የመስቀል በዓል ለማክበር ወደ ቤተሰባቸው የሚጓዙ መንገደኞች ያለምንም ችግር የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ገለጸ

የመስቀል በዓል ለማክበር ወደ ቤተሰባቸው የሚጓዙ መንገደኞች ያለምንም ችግር የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረጉን የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ጽህፈት ቤት ገለጸ

የበአል ተጓዦችን ህብረ ብሄራዊነት በሚያጠናክር መልኩ ለማስተናገድ ዝግጅት ስለመደረጉም ተመላክቷል።

የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ቃሲም ግርማ እንዳሉት፤ ቀደም ባሉ ጊዜያት ከተከበሩ በዓላት ልምድ በመውሰድ እና የነበሩ ችግሮችን አርሞ ውጤታማ ስራ ለመስራት ዝግጅት ተደርጓል።

በዋናነት በርካታ የመስቀል በዓል የሚያከብሩ ዜጎች ከተማዋን አቋርጠው ወደ ትውልድ ቀዬአቸው ስለሚጓዙ መንገደኞች ያለምንም ችግር የትራንስፖርት አገልግሎት እንዲያገኙ ለማስቻል አስፈላጊው ቅድመ ዝግጅት መደረጉን ኃላፊው ገልጸዋል።

በዚህም በመስቀል በዓል የትራንስፖርት ፍሰቱ ስለሚጨምር በመናኸሪያ በመርሃ ግብር የታገዙና መደበኛ የትራንስፖርት አገልገሎት ከሚሰጡ 250 ተሸከርካሪዎች በተጨማሪ 115 መለስተኛና አነስተኛ የህዝብ ተሽከርካሪዎች ስለመዘጋጀታቸውም አመላክተዋል።

በበዓሉ ምክንያት የትራንስፖርት ፍሰቱ ስለሚጨምር ይህን ሊያደናቅፍና ሊያስተጓጉል የሚችል ነገር እንዳይኖር መንገዱን የማጽዳት ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

በተለይም የትራፊክ አደጋ እንዳይከሰት እና ትርፍ የማስከፈልና የመጫን ተግባር እንዳይከናወን በየደረጃው ካሉ ባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት ተግባሩን መቆጣጠር በሚቻል መልኩ ዝግጅት እንደተደረገም አቶ ቃሲም አስረድተዋል።

የበዓል ተጓዦች ወደ ከተማዋ ሲደርሱ ህብረ ብሄራዊነታቸውን በሚያጠናክር መልኩ ለማስተናገድ ዝግጅት መደረጉን ጠቁመው፤ ይህን ለሚያሳልጡ የትራፊክና የመንገድ ደህንነት ባለሙያዎች እንዲሁም ለሌሎችም አጋዥ ወጣቶች ስልጠና እንዲወስዱ በማድረግ ስምሪት መሰጠቱንም አመላክተዋል።

በመጨረሻም ኃላፊው ለመላው የክርስትና አምነት ተከታዮች መልካም የመስቀል በዓል እንዲሆንላቸው የመልካም ምኞት መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።

ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን