ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት ‘ዮ ማስቃላ’ በኅብር ቀለማት አሸብርቆ በልዩ ድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት ‘ዮ ማስቃላ’ በኅብር ቀለማት አሸብርቆ በልዩ ድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ እና ሌሎች ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች በተገኙበት “ዮ ማስቃላ” የጋሞ ሕዝብ የአዲስ ዓመት ማብሰሪያ፤ የዘመን መለወጫ በዓል በኅብራዊነት አሸብርቆ፤ በህዝቦች አብሮነትና አንድነት አጊጦ፤ እጅግ ባመረ መልኩ በሰላምና በፍቅር ሰገነቷ አርባምንጭ በድምቀት በመከበር ላይ ይገኛል፡፡

“ዮ ማስቃላ” ለጋሞዎች የመሻገርና የብሩህ ተስፋ ምልክት ነወ፡፡

የአሻጋሪ እሴቶችና ሥርዓቶች ባለቤት የሆነው ጥበበኛው የጋሞ ህዝብ፤ በራሱ የጊዜ ቀመር የአዲስ ዓመት መባትን በማብሰር በልዩ ድምቀት የሚያከብረው በዓሉ፤ ከአሮጌው ወደ አዲሱ ዓመት በብሩህ ተስፋ መሻገሪያ፤ ለመጪው ዘመንም የመታደስና ሰርቶ የመለወጥ የተስፋ ስንቅ፣ የብርሃን ምልክትና ካስማ ተደርጎ የሚወሰድ ነው፡፡

ክብረ-በዓሉ የሰላምና የእርቅ እሴቶች ጎልተው የሚታዩበት ሲሆን፤ በጋሞዎች ዘንድ አዲሱን ዓመት ቂም፣ ቁርሾ እና ሐዘን ይዞ መሻገር ነውር በመሆኑ የተጣሉና የተቃቃሩ ቢኖሩ ዕርቅ አውርድው፤ ፀብን በይቅርታ በመሻገር በ “ዮ ማስቃላ” ሰላምና ፍቅር ይነግሳል፤ ያዘኑም በአዲሱ ዘመን ብሩህ ተስፋ በመጽናናት ደስታ ይሰፍናል፡፡

የ “ዮ ማስቃላ” የሰላም እሴት ከህዝቡ ድንቅ የዱቡሻ የእርቅና የአስተዳደር ሥርዓት ጋር ተዳምሮ ለሀገር የሰላም እሴት ግንባታ ፋይዳው ከፍተኛ ነው፡፡

የኅብረ-ብሔራዊው ክልላችን ነፀብራቅ፤ ሌላኛው የኅብራዊነት ጌጥ የሆነው የጋሞ ዞን፤ ብዝኃነት የጥንካሬ መሠረት፤ የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ማዕዘን መሆኑን ማሳያ ሲሆን፤ በተለይ በወርሃ መስከረም መባቻ በዞኑ ህዝቦች በየራሳቸው የጊዜ ቀመር በተቀራራቢ ወቅት የሚከበሩት የዘመን መለወጫ በዓላት ለዚህ ጉልህ ማሳያ ናቸው፡፡

በዞኑ በዘመናት አብሮነት የተዛመዱ፤ የተጋመዱ እና ባህል እሴቶቻቸውን ተወራርሰው የተሠናሠሉት የጋሞ፤ የዛይሴ እና የጊዲቾ ህዝቦች፤ የዘመን መለወጫ በዓሎቻቸውን ዘመናት የተሻገረ አብሮነትና ትስስራቸውን በሚያንፀባርቁ ተቀራራቢ ይዘት ባላቸው የእርቅ፤ የሰላም፤ የአንድነትና የወንድማማችነት እሴቶች በጋራ ያከብራሉ፡፡

በዛሬው ዕለት በመከበር ላይ የሚገኘው “ዮ ማስቃላ”ም የተለያዩ ኅብር ህዝቦችን የሚያገናኝ የአብሮነት ዓውድ ሲሆን፤ የዞኑ ህዝቦች በኅብር ቀለሞቻቸው ደምቀው ከሌሎች ወንድም ህዝቦች ጋር በአብሮነትና በአንድነት በታላቅ ድምቀት የሚያከብሩት የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ምሰሦ ነው፡፡

ክብረ-በዓሉ የሰላም፤ የፍቅር፤ የአንድነት፤ የመደጋገፍና የመተሳሰብ እሴቶችን ባቀፉ ቱባ ባህላዊ ሥርዓቶች ታጅቦ የሚከበር በመሆኑ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳውም የላቀ ነው፡፡

በክብረ-በዓሉ ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደን ጨምሮ ሌሎች የፌዴራልና የክልል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፥ የዞንና የከተማ አስተዳደር አመራሮች፥ የሀገር ሽማግሌዎች፤ የኃይማኖት አባቶች፤ የአርባ ምንጭ ከተማና የአካባቢው ነዋሪዎች፤ ከተለያየ ጫፍ የመጡ የወንድም ህዝቦች ሉኡካን እና ሌሎች ተጋባዥ እንግዶች ተገኝተዋል።

በድጋሚ መልካም አዲስ ዓመት!

ዮ…ዮ…. ማስቃላ ዮ…ዮ…ዮ!!!