡት አስተያየት፤ በበዓላት ወቅት የሚታየው የዋጋ ጭማሪ በየጊዜው እየጨመረ መምጣቱንና አቅማቸውን እየፈተነው መሆኑን ገልጸዋል።

በተለይም በዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ላይ ለሚገኙ የማኅበረሰብ ክፍሎች አሉታዊ ጫና እያሳደረ መሆኑንም ተናግረዋል።

ኅብረተሰቡ በበዓላት ወቅት ከሚጠቀማቸው የቁም እንስሳት በተጨማሪ፣ በሌሎች ምርቶች ላይም ከዓምናው የተለየ የዋጋ ጭማሪ መታየቱን አቶ ብዙነህ ጎበሽ እና ሙግሶ ግቶ ገልጸዋል።

በመሆኑም የሚመለከተው አካል የቁጥጥርና የክትትል ሥራዎችን በማጠናከር የምርት አቅርቦትን በመጨመር ገበያውን እንዲያረጋጋ አስተያየት ሰጪዎቹ ጠይቀዋል።

የአርባምንጭ ከተማ ንግድና ኢንዱስትሪ ልማት መምሪያ ኃላፊ ወ/ሪት መስከረም ዛፉ በበኩላቸው፤ የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ በምግብ ነክና በቤት ውስጥ ፍጆታ ዕቃዎች ላይ የዋጋ ጭማሪ እንዳይኖር እና ገበያውን ለማረጋጋት የተለያዩ የመፍትሔ እርምጃዎች እየተወሰዱ መሆኑን አስታውቀዋል።

በተለይም የኑሮ ውድነት ጫናን ለመቀነስ አምራቾች፣ የህብረት ሥራ ማኅበራት እና ጅምላ አቅራቢዎች ምርቶቻቸውን ያለ ደላላ ጣልቃ ገብነት በቀጥታ ለሸማቹ በተቋቋሙ የሰንበት ገበያዎችና በልኳንዳ ቤቶች በቅናሽ ዋጋ እንዲያቀርቡ መደረጉን ኃላፊዋ አንስተዋል።

ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ፣ ምርት የሚደብቁ እና በሕገወጥ መንገድ ገበያውን ለማናጋት የሚሞክሩ ነጋዴዎች ላይም ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ ይገኛል ብለዋል።

ኅብረተሰቡ በየአካባቢው የተዘጋጁ የቅናሽ ገበያዎችን በመጠቀም እና ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ የሚያደርጉ ነጋዴዎችን ሲያጋጥሙ ለአስቸኳይ ጥቆማ በተዘጋጁ ስልክ ቁጥሮች በመጠቀም የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ አለሚቱ አረጋ – ከአርባ ምንጭ ጣቢያችን