በዓልን ምክንያት በማድረግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ እየተሰራ መሆኑ ተገለፀ
የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ ያልተገባ የዋጋ ጭማሪ እንዳይደረግ በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የከምባታ ዞን ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ አስታወቀ።
በበዓሉ ወቅት ምክንያታዊ ያልሆነ የዋጋ ጭማሪ እንዳይከሰት ሁሉም የበኩሉን እንዲወጣ መምሪያው ጥሪ አቅርቧል።
የዞኑ ንግድና ገበያ ልማት መምሪያ ኃላፊ አቶ ታረቀኝ ተስፋዬ፤ ያለ በቂ ምክንያት የሚደረግ የዋጋ ጭማሪ ከአሰራር ውጭ በአቋራጭ ለመበልጸግ የሚደረግ እንቅስቃሴ በመሆኑ የህግ ተጠያቂነት እንደሚያስከትል ገልፀው መሰል ድርጊቶችን አስቀድሞ ለመከላከል በቅንጅት እየተሰራ ነው ብለዋል።
በበዓሉ ምክንያት የምርት አቅርቦት ችግር እንዳይከሰት እየተሠራ መቆየቱን የተናገሩት ኃላፊው፤ በበዓላት ወቅት የተለያዩ ለጤና ጠንቅ ሊሆኑ የሚችሉ ባዕድ ነገሮችን ከምርቶች ጋር ደባልቆ መሸጥ፣ ትክክለኛ ያልሆነ ሚዛን በመጠቀም ማጭበርበርን ለመከላከል ትኩረት መሰጠቱን ጠቁመዋል፡፡
መምሪያ ኃላፊው አክለውም ሀሰተኛ የብር ኖት፣ በበዓሉ ወቅት የትራንስፖርት አገልግሎትን ለማስተጓጎል ነዳጅን ምክንያት በማድረግ የሚደረግ የዋጋ ጭማሪን ጨምሮ መሰል የወንጀል ድርጊቶችን ለማስቀረት ክትትል እየተደረገ ነው ብለዋል፡፡
የመጠቀሚያ ጊዜ ያለፈባቸውን የፋብሪካ ምርቶችን የመቆጣጠር ተግባርም በቅንጅት እየተሰራ መሆኑን አስረድተዋል።
ከዚህ ቀደም በህገ ወጥ መንገድ ነዳጅ ጭኖ ሲንቀሳቀስ የተገኘን ተሽከርካሪ ከፀጥታ አካላት ጋር በመናበብ በህግ ቁጥጥር ስር በማዋል እንዲወረስ መደረጉን አስታውሰው፤ ህብረተሰቡ መሰል የወንጀል ድርጊቶችን ሲያስተውል ለፀጥታ አካላት ጥቆማ በመስጠት እንዲተባበር የጥሪ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ዘጋቢ፡ አለማየሁ ማተቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
የጎፋና ኦይዳ ህዝቦች የባህል፣ የታሪክና የቋንቋ ሲምፖዚየም በሳውላ ከተማ እየተካሄደ ነው
ጥራት ያለው ቡና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ
የግብርና ቴክኖሎጂን በማስፋት አርሶ አደሩ ለገበያ የሚተርፍ ምርት እያመረተ መሆኑ ተገለጸ