የሀድያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል ከብሔሩ ዘመን መለወጫነት ባሻገር የሚያበረክተው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ ነው – የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ
ሀዋሳ፡ መስከረም 12/2019 ዓ.ም (ደሬቴድ) የሀድያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል ከብሔሩ ዘመን መለወጫነት ባሻገር የሚያበረክተው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ መሆኑን የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ አስታወቁ፡፡
በዓሉን በዩኔስኮ ለማስመዝገብ ያለውን ስራ ሁሉም ባለድርሻ እንዲደግፍም ዋና አስተዳዳሪው ጠይቀዋል።
የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል በበዓሉ ማክበሪያ ቦታ በሀዲይ ነፈራ በድምቀት ተከበሯል።
የሀድያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ ለበዓሉ ታዳሚዎች የእንኳን ደህና መጣቸሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት እንደተናገሩት፤ የሀድያ ብሔር የራሱ የሆነ የዘመን መለወጫ ቀመር ካላንደር ካላቸው ብሔር ብሔረሰቦች መካከል አንዱ ነው።
የያሆዴ በዓል ከጥንት ጀምሮ መስከረም በገባ ሁለተኛ ሳምንት በብሔሩ ዘንድ በታላቅ ድምቀት የሚከበር ሲሆን የህዝብ ለህዝብ ትስስርን የሚያጎላ ታላቅ በዓል አንደሆነም አብራርተዋል።
የያሆዴ በዓል ከብሔሩ ዘመን መለወጫነት ባሻገር የሚሰጠው ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ ከፍተኛ ነው ያሉት ዋና አስተዳዳሪው አቶ ማቴዎስ፤ በበዓሉ የተጣሉ የሚታረቁበት፣ ያለው ለሌለው የሚያካፍልበት፣ የአንድነት፣ የፍቅርና የመተሳሰብ በዓል ሲሆን በያሆዴ በዓል እንኳን ሰው የቤት እንስሳትም ሩቅ ሳይሄዱ በአካባቢ እንክብካቤ የሚያገኙበት ድንቅ እሴት የያዘ በዓል መሆኑንም አክለዋል።
የዘንድሮውን የሀዲያ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል ታላቁ የብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች በዓል በክልሉ በተከበረበት፣ ሰባተኛውን ጠቅላላ ምርጫ በስኬት በተጠናቀቀበት፣ በምክክር የፀናች ሀገርን ለመመሥረት ታሪካዊው ሀገራዊ ምክክር በተካሄደበት ዓመት ማግስት ላይ መከበሩ ከሌሎች ጊዜያት ለየት ያደርገዋል ብለዋል ዋና አስተዳዳሪው።
የያሆዴ በዓል ለቱሪዝም ዘርፉ ዕድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያለው በመሆኑ የበዓሉን እሴት በዩኔስኮ ለማስመዝገብ እየተሰሩ ያሉ ሰራዎችን ሁሉም ባለድርሻ እንዲደግፍም ዋናአስተዳዳሪው ጠይቀዋል።
የሀዲያ ዞን ባህል ቱሪዝም መምሪያ ኃላፊ አቶ መስፍን ቦጋለ በበኩላቸው፤ የያሆዴ በዓል የክረምት ጭቃ፣ ጭጋግና ደመና አልፎ የመስከረም ብርሃን ፈንጥቆ አደይ አበባ በሚፈካበት ወቅት የሚከበር የብሄሩ ታላቅ በዓል መሆኑን ገልጸዋል።
በዓሉ የአንድነትና የፈቅርና የመተሳሰብ በዓል ሰለመሆኑም አሳውቀዋል።
በዓሉ በያሆዴ ባህላዊ ጭፈራን ጨምሮ በተለያዩ የብሔሩ ባህላዊ ምግቦች አና በሌሎችም ባህላዊ ክዋኔዎች ታጅቦ በሀዲይ ነፈራ በታላቅ ድምቀት ተከብሯል።
በዛሬው ዕለት በሀድይ ነፈራ በተከበረው የሀድያ ብሔር ዘመን መለወጫ በዓል የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር)፣ በብልጽግና ፓርቲ የክልሉ ብልጽግና ፖርቲ ጸህፈት ቤት ኃላፊ ዲላሞ ኦቶሬ (ዶ/ር) ጨምሮ የፌደራል፣ የክልል፣ የዞን፣ የከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፣ የባህል ሽማግሌዎች፣ ከተለያዩ አካባቢዎች የተጋበዙ እንግዶች፣ የብሔሩ ተወላጆችና ሌሎችም ታዳሚዎች ተገኝተዋል።
ዘጋቢ: ኤርጡሜ ዳንኤል – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
መሳላ የሕዝቦችን ትስስር፣ አንድነትና መከባበርን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል ነው – የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የ”ያሆዴ” በዓልን ስናከብር ስለ ሀገራችን ልማትና ስለ ህዝባችን አብሮነት የበለጠ የምንተጋበት ወቅት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል
የጠምባሮ ብሔረሰብ የባህል፣ የታሪክና ቀንቋ ሲምፖዚየም በሙድላ ከተማ እየተካሄደ ነው