በስፖርቱ ዘርፍ እየተደረገ ያለዉ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እንደሚደረግ ተገለጸ

በስፖርቱ ዘርፍ እየተደረገ ያለዉ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፍ እንደሚደረግ ተገለጸ

በስፖርቱ ዘርፍ እየተደረገ ያለዉ እንቅስቃሴ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ድጋፉ እንደሚቀጥል በማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል የቀቤና ልዩ ወረዳ አስተዳደር ገለጸ፡፡

በልዩ ወረዳዉ የሰላም ወርልድ ቴኳንዶ ማሰልጠኛ ማዕከል ስምንተኛ አመት የምስረታ እና ሰባተኛ ዙር የምረቃ ስነ-ስርዓት በወልቂጤ ከተማ ባስመረቀበት ወቅት ነዉ።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊና የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ የህያ ሀምዛ በዚህ ወቅት እንደገለጹት ወጣቶች በስነ ምግባር ታንፀዉ እንዲያድጉ የስፖርቱ ዘርፍ እያበረከተ ያለዉ አስተዋፆ ከፍተኛ ነዉ።

በቀቤና ልዩ ወረዳ በስፖርቱ ዘርፍ እየተገኙ ያሉትን ለዉጦች ለማስቀጠል የልዩ ወረዳዉ መንግስት እያደረገ ያለዉን ድጋፍ እንደሚያጠናክር ኃላፊዉ ገልጸዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ወጣቶችና ስፖርት ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ አብድልወሃብ ኑረዲን በበኩላቸው በልዩ ወረዳዉ በሁሉም የስፖርት አይነቶች ተጨባጭ ለዉጦችን ለማስመዝገብ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

በተለይም በቴኳንዶ ስፖርት ዘርፍ ላይ እየተገኘ ያለዉን ዉጤት ለማስቀጥል ጽ/ቤቱ ድጋፍ እና ክትትል እንደሚያደርግ ነዉ የገለጹት።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ወርልድ ቴኳንዶ ፌዴሬሽን ፕሬዝዳንት ቶፊቅ ነስሩ በልዩ ወረዳዉ ከ15 በላይ የወርልድ ቴኳንዶ ማሰልጠኛ ማዕከላት ስልጠና በመስጠት ላይ እንደሚገኙ በመጠቆም ማዕከላቱ ብቁ፣ ተወዳዳሪ እና ተተኪ ስፖርተኞችን እንዲፈጥሩ ከባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመሆን እየተሰራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።

የሰላም ወርልድ ቴኳንዶ ማሰልጠኛ ማዕከል አሰልጣኝ ሙአዝ ስራጅ እንዳሉት ማዕከሉ ባለፉት 8 አመታት በርካታ ተማሪዎችን በማሰልጠን ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰዉ በዛሬዉ እለት ከ200 በላይ ተማሪዎቹን ለሰባተኛ ዙር ማስመረቁን አንስተዋል።

በልዩ ወረዳዉ በዘርፉ እየተሰጠ ያለዉ ትኩረት ተተኪ ስፖርተኞችን ለማሳደግ ያለዉ ሚና ከፍተኛ በመሆኑ ይህም ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ገልፀዋል።

በምረቃ ስነ ስረዓቱ ያነጋገርናቸዉ ተመራቂዎች በሰጡት አስተያየት ስፖርት መስራት ጤናቸዉ እንዲጠበቅ፣ አይምሮኣቸዉ ብቁ እንዲሆንና በአካል የዳበረ እንዲሆኑ ፋይዳው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል።

ዘጋቢ፡ ሪያድ ሙህዲን – ወልቂጤ ጣቢያችን