መሳላ የሕዝቦችን ትስስር፣ አንድነትና መከባበርን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል ነው – የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች

የከምባታ ብሔር ዘመን መለወጫ የሆነው መሳላ በዓል የሕዝቦችን ትስስር፣ አንድነትና መከባበርን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል ነው ሲሉ በበዓሉ የታደሙ የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች ተናገሩ።

ይህ አኩሪ ባህልና ዕሴት ሊጠናከር እንደሚገባም ተወካዮቹ ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ ወ/ሮ ፋጤ ስርሞሎ፣ የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ምክትል ርዕሰ መስተዳደር የማህበራዊ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ትምህርት ቢሮ ኃላፊ አቶ አንተነህ ፈቃዱ፣ የክልሉ የብሔረሰቦች ምክር ቤት ዋና አፈ ጉባኤ አቶ አቡቶ አኒቶ እና የተለያዩ የፌደራል እንዲሁም የክልል ከፍተኛ አመራሮች በተገኙበት የመሳላ በዓል ተከብሯል።

በበዓሉ ከተለያዩ ብሔሮች የተሳተፉ ተወካዮች በከምባታ ብሔር ዘመን መለወጫ መሳላ በዓል ላይ በመሳተፋቸው ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረው፤ ከደስታ ባለፈ የሕዝቦችን የእርስ በእርስ መቀራረብና መተሳሰብን ያጠናከረ ታላቅ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።

መሳላ በርካታ እሴቶች ያሉት ታሪካዊ በዓል መሆኑን ያብራሩት ተወካዮቹ፤ በዓሉ ለከምባታ ብቻ ሳይሆን ለሀገር የሚጠቅሙ በርካታ ባህሎችን የተጎናጸፈ ነው ብለዋል።

የመሳላ በዓል የሕዝቦችን ትስስር፣ አንድነትና መከባበር የሚያጎለብት ታላቅ የፍቅር በዓል ነው በማለትም የበዓሉን ፋይዳ አስረድተዋል።

ይህንን ታላቅ ቱባ ባህል በማጠናከር እና ለትውልድ በማሸጋገር ሕዝቦች እርስ በእርስ እንዲቀራረቡ የሁሉንም ድርሻ የሚፈልግ መሆኑን አብራርተዋል።

ዘጋቢ: መልካሙ ታፈሰ – ከሆሳዕና ጣቢያችን