የዘንድሮው የመስቀል በዓል የሰንጋ ገበያ ከአምና ጋር ሲነፃፀር የዋጋ ቅናሽ መኖሩን በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ ሸማቾች ተናገሩ

የዘንድሮው የመስቀል በዓል የሰንጋ ገበያ ከአምና ጋር ሲነፃፀር የዋጋ ቅናሽ መኖሩን በጉራጌ ዞን የወልቂጤ ከተማ ሸማቾች ተናገሩ

የዘንድሮው መስቀል በዓል የሰንጋ ገበያ ከአምናው ጋር ሲነፃፀር የዋጋ ቅናሽ መኖሩን በጉራጌ ዞን ወልቂጤ ከተማ አግኝተን ያነጋገርናቸው ሸማቾች ተናግረዋል።

ሸማች ላይ ሕገ-ወጥ የንግድ አሠራሮች እንዳይከሰቱና በአላስፈላጊ ደላሎች እንዳይታለሉ ከባለድሻ አላላት ጋር እየሰራ መሆኑን የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ገልጿል።

በጉራጌ ማህበረሰብ ዘንድ በድምቀት ከሚከበሩ አበይት በዓላት መካከል የመስቀል በዓል አንዱ ነው።

በወልቂጤ ከተማ በጉብሬ ክፍለ ከተማ የሰንጋዎች መሸጫ በረት ሲሸጡና ሲገዙ አግኝተን ያነጋገርናቸው ገበያተኞች በሰጡን አስተያየት፤ ሰንጋ ከ57 ሺህ ብር ጀምሮ እስከ 120 ሺህ ብር እየተሸጠ መሆኑን ጠቅሰው ከዚህ በታች በሆነ ዋጋ እየተገበያዩ መሆኑንም ተናግረዋል።

ጥሩ የበዓል ድባብ እንዳለ የገለፁት ሻጭና ገዢዎቹ፤ የገበያው ሁኔታ ከአምናው ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር ሰፊ የዋጋ ቅናሽ የታየበትና የተረጋጋ የበዓል ገበያ ስለመሆኑም አስረድተዋል።

የወልቂጤ ከተማ አስተዳደር ንግድና ገበያ ልማት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ንቅበሸዋ ከተለያዩ የከተማዋ አጎራባች አካባቢዎች ጭምር ሰንጋ በስፋት መግባቱንና የሰንጋ አቅርቦት እጥረት እንዳልተፈጠረ ተናግረዋል።

ከዋጋ አንፃርም ከአምናው ወቅት ጋር ሲነፃፀር እጅግ ቅናሽ በሆነ መልኩ ግብይት መካሄድ መቻሉንም አክለው ገልፀዋል፡፡

በሸማቹ ላይ ሕገ-ወጥ የንግድ አሠራሮች እንዳይከሰቱና በአላስፈላጊ ደላሎች እንዳይታለል ጽ/ቤቱ ከባለድሻ አላላት ጋር በጥምረት እየሰራ እንደሆነም ነው ሀላፊው የተናገሩት።

በዓሉ ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የሰላም እና የደስታ እንዲሆን አቶ ግርማ መልካም ምኞታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ ሚፍታ ጀማል – ከወልቂጤ ጣቢያችን