ለፍርድ ቤቱ ከቀረቡ 720 መዝገቦች ወስጥ 717ቱ ውሳኔ ማግኘታቸውን የቀቤና ልዩ ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታወቀ
በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ለፍርድ ቤቱ ከቀረቡ 720 የወንጀልና የፍትሐብሔር መዝገቦች ወስጥ 717ቱ ውሳኔ ማግኘታቸውን በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት አስታውቋል።
ፍርድ ቤቱ በ2018 በጀት አመት የስራ አፈፃፀምና በ2019 እቅድ ዙሪያ ከሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ጋራ ውይይት አካሂዷል።
የቀቤና ልዩ ወረዳ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ፕሬዚዳንት አቶ ሙከረም ኑረዲን በዚህ ወቅት እንደተናገሩት፤ በበጀት ዓመቱ ለከፍተኛ እና ለመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ቤት የሚቀርቡ መዝገቦች የቆይታ ጊዜ በማሳጠር ለዜጎች ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት በተደረገው ጥረት የተሻለ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል።
ለፍርድ ቤት የሚቀርቡ መዝገቦችን በ2 ወር ጊዜ ውስጥ ውሳኔ እንዲያገኙና የአገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽነትን በማሳደግ የማህበረሰቡን ወጪና እንግልት ለመቀነስ በትኩረት መሰራቱ ለተገኘው ውጤት አስተዋፅኦ ማድረጉን ፕሬዝዳንቱ አመላክተዋል።
አያይዘውም በተቋቋሙ ተዘዋዋሪ ችሎቶች የቀረቡ 22 መዝገቦች ውሳኔ ማግኘት መቻላቸውን ገልፀዋል።
ከዳኝነት፣ ከፍትሐብሔርና ከሌሎች የፍርድ ቤቱ የህግ አገልግሎቶች ከ9 ሚሊየን 654 ሺህ ብር በላይ ለመንግስት ገቢ ማድረግ መቻሉን የገለፁት አቶ ሙከረም፤ ፍርድ ቤት ቀርበው መከራከር ለማይችሉ የአቅም ውስንነት ላለባቸው 46 ዜጎች ነፃ የህግ፣ የጥብቅናና የምክር አገልግሎት መስጠት መቻሉንም አስረድተዋል።
በበጀት አመቱ ለሁለቱም ፍርድ ቤቶች ቀርበው ከታዮ የወንጀልና የፍትሐብሔር መዝገቦች መካከል የአስገድዶ መድፈር፣ ህገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ ሙስና፣ ፍቺና ሌሎች ጉዳዮች በብዛት መቅረባቸውን ጠቅሰዋል፡፡
ለማህበረሰቡ ፈጣንና ቀልጣፍ አገልግሎት ለመስጠት በሚደረገው ጥረት የባለድርሻ አካላት ቅንጅት ወሳኝ መሆኑን ፕሬዝዳንቱ ጠቁመው፤ ጠንካራ ጎኖችን በማስቀጠል ክፍተቶችን ለመሙላት መሥራት ከሁሉም እንደሚጠበቅ ገልፀዋል፡፡
የመድረኩ ተሳታፊ ከሆኑ የተቋሙ ሰራተኞች መካከል አቶ ጅላሉ ሸምሱና ወ/ሮ ወይኒቱ ደመላሽ በሰጡት አስተያየት፤ በቀጣይ የተሻለ ስራ በመስራት ለማህበረሰቡ ቀልጣፋና ፍትሃዊ አገልግሎት ለመስጠት በትኩረት እንደሚሰሩ ተናግረዋል፡፡
በመድረኩ በ2018 በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ ሰራተኞች የእውቅናና የሽልማት ፕሮግራም የተከናወነ ሲሆን የ2019 በጀት ዓመት እቅድ የግብ ስምምነት ተካሂዷል።
ዘጋቢ፡ ወለላ ኤሊያስ – ከወልቂጤ ጣቢያችን

More Stories
መሳላ የሕዝቦችን ትስስር፣ አንድነትና መከባበርን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል ነው – የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች
የሀድያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል ከብሔሩ ዘመን መለወጫነት ባሻገር የሚያበረክተው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ ነው – የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የ”ያሆዴ” በዓልን ስናከብር ስለ ሀገራችን ልማትና ስለ ህዝባችን አብሮነት የበለጠ የምንተጋበት ወቅት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል