ሶማሊያዊው ዳኛ ኦማር አርታን የዩኤፋ ሱፐር ካፕን በዋና ዳኝነት በመምራት የመጀመሪያው አፍሪካዊ ሊሆኑ ነው
በሰሜን እና መካከለኛው አሜሪካ በተካሄደው የ2026 ዓለም ዋንጫ ላይ እንዳይዳኙ በመከልከላቸው ልብ የሚሰብሩ አጋጣሚዎችን ያሳለፉት ሶማሊያዊው ዋና ዳኛ ኦማር አርታን፣ በነገው ዕለት በአውስትሪያ ሳልዝበርግ በሚካሄደው የዩኤፋ ሱፐር ካፕ ውድድር ላይ በዋና ዳኝነት በመሰየም ታሪክ ሊሰሩ ነው።
ይህ ውሳኔ አርታንን ከአውሮፓ አህጉር ውጪ የዩኤፋ ሱፐር ካፕን በመምራት የመጀሪያው ዋና ዳኛ የሚያደርጋቸው ሲሆን፣ የ2025 የአፍሪካ ኮንፌዴሬሽን የዓመቱ ኮከብ ወንድ ዳኛ ተብለው መሰየማቸው ይታወሳል።
የአውሮፓ ሻምፒዮንስ ሊግ አሸናፊው ፓሪስ ሴንት ዠርሜን ከዩሮፓ ሊግ አሸናፊው አስተንቪላ ጋር በሚያደርጉት ጨዋታ ላይ ጨዋታውን በበላይነት ይመራሉ።
አርታንን አግዘው በጨዋታው ላይ የሚሰየሙት ረዳት ዳኞች ሙሉ በሙሉ ከአፍሪካ የተወጣጡ ሲሆን፤ የጅቡቲው ሊባን አብዱልራዛቅ አህመድ እና የኬንያው እስጢፋኖስ ኤሌአዛር ኦንያንጎ ረዳት ዳኛ ሆነው ያገለግላሉ።
ይህ ታሪካዊ ውሳኔ በዩኤፋ እና በአፍሪካ እግር ኳስ ኮንፌዴሬሽን (ካፍ) መካከል በቅርቡ በተፈረመው የትብብር ስምምነት መሠረት የተደረገ መሆኑ ተገልጿል።
ኦማር አርታን በ2026 ዓለም ዋንጫ ላይ በዳኝነት እንዲያገለግሉ ፊፋ መርጧቸው የነበረ ቢሆንም፣ በቪዛ እና በጉዞ እገዳ ምክንያት አሜሪካ መግባት ሳይችሉ ቀርተዋል።
ይህ ውሳኔ በእግር ኳሱ ዓለም ከፍተኛ ቅሬታን ያስነሳ ቢሆንም፣ አርታን በጠንካራ ስፖርታዊ መንፈስ ወደፊት በመቀጠል ለአውሮፓ ትልቁ ውድድር ለመታጨት በቅተዋል።
ኦማር አርታን ከእገዳው በኋላ ወደ ሀገሩ ሲመለስ በተደረገለት የጀግና አቀባበል ወቅት በሰጠው አስተያየት”በአሜሪካ የነበረው አጋጣሚ በጣም ፈታኝ ጊዜ ነበር፤ ነገር ግን ህልማችሁን ፈጽሞ አታቋርጡ።እኔ ስኬታማ መሆን ካቻልኩ፣ ማንኛውም ሰው ማሳካት ይችላል” ይችላል ሲል ተናግሯል።
የካፍ ፕሬዝዳንት ዶክተር ፓትሪስ ሞትሴፔ የዩኤፋን ውሳኔ አስመልከተው በሰጡት አስተያየት “ይህ ለአርታን ብቻ ሳይሆን ለመላው አፍሪካውያን ዳኞች ትልቅ ኩራትና የታሪክ ምዕራፍ ነው” ሲሉ ገልጸዋል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
አርሰናል ብሩኖ ጊማራኤሽን በይፋ አስፈረመ
ሪያል ማድሪድ ያን ዲዮማንዴን በታሪካዊ የዝውውር ክፍያ አስፈረመ
ብሩኖ ጊማሬስ የሕክምና ምርመራውን በስኬት አጠናቀቀ