የግብርና ቴክኖሎጂን በማስፋት አርሶ አደሩ ለገበያ የሚተርፍ ምርት እያመረተ መሆኑ ተገለጸ
የግብርና ቴክኖሎጂን በማስፋት ወረዳው ቀድሞ ከሚታወቅባቸው ምርቶች በተጨማሪ በውስን መሬት ሰፊ ምርት በሚገኝባቸው አዳዲስ ኢኒሼቲቮች አርሶ አደሩ ለገበያ የሚተርፍ ምርት እያመረተ መሆኑን የጉመር ወረዳ አስተዳደር አስታውቋል።
በወረዳው ቡርዳና ደንበር ቀበሌ የሚገኙ አርሶ አደሮች በግብርና ባለሙያ ምክረ ሀሳብ መሠረት በመስራታቸው ተጠቃሚ መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡
የጉመር ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ደገሙ አለሙ እንደገለፁት በ2018 ክረምት ወቅት በግብርናው ዘርፍ አርሶ አደሩን ተጠቃሚ ለማድረግ የተከናወኑ ተግባራት ውጤታማ ሆነዋል።
ወረዳው ቀድሞ ከሚታወቅባቸው አዝእርት እና ስራ ስር ምርቶች በተጨማሪ በግብርና ቴክኖሎጂ በመታገዝ አዳዲስ ምርቶች ማምረት በመቻሉ የአርሶ አደሮችና ሸማቾች ኑሮ እየተረጋጋ ይገኛል ብለዋል።
በዘርፉም የጥራጥሬ፣ የፍራፍሬ እና የስራ ስር ምርቶች 10 ሺህ 250 ሔክታር ገደማ መሬት በዘር ተሸፍኖ በጥሩ ቁመና ይገኛል ብለዋል።
ይህንንም ተግባር በአመራሮች፣ በባለሙያዎች እና በአርሶ አደሮች ቅንጅት ማሳካት መቻሉን ምክትል አስተዳዳሪው ጠቁመው፤ በዘር የተሸፈነውን መሬት ምርታማነት ከፍ በማድረግ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማሳደግ ተገቢውን የድጋፍና ክትትል ተግባራት በማከናወን የግብርና ቴክኖሎጂዎችን እንዲጠቀሙ ተደርጓል ብለዋል።
ወቅቱ የዩሪያ ቶፕድሬሲንግ ማዳበሪያ ጥቅም ላይ የሚውልበት ጊዜ በመሆኑ በልዩ ትኩረት ምርትና ምርታማነትን የማሳደግ ስራ ማከናወን እንደሚያሻም አስረድተዋል።
ከዚህ ጎን ለጎን አርሶ አደሩን ወጪ ቆጣቢና ለጤና ተስማሚ ምርት ለማምረት እያገዘ ያለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ የመጠቀም ልማድ ገቢ ማግኛ መሆኑን ጠቁመው፤ ተግባሩንም ለማስፋት የቨርሚ ኮምፖስት ማምረቻ መገንባቱን ገልጸዋል።
አቶ ደገሙ አያይዘውም አርሶ አደሮች ተሞክሮ የሚወስዱባቸው በወረዳው ካሉ 18 የአርሶ አደር ማሠልጠኛ ተቋማት መካከል አስሩን ሞዴል ማድረግ መቻሉን አንስተዋል።
በውስን መሬት ተጠቅመው ውጤታማ የሚሆኑባቸውን የጓሮ አትክልትና ስራ ስር ምርታማነት እያሰፉ በመቶ ካሬ ሜትር መሬት ላይ ከራሳቸው አልፈው ለገበያ የሚያመርቱ አርሶ አደሮች ተፈጥረዋል ብለዋል።
በወረዳው ቡርዳና ደንበር ቀበሌ የግብርና ባለሙያ የሆነው ወጣት በረከት መሠለ እንደገለፀው፤ በቀበሌው በስራ ስር የአትክልት ዘርፍ አርሶ አደሮች በማሰልጠኛ ተቋማት በተሠጣቸው ትምህርት መሠረት እየሠሩ በመሆናቸው ለውጥ እየመጣ ይገኛል።
በቀበሌው በመኸር እርሻ 665 ሔክታር ማሳ መሸፈን መቻሉን አንስቶ፤ በየመንደሩ ሰባ አርሶ አደሮች አስር መደብ የጓሮ አትክልት የማምረት ኢኒሼቲቭ ለውጥ እያመጣና ውጤታማ እየሆነ እንደሚገኝ ገልጿል።
በቀበሌው የውሃ አማራጭ ባይኖርም የደጋፊ መስኖ ተግባር የጓሮ አትክልትን በስፋት የማምረት ስራ እንዲሰራ አድርጓል ብሏል።
በወረዳው ቡርዳና ደንበር የተለያዩ መንደሮች አግኝተን ካነጋገርናቸው አርሶ አደሮች መካከል ወ/ሮ ጠጅነሽ ስፍር፣ ተቋመች ክንፈ እና ረሒማ አብራር እንደገለፁት፤ የግብርና ባለሙያዎች ባስተማሯቸው መሠረት የጥራጥሬ፣ የስራ ስርና የሌሎች አትክልቶች ምርት አምርተው ከራሳቸው አልፎ ለገበያ እያቀረቡ እንዲሁም የተቸገሩትን እየረዱ ይገኛሉ።
ተግባራቸውን በሚያከናውኑበት ወቅትም ግብዓት በአግባቡ በመጠቀም ከጎጂ እንስሳት ጠብቀው ምርታቸውን ማስፋት መቻላቸው ተጠቃሚ እንዲሆኑ ማድረጉንም ገልፀዋል።
ዘጋቢ፡ አማረ መንገሻ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
የጎፋና ኦይዳ ህዝቦች የባህል፣ የታሪክና የቋንቋ ሲምፖዚየም በሳውላ ከተማ እየተካሄደ ነው
ጥራት ያለው ቡና የአርሶ አደሮችን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ሚናው የጎላ መሆኑን በጌዴኦ ዞን የይርጋጨፌ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት አስታወቀ
መሳላ የሕዝቦችን ትስስር፣ አንድነትና መከባበርን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል ነው – የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች