የአካባቢ ጥበቃ አዋጅ

በአለምሸት ግርማ

ተፈጥሮን ወይም አካባቢን መንከባከብ ሰዎች ጤናማ ህይወት እንዲኖራቸው የሚያስችል ዋነኛ ተግባር ነው። ለዚህም አካባቢን ለመንከባከብ የሚያስችል አሰራር እንደየሀገራቱ ሁኔታ ይተገበራል። በሀገራችንም ይህን በተመለከተ ዘርፈ ብዙ ስራዎች የሚከናወኑ ሲሆን አረንጓዴ አሻራ በትኩረት እየተሰራበት ያለ መስክ ነው።

መርሃ ግብሩ በጥብቅ ቁጥጥርና ክትትል በመተግበሩ አሁን ላይ አጥጋቢ ውጤት እያሳየ ይገኛል። እንዲሁም ሀገሪቱን አረንጓዴ ገጽታ በማላበስ፣ የአየር ንብረት ለውጥን የሚቋቋም መልክዐ ምድር በመገንባት በኩል የተሳካ የሚባል ውጤት አስገኝቷል፡፡

በ2011 ዓ.ም የተጀመረው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በአራት አመት ውስጥ 20 ቢሊዮን ችግኝ መትከልን አላማ አድርጎ የተጀመረ ሲሆን በዚህም በመጀመሪያው አመት ብቻ 4 ነጥብ 7 ቢሊዮን ችግኝ በመትከል እቅዱን ሙሉ በሙሉ ማሳካት ተችሏል።

የመርሃ ግብሩ ዋና ግብም የተራቆተውን መሬት በደን መሸፈን ያለመ ነው። በተጨማሪም ለችግሩ አፋጣኝ እርምጃ መውሰድ ስለሚገባ እና የአየር ፀባይ ለውጥ የሚያስከትለውን አውዳሚ ተጽእኖ በመላው አለም በተለያዩ ቦታዎች ላይ በተጨባጭ የሚታይ በመሆኑ ነው።

መርሃ-ግብሩ በየዓመቱ እየተከናወነ ሲሆን በዘንድሮው መርሃ ግብርም በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል 361 ሺህ 415 ሄክታር መሬት መዘጋጀቱን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቋል።

ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ አጠቃላይ ዝግጅቱን በማስመልከት እንዳስታወቀው በአንድ ጀንበር ለሚካሄደው የችግኝ ተከላ መርሃ ግብር 9 ሺህ 500 የመትከያ አካባቢዎች ተለይተዋል።

ከኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስቴርና ከስፔስ ሳይንስ ኢንስቲትዩት ጋር በመተባበር 9 ሺህ 500 ቦታዎችን በካርታ የማካተትና ድረገፅ በማበልፀግ ወደ ስራ መገባቱንም ተገልጿል።

በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል ለተያዘው እቅድ ዜጎች ሁሉ በነቂስ ወጥተው አሻራቸውን እንዲያኖሩ ጥሪ ቀርቧል። ከሚተከሉ ችግኞች መካከል 60 በመቶው ለጥምር ደን ግብርና፣ 35 በመቶው ለተፋሰስ ልማትና ለደን ሽፋን እንዲሁም አምስት በመቶው ለከተማ ውበት የሚያገለግሉ መሆናቸውም ተገልጿል።

በተከላው የሚሳተፉ አካላት ችግኞችን ወደ መትከያ ቦታ በጥንቃቄ በማድረስ፣ ማስቀመጫ ፕላስቲኮችን በጥንቃቄ በማስወገድ ኢንዲተክሉና ለተያዘው ግብ የበኩላቸውን አስተዋፅኦ እንዲያደርጉም ጥሪ ቀርቧል። በጥንቃቄና በሙያዊ መንገድ ችግኞች እንዲተከሉ የሚያግዙ ባለሙያዎችም በሁሉም አካባቢዎች የሚሰማሩ መሆኑም ተጠቅሷል።

ሐምሌ 10 ቀን 2015 ዓ.ም በአንድ ጀንበር 500 ሚሊዮን ችግኞችን ለመትከል በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የተደረገው ጥሪ የኢትዮጵያ የአረንጓዴ ልማት ትግበራ በተግባር የሚታይበት እንደሚሆን ይጠበቃል።

ይህም በህገ መንግስቱ አንቀፅ 44 ንዑስ አንቀጽ 1 ላይ እንደተቀመጠው “ሁሉም ሰዎች ንፁህና ጤናማ በሆነ አካባቢ የመኖር መብት አላቸው” የሚለውን የሚያረጋግጥ ተግባር ነው።

