”የአተካና ምሽት” የእናቶች መሳላ በመባል የሚታወቅ የመሳላ በዓል ልዩ ድምቀት መሆኑ ተገለፀ
የከምባታ ብሔር የዘመን መለወጫ ‘መሳላ’ በዓል ዋዜማ የአተካና ምሽት የዞኑ መቀመጫ በሆነችው በዱራሜ ከተማ በተለያዩ ሁነቶች በድምቀት ተከብሯል።
“አተካና” ከተመረጠ እንሰት ተፍቆ የወጣ የቆጮ ዓይነት (ሜሬሮ) ከተሰኘው በቅቤና ወተት ተለዉሶ ለማዕድ የሚቀርብ ድንቅ ባህላዊ ምግብ ነው።
የከምባታ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ አረጋ እሸቱ በአተካና ምሽት ባደረጉት ንግግር
”አማካ መሳላ” (የእናቶች መሳላ) ተብሎ የሚታወቀው አተካና ዝግጅቱ የሚጀምረው በበጋ ወራት መሆኑን ጠቁመው፤ ይህም የሚያሳየው በመሳላ ሂደት ያለውን የመደጋገፍ ባህልን፣ ቤተሰብ ውስጥ ”ለመሳላ” ያለዉን የስራ ክፍፍል ያሳያል ብለዋል።
ይህን ወርቃማ የሆነ ባህላዊ እሴት ”የመሳላ”ልዩ ውበት አተካና ምሽት ”የአማካ መሳላ”(የእናቶች መሳላ) ሳይበረዝ ለቀጣይ ትውልድ የማስተላለፍ ኃላፊነትን መወጣት እንዳለባቸው አዝገንዝበዋል።
“ያለአተካና ‘መሳላ’ሙሉ አይሆንም”፤ ስለሆነም እናቶች የ”መሳላ” ዉበት ልዩ ድምቀት የሆነውን አተካና ለማዘጋጀት ብዙ ድካምና ጥረት የሚያሻው ነው ያሉት ደግሞ የዱራሜ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ አቶ አክሊሉ አቡቶ ናቸው።
አቶ አክሊሉ አክለውም፤ አተካና ከጊዜያት ቆይታ በኋላ ከእንሰት መረጣና ከቦታ ዝግጅት ጀምሮ ልዩ ትኩረት የሚሰጠው ባህላዊ ምግብ ከመሆኑም በላይ መሳላ በልዩ ድምቀት እንዲከበር የሚያደርግ የእናቶች መሳላ ነው ብለዋል።
“አተካና” ከእርድ ቀን አስቀድሞ ይከበራል፤ በመሳላ ምክንያት ከተለያዩ ቦታዎች የሚመጡ እንግዶች፣ የቤተሰብ አባላት በአተካና በዓሉን እንደሚጀምሩ ገልፀዋል።
“የአተካና ምሽት” የአተካና እራት የመብላት ሥነ-ሥርዓት በዞኑ ዱራሜ ከተማ፣ በ”ኡቱቢ ወጋ” አደባባይ የተካሄደ ሲሆን አተካና ሲሰራ ጊዜ ተወስዶበት እንደሚዘጋጅ ሁሉ ሲበላም ለረጅም ጊዜ ሳይበላሽና ጣዕሙ ሳይቀየር የሚቆይ ተወዳጅ ባህላዊ ምግብ መሆኑ ተመላክቷል።
የ”አተካና ምሽት” ፕሮግራሙ ከፌዴራል ጀምሮ የየመዋቅሩ ከፍተኛ የመንግስት የስራ ኃላፊዎች፣ የሀገር ሸማግሌዎች፣ ተጋባዥ እንግዶችና የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች በተገኙበት በድምቀት ተከብሯል።
ዘጋቢ: አለማየሁ ማተቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን

More Stories
መሳላ የሕዝቦችን ትስስር፣ አንድነትና መከባበርን የሚያጎለብት ታላቅ በዓል ነው – የተለያዩ ብሔር ብሔረሰብ ተወካዮች
የሀድያ ብሔር ዘመን መለወጫ “ያሆዴ” በዓል ከብሔሩ ዘመን መለወጫነት ባሻገር የሚያበረክተው ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ፋይዳ የጎላ ነው – የሀዲያ ዞን ዋና አስተዳዳሪ አቶ ማቴዎስ አኒዮ
የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ርዕሰ መስተዳድር እንዳሻው ጣሰው (ዶ/ር) የ”ያሆዴ” በዓልን ስናከብር ስለ ሀገራችን ልማትና ስለ ህዝባችን አብሮነት የበለጠ የምንተጋበት ወቅት ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል