በቡታጅራ መናኸሪያ የአገልግሎት አሰጣጥ በሕግና መመሪያ እንዲመራ በመደረጉ ችግሮችን መፍታት መቻሉ ተገለጸ

በቡታጅራ መናኸሪያ የአገልግሎት አሰጣጥ በሕግና መመሪያ እንዲመራ በመደረጉ ችግሮችን መፍታት መቻሉ ተገለጸ

የመናኸሪያው አገልግሎት አሰጣጥ በሕግና መመሪያ እንዲመራ በመደረጉ ቀደም ሲል የነበሩ ችግሮችን መፍታት መቻሉን በምሥራቅ ጉራጌ ዞን የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ገለጸ።

ተገልጋዮችም በመናኸሪያው አገልግሎት አሰጣጥ ደስተኛ መሆናቸውን ተናግረዋል።

በምሥራቅ ጉራጌ ዞን የቡታጅራ ከተማ አስተዳደር ትራንስፖርት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ቃሲም ግርማ በደቡብ ሬዲዮና ቴሌቪዥን ድርጅት ወልቂጤ ጣቢያችን ጋር በነበራቸው ቆይታ እንዳሉት፤ መናኸሪያው ዜጎች ሁለንተናዊ ፍላጎታቸውን ለማሟላት እንቅስቃሴ ሲያደርጉ በመነሻነትም ሆነ በመድረሻነት የሚጠቀሙበት ማዕከል ነው።

ይህንኑ ተከትሎ ሁሉም ዜጋ ያለ እንግልት እንዲገለገል ለማስቻል በመናኸሪያው የሚሰጡ አገልግሎቶች በሕግና መመሪያ እንዲመሩ መደረጉን የገለጹት አቶ ቃሲም፤ በዚህም ቀደም ሲል ይስተዋሉ የነበሩ ችግሮችን መፍታት ተችሏል ብለዋል።

በዋናነት ዕቃ መጫንና ማውረድን ጨምሮ ተሳፋሪን በማዋከብ ትርፍ እንዲከፍልና እንዲጫን የሚያደርጉ ሕገ-ወጥ አደረጃጀቶችን በማስወገድ፣ መመሪያና ደንብ ተዘጋጅቶ መቆጣጠር በሚያስችል መልኩ ማስተካከል ስለመቻሉም ኃላፊው ገልጸዋል።

በተጨማሪም የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎት ከመስጠት ባለፈ፣ ሌሎች አጋዥ ቴክኖሎጂዎችን በመጠቀም በመናኸሪያው ሕገ-ወጥ ተግባር እንዳይከወን ክትትል መደረጉ አዎንታዊ ለውጥ እንዲመጣ አስችሏል ብለዋል።

በጽሕፈት ቤቱ የሥነ-ምግባር ባለሙያ አቶ ዙቤር አብደላ በበኩላቸው፤ በመናኸሪያው የአሠራር ደንብና መመሪያ መሠረት በማይንቀሳቀሱና የሥነ-ምግባር ጉድለት በታየባቸው አካላት ላይ ርምጃ መወሰዱን አብራርተዋል።

የኢ-ቲኬቲንግ አገልግሎትን በተገቢው ባልሰጡና ሌላ ፍላጎት ባሳዩ ባለሙያዎች ላይ አስተዳደራዊ ርምጃ መወሰዱን በመግለጽ፣ አሠራሩ ከጊዜ ወደ ጊዜ መሻሻል እያሳየ መምጣቱን ተናግረዋል።

በጽሕፈት ቤቱ የመናኸሪያ ስምሪት የሥራ ሂደት አስተባባሪ አቶ መሐመድ ስርሞሎ፤ መናኸሪያው ከሕገ-ወጦች ነጻ መደረጉ የተቀላጠፈ አገልግሎት ለመስጠት አስችሏል ብለዋል።

በመሆኑም አንዳንድ የሕዝብ ትራንስፖርት አሽከርካሪዎች ከቲኬት ውጪ ለማስከፈል የማስማማት ሥራ እንደሚሠሩና፣ በመረጃ በተያዙ አሽከርካሪዎች ላይ ርምጃ መወሰዱን አቶ መሐመድ አክለዋል።

አስማምቶ ከታሪፍ በላይ ማስከፈል ተቀባይነት የሌለው ተግባር በመሆኑ፣ የትራንስፖርት ተጠቃሚው ማኅበረሰብም ሕግን ለማስከበር የሚደረገውን ጥረት ሊደግፍ ይገባል ብለዋል።

በመናኸሪያው አግኝተን ያነጋገርናቸው የሕዝብ አሽከርካሪዎችም፤ ለሕግ ተገዢ ሆነው በተቀመጠው ታሪፍ መሠረት እየሠሩ መሆናቸውን ገልጸው ይሁን እንጂ የሚደረጉ የታሪፍ ማሻሻያዎች የወቅቱን የመኪና መለዋወጫ ዕቃዎች ግዢ ታሳቢ ያደረጉ መሆን እንዳለባቸው ተናግረዋል።

የትራንስፖርት ተገልጋዮች በበኩላቸው በመናኸሪያው ያለ እንግልትና ተጽዕኖ አገልግሎት እያገኙ መሆኑን በመግለጽ በአገልግሎት አሰጣጡ ደስተኛ መሆናቸውን አስረድተዋል።

ዘጋቢ፡ አማን ቢካ – ከወልቂጤ ጣቢያችን