ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ስጋቶችን መቀነስ ላይ ያተኮረ የሲቪል ሰርቫንት ውይይት በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ ተካሄደ

ሰው ሰራሽና የተፈጥሮ አደጋ ስጋቶችን መቀነስ ላይ ያተኮረ የሲቪል ሰርቫንት ውይይት በጌዴኦ ዞን ይርጋጨፌ ከተማ ተካሄደ

“የህዝብ አቅም ለሰብዓዊ ድጋፍ” በሚል መሪ ቃል የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ከሲቪል ሰርቫንቱ ጋር የምክክር ውይይት አካሂዷል።

‎በውይይቱ የተገኙት የይርጋጨፌ ከተማ አስተዳደር ምክትል ከንቲባና የሥራና ክህሎት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዮሴፍ አየለ፤ ኢትዮጵያ በራሷ አቅም ወደፊት እንዳትራመድ በየወቅቱ የሚጫንባትን ቀንበር እየሰበረች ራሷን ችላ ለመቆም እየታገለች ያለች ሀገር መሆኗን አስረድተዋል።

‎የኢኮኖሚ ጡንቻቸውን ያፈረጠሙ ሀገራት በስመ እርዳታ የኢትዮጵያን ዕድገት ወደኋላ ሲጎትቱ መቆየታቸውን ያስታወሱት ምክትል ከንቲባው፤ የእነዚህን ሀገራት የአይችሉምን እሳቤ በመቀልበስ በራስ አቅም ወደፊት ለመራመድ የተጀመረው ጥረት ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ አሳስበዋል።

‎የይርጋጨፌ ከተማ ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብርሃም ሆርዶፋ በበኩላቸው፤ ውይይቱ ከከተማው ሲቪል ሰርቫንት በተጨማሪ የሀይማኖት ተቋማት ባለድርሻዎችን ያካተተ እንደነበር አንስተው፤ ሀገሪቱ ረጂነት ይዞ ከሚመጣው የእጅ አዙር ጫና ሙሉ በሙሉ በመላቀቅ የራሷን ሀብት እንድታፈራ የሚጠበቅባቸውን ለመወጣት ያላቸውን ቁርጠኝነት ያሳዩበት እንደነበር አስረድተዋል።

‎ከኢኮኖሚ ጥገኝነት ለመላቀቅ ሁሉም የሥራ እና የቁጠባ ባህሉን ማዳበር አለበት ያሉት አቶ አብርሃም፤ የአምራች ዜጋን ጊዜ፣ አቅምና ጉልበት በማባከን ምርታማነት እንዲቀንስ ምክንያት የሚሆኑ ችግሮችን በመለየት መፍታት ለነገ የማይባል ጉዳይ መሆኑን አስታውቀዋል።

‎በውይይቱ የተሳተፉ የመንግሥት ሰራተኞች በበኩላቸው የተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋ ስጋቶችን ለመቀነስ ሁሉም በየመስኩ እየተረባረበ መሆኑን ገልጸው፤ የአቅማቸውን ድጋፍ ለማድረግም ይህ አጋጣሚ በመፈጠሩ ደስተኞች እንደሆኑና ለድጋፉ ቁርጠኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

‎ዘጋቢ: ሳሙኤል በቀለ – ከይርጋጨፌ ጣቢያችን