ማሳን በሙሉ ፓኬጅ መሸፈን የሚሰጠውን ጥቅም በመረዳት ወደ ተግባር ገብተናል – በሀዲያ ዞን ሰርቶ ማሳያ ክላስተር ተደራጅተው እያመረቱ ያሉ አርሶአደሮች
ሀዋሳ፡ ሐምሌ 20/2015 ዓ.ም (ደሬቴድ) ማሳን በሙሉ ፓኬጅ መሸፈን የሚሰጠውን ጥቅም በመረዳት ወደ ተግባር መግባታቸውን በሀዲያ ዞን ሰርቶ ማሳያ ክላስተር ተደራጅተው እያመረቱ ያሉ አርሶአደሮች ተናገሩ።
ከ1መቶ 46ሺህ ሄክታር በላይ ማሳ በመኸር እርሻ በሙሉ ፓኬጅ ለመሸፈን ግብ ጥሎ እየተንቀሳቀሰ መሆኑን የሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ ገልጿል።
የሰርቶ ማሳያ ክላስተር የዘር ማስጀመሪያ ፕሮግራም በምሻ ወረዳ ሞርስጦ ገበሬ ማሕበር ጄጄ በተባለው ክላስተር ተካሂዷል።
ፕሮገራሙን ያስጀመሩት የደቡብ ክልል ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኢንስቲትዩት ዋና ዳይሬክተር የሆኑት አቶ ገርማሜ ጋሩማ ማሳን በሙሉ ፓኬጅ መሸፈን ምርትና ምርታማነት ከ30 እስከ 40 ከመቶ እንዲጨምር አስተዋጽኦ እንደሚያደርግ አስገንዝበዋል።
ተቋሙ አርሶ አደሩ ይህንን በተግባር አይቶ እንዲተገብር ለማስቻል አርሶአደሮችን በክላስተር በማደራጀት ወደ ተግባር ከተገባ ወዲህ ስንዴ በሄክታር ከዘጠና ኩንታል በላይ መገኘቱን ጠቁመዋል።
ድርጅቱ በማሳ ዝግጅት ዙሪያ ግንዛቤ ከማስጨበጥ ባለፈም ሙሉ ግብዓቶችን እንደሚያቀርብ የተናገሩት ዳይሬክተሩ አርሶ አደሮቹ በአረምና በሰብል ላይ ሊከሰቱ የሚችሉ በሽታዎችን በመቆጣጠር ለምርታማነት የድርሻቸውን እንዲወጡ ጠይቀዋል።
በዕለቱ የተገኙት የሀዲያ ዞን ግብርና መምሪያ ምክትል ሀላፊ አቶ ተሻለ ዮሐንስ በበኩላቸው በዞኑ በመኸር እርሻ በዘር ለመሸፈን ከታቀደው ማሳ 75 ሄክታሩ በሰርቶ ማሳያ ክላስተር እንደሚሸፈን ጠቁመው፡፡
በክላስተሮቹ ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ የሚተገበሩ ስራዎች ለሌሎች አስተማሪ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ በአንድ ሄክታር ላይ በአማካይ ሃያ ሺህ ብር ለግብዓት ወጪ እንደሚደረግ አንስተዋል።
እንደ አቶ ተሻለ ገለጻ 1መቶ 46ሺህ 432 ሄክታር ማሳ በዘር ለመሸፈን የታቀደ ሲሆን ይህ ዘገባ እስከተጠናቀረበት ጊዜ ድረስ 35ሺህ ሄክታሩ በዘር ተሸፍኗል።
በዘር ወቅቱ ጾም የሚያድር ማሳ እንዳይኖር ተደርጎ ዝግጅት ቢደረግም በአለም ወቅታዊ ሁኔታና ምንዛሬ ዕጥረት ምክንያት የአፈር ማዳበሪያን በወቅቱ ማቅረብ አለመቻሉ እጅግ እንዳሳዘናቸው የገለጹት አቶ ተሻለ በአሁኑ ወቅት ከጅቡቲ ወደብ ወደ መሀል አገር እየገባ ስለሆነ አርሶ አደሩ በትዕግሥት እንዲጠባበቅ አሳስበዋል።
የምሻ ወረዳ ግብርና ጽህፈት ቤት ሀላፊ አቶ አለማየሁ ኤርደዶ በበኩላቸው ሰርቶ ማሳያ ላይ የታየውን ተሞክሮ ሌሎችም እንዲቀስሙ የማድረግ ስራ እንደሚሰራ ተናግረዋል።
በወረዳው ጄጄ ሰርቶ ማሳያ ክላስተር በማሕበር ተደራጅተው ስንዴ በሙሉ ፓኬጅ እየዘሩ አግኝተን ያናገርናቸው አርሶ አደሮች ከማሳ ዝግጅት ጀምሮ እስከ ምርት አሰባሰብ ድረስ መደረግ ያለበትን ተግባር በቅደም ተከተል እየፈጸሙ መምጣታቸውን አውስተዋል።
ክንውኑ ምርትና ምርታማነት እንዲጨምር ጉልህ አስተዋጽኦ እንዳለው በመረዳት በሙሉ አቅማቸው ወደ ስራ መግባታቸውን አስረድተዋል።
ዘጋቢ: ጌታቸው መጮሮ – ከሆሳዕና ጣቢያችን
More Stories
ከተረጅነት ለመላቀቅ እና በምግብ ራስን ለመቻል ግብርና ዋነኛ መሠረት ነው – የኮሬ ዞን አስተዳደር
ከ360 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የተገዙ የላብራቶሪ ዕቃዎች ለአገልግሎት ዝግጁ መደረጋቸው ተገለጸ
ከተለያዩ ሀገር አቀፍ የሚዲያ ተቋማት የተወጣጡ የሚዲያ ባለሙያዎች በቡርጂ ዞን በክላስተር እየለማ ያለውን ጤፍ ጎበኙ