ሳዲዮ ማኔ በትውልድ መንደሩ ባምባሊ 20 ሚሊዮን ዶላር በመመደብ ግዙፍ የልማት ፕሮጀክት ጀመረ
ሴኔጋላዊው የፊት መስመር ተጫዋች ሳዲዮ ማኔ ከሜዳ ውጭ በሚያከናውናቸው የበጎ አድራጎት ሥራዎች አርአያነቱን ቀጥሏል።
ሳዲዮ ማኔ “ኤስ.ኤም.10 አግሮ” (SM10 AGRO) የተሰኘ ታላቅ የግብርና ልማት ፕሮጀክት እውን ለማድረግ በትውልድ መንደሩ ባምባሊ 20 ሚሊዮን ዶላር (ከ20 ቢሊዮን በላይ የኢትዮጵያ ብር ገደማ) መዋዕለ ንዋይ ማፍሰሱ ተገልጿል።
ይህ ግዙፍ የልማት እቅድ በአካባቢው ማህበረሰብ ኢኮኖሚያዊ ሕይወት ላይ ትልቅ ለውጥ ለማምጣት ትልቅ ግቦችን መሰነቁ ተነግሯል።
በፕሮጀክቱ አማካኝነት ከ2,500 በላይ ለሚሆኑ ዜጎች ዘላቂ የሥራ ዕድል ይፈጠራል።
ከ78,000 በላይ የማንጎ ዛፎችን በመትከል አካባቢውን አረንጓዴ ለማድረግ እና የአየር ንብረት ለውጥን ለመቋቋም ይሠራልም ተብሏል።
እንዲሁም የግብርና ምርትን በማሳደግ የአካባቢውን ማህበረሰብ ኑሮ ማሻሻል ከግቦቹ መካከል ተጠቃሾች ናቸው።
ሳዲዮ ማኔ ለትውልድ አገሩ ያለው ልዩ ፍቅር እና የማህበራዊ ኃላፊነት ስሜት ሲገልጽ«በሜዳ ላይ ባስቆጠርኳቸው ግቦች ብቻ ተመዝግቤ መቅረት አልፈልግም።
ስታዲየሞች፣ የኤሌክትሪክ መብራቶች እና ድሎች ከመታየታቸው በፊት ባምባሊ ነበረ» በማለት ገልጿል።
እግር ኳስ ተጫዋቹ ከዚህ ቀደምም በባምባሊ ከተማ ዘመናዊ ሆስፒታል፣ ትምህርት ቤቶች፣ የነዳጅ ማደያ እና ሌሎች መሰረተ ልማቶችን በመገንባት ለአካባቢው ማህበረሰብ አለኝታነቱን አሳይቷል።
አሁን ደግሞ “ኤስ.ኤም.10 አግሮ” የተሰኘውን ይህንን ሁለገብ የግብርና ፕሮጀክት በመቅረጽ የዜጎችን የኢኮኖሚ አቅም ለማጠናከር እና አካባቢውን በዘላቂነት ለማልማት ሌላ ታሪካዊ ምዕራፍ ከፍቷል።
ዘጋቢ፡ ሙሉቀን ባሳ

More Stories
ካይ ሃቨርትዝ ጉዳት አጋጠመው
“ማንቸስተር ሲቲ በዚህ አጨዋወት ሊጉን ማሸነፍ አይችልም”ፖል ሜርሰን
ኬሮድ የጎዳና ላይ ሩጫ ህዝብ ለህዝብ የሚያስተሳስርና አንድነታችንን ይበልጥ የምናጠናክርበት በመሆኑ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ የማእከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ወጣቶችና ስፖርት ቢሮ አስታወቀ