ከዚህ በተጨማሪ በዚህና በሌሎች መርሃ ግብሮች የተተገበሩ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎችን አለመንከባከብ ወይም ጉዳት ማድረስ ለዘርፉ የወጣውን ህግ አለማክበር በህግ ተጠያቂ እንደሚደርግ የአካባቢ ብክለት ቁጥጥር አዋጅ ያመለክታል።

አንዳንድ ማሕበራዊና ኢኮኖሚያዊ የልማት ጥረቶች ልማቱን የሚቀለብስ ጎጂ አካባቢያዊ ተፅዕኖ ሊያስከትሉ የሚችሉ በመሆናቸው፣ በአጠቃላይ አካባቢን መጠበቅ፣ በተለይም የሰውን ጤንነትና በጎ ሁኔታ እንደዚሁም የሕያዋንን ደሕንነትና የተፈጥሮን ሥነ-ውበት ማቆየት የሁሉም ተግባርና ኃላፊነት በመሆኑም ነው፡፡ የመከላከያ ወይም የማስወገጃ እርምጃዎችን በመውሰድ በማሕበራዊና በኢኮኖሚያዊ ልማት ጥረቶች ሂደት የሚከሰተውንና የማይፈለገውን ብክለት ማስወገድ ሳይቻል መከላከል ተገቢ በመሆኑ አዋጁ ሊወጣ ችሏል።

የብክለት ቁጥጥርን በተመለከተ በወጣው አዋጅ 9/12(1995) አንቀፅ 300 መሰረት፡-

1.ማንም ሰው ተገቢን የአካባቢ ደረጃ በመተላለፍ አካባቢን ሊበከል ወይም በሌላ ሰው በኩል እንዲበከል ሊያደርግ አይፈቀድለትም።

2. ሕግ በመተላለፍ ማንኛውንም በካይ ወደ አካባቢ በሚለቅ ሰው ላይ ባለሥልጣኑ ወይም የሚመለከተው የክልል የአካባቢ መሥሪያ ቤት አስተዳደራዊ ወይም ሕጋዊ ዕርምጃ መውሰድ ይችላል።

3.ብክለትን ወይም ሌላ አካባቢያዊ ጉዳትን ሊያስከትል በሚችል የተግባር መስክ የተሰማራ ማንም ሰው፣ የቆሻሻ መመንጨትን ለማስወገድ ወይም ወደ ተፈላጊው መጠን ለመቀነስ በባለሥልጣኑ ወይም በሚመለከተው የክልል የአካባቢ መሥሪያ ቤት ትዕዛዝ መሠረት በተገቢ ቴክኖሎጂና ሲቻልም ቆሻሻን መልሶ በጥቅም ላይ ለማዋል በሚያስችሉ ዘዴዎች መጠቀም አለበት።

4.ብክለትን ያደረሰ ማንኛውም ሰው፣ ባለሥልጣኑ ወይም የሚመለከተው የክልል የአካባቢ መሥሪያ ቤት በሚወሰነው ሁኔታና የጊዜ ገደብ መሠረት አካባቢውን ማፅዳት፣ ወይም ለማፅጃ የወጣውን ወጪ መሸፈን አለበት።

5. በጤና ወይም በአካባቢ ላይ አደጋ እንዳያስከትል ከሚያሰጋ የሥራ እንቅስቃሴ ሊመጣ የሚችል ጉዳትን ለመከላከል ባለሥልጣኑ ወይም የሚመለከተው የክልል የአካባቢ መሥሪያ ቤት ድርጅትን እስከ መዝጋት ወይም ወደ ሌላ ቦታ እስከ ማዛወር የሚደርስ ማንኛውንም አስፈላጊ እርምጃ መውሰድ ይችላል።

ብክለትን በሚመለከት ስለሚፈፀም ጥፋት በአዋጁ እንደተደነገገው አንድ የተፈጥሮ ሰው የዚህን አዋጅ ወይም በሥሩ የሚወጡትን ደንቦች በመተላለፍ በካይን ወደ አካባቢ በመልቀቅ ጥፋተኛ ሆኖ ሲገኝ፣ ከአንድ ሺህ ብር በማያንስና ከአምስት ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ወይም ከአንድ ዓመት በማያንስና ከአሥር ዓመት በማይበልጥ እሥራት ወይም በሁለቱም ይቀጣል።

ጥፋቱን የፈፀመው በሕግ የሰውነት መብት የተሰጠው አካል ከሆነ ከአምስት ሺህ ብር በማያንስና ከሃያ አምስት ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ይቀጣል፤ የሥራ ኃላፊውም ከአምስት ዓመት በማያንስና ከአስር ዓመት በማይበልጥ እሥራት ወይም ከአምስት ሺህ ብር በማያንስና ከአስር ሺህ ብር በማይበልጥ የገንዘብ መቀጮ ወይም በሁለቱም ይቀጣል።