ሰው ተኮር የበጎነት እሴቶች በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል – ዶ/ር መሀመድ ኑሪዬ

ሰው ተኮር የበጎነት እሴቶች በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል – ዶ/ር መሀመድ ኑሪዬ

ሰው ተኮር የበጎነት እሴቶች በሁሉም አካባቢዎች ተደራሽ እንዲሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ እንደሚገኝ በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑሪዬ ገለፁ።

ኃላፊው ይህን ያሉት ‹‹በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ›› በሚል መሪ ቃል በተቋማቸው የገንዘብ ድጋፍ በጉራጌ ዞን አገና ከተማ ለአንዲት አቅመ ደካማ እናት የተገነባው የመኖሪያ ቤት ተጠናቆ የቁልፍ ርክክብ በተደረገበት ወቅት ነው።

በስነ ስርአቱ ላይ የተገኙት በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የመሠረተ ልማት አስተባባሪና የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ ዶ/ር መሀመድ ኑሪዬ፤ ሰው ተኮር የበጎነት እሴቶች በሁሉም አካባቢ ተደራሽ እንዲሆኑ መንግስት ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል ብለዋል።

የበጎነት ተግባር ለፈፃሚው ከሚያስገኘው የህሊና እርካታ በተጨማሪ በፈጣሪ ዘንድም የሚያፀድቅ መልካም ስራ በመሆኑ የመረዳዳት እሴቱ በተጠናከረ ሁኔታ ሊቀጥል እንደሚገባ ዶ/ር መሀመድ ተናግረዋል።

በአገና ከተማ ለአቅመ ደካማ እናት የተገነባው የመኖሪያ ቤት ስራ ጥራቱን ጠብቆ በታቀደለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ አስተዋጽኦ ላበረከቱ ሁሉም አካላት ምስጋና ያቀረቡት ኃላፊው፤ ለመሠል በጎ ስራዎች የሚያደርጉትን ድጋፍ እንደሚያስቀጥሉ ጠቁመዋል።

የጉራጌ ዞን ብልፅግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ናስር ሀሰን በበኩላቸው፤ በበጀት አመቱ ‹‹በጎነት ለኢትዮጵያ ከፍታ›› በሚል መሪ ቃል በዞኑ ህብረተሰቡንና ግብረ ሰናይ ድርጅቶችን በማሳተፍ በ16 የተለያዩ ዘርፎች የበጎ ተግባራት ስራዎች ሲከናወኑ መቆየታቸውን አስታውቀዋል።

ከመርሃ ግብሮቹ መካከል የመኖሪያ ቤት ግንባታ አንዱ መሆኑን ያወሱት አቶ ናስር፤ በተያዘው አመት በዞኑ 428 ቤቶችን ገንብቶ ለአቅመ ደካማ ወገኖች ማስረከብ ተችሏል ብለዋል።

ከዚህም በተጨማሪ ለመከላከያ ሰራዊት አባላትና ቤተሰቦቻቸው የቤት ግንባታን ጨምሮ ሌሎች አስፈላጊ ድጋፎችን ማድረግ መቻሉን አቶ ናስር አስረድተዋል።

የአገና ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ ሀብቴ ዘርጋ በበጎ ተግባር መርሃግብሮች የሰዎችን የመኖር ተስፋ የሚያለመልሙ በርካታ መልካም ተግባራት መከናወናቸውን ጠቁመው፤ በከተማው ለወ/ሮ ዝምወት አሶሬ የተደረገው የቤት ግንባታም የዚሁ ማሳያ ነው ብለዋል።

በዕለቱ ድጋፍ የተደረገላቸው ወ/ሮ ዝምወት አሶሬም በተደረገላቸው የመኖሪያ ቤት ግንባታና የቤት ቁሳቁስ ድጋፍ ከፍተኛ ደስታ እንደተሰማቸው በመግለፅ፤ የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ላደረገላቸው ድጋፍ ምስጋና አቅርበዋል።

ዘጋቢ፡ አስቻለው ተስፋ – ከወልቂጤ ጣቢያችን