የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ማስፈፀሚያ ከ45.7 ቢሊየን ብር በላይ በጀት አፀደቀ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት ለ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ማስፈፀሚያ ከ45.7 ቢሊየን ብር በላይ በጀት አፀደቀ

የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ክልል ምክር ቤት እያካሄደ ባለዉ 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ የ2018 በጀት ዓመት ተጨማሪ በጀት ብር 5,795,504,182.25 እንዲሁም የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ማስፈፀሚያ 45,700,231,971 ብር አጽድቋል፡፡

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ ሕዝቦች ክልል በ2019 በጀት ለክልል ከመደበዉ በጀት 65 በመቶ በጀት ለካፒታል ፕሮጀክት መመደቡን የክልሉ ርዕሰ መስተዳድር ኢንጂነር ነጋሽ ዋጌሾ(ዶ/ር) ገልጸዋል።

የክልሉ ምክር ቤት በታርጫ ከተማ እያካሄደ ባለዉ 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 10ኛ መደበኛ ጉባኤ ላይ የክልሉን መንግስት የ2019 ጠቋሚ ዕቅድ ባቀረቡበት ወቅት እንደገለፁት፤ የክልሉ መንግስት ለክልል ከተመደበዉ በጀት የህዝቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ 65 በመቶዉን ለካፒታል ፕሮጀክት መመደቡን አስታዉቀዋል፡፡

የ2019 በጀት ዓመት ዕቅድ የ2018 አፈፃፀምን መነሻ ያደረገ፤ የክልሉን ልማት፣ ሰላምና መልካም አስተዳደር ለመመለስ ትኩረት መደረጉን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ የምግብ ሉዓላዊነትን ማረጋገጥ፣ የዲጂታል ኢኮኖሚ ግንባታን ማጠናከር፣ የገጠር ኮሪደርን ጨምሮ እንደሀገርም ሆነ እንደክልል የተጀመሩ ኢንሼቲቮችን አጠናክሮ ማስቀጠል የዕቅድ አካል መደረጉን አብራርተዋል፡፡

የኑሮ ዉድነትን መቅረፍ የሚያስችሉ ተግባራተን ማጠናከር፣ የማምረቻና መሸጫ እንዲሁም የብድር አቅርቦት በማመቻቸት የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት በትኩረት ይሰራል ብለዋል፡፡

የመንገድ፣ የጤና፣ የዉሃና ሌሎችም መሰረተ ልማቶች ግንባታ በቀጣይ በትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል፡፡

ለክልሉ የሚሰጠዉ የድጎማ በጀት ብዙም አለማደጉን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉን ገቢ የማመንጨት አቅም ማሳደግ ትኩረት እንደሚደረግበት ተናግረዋል፡፡

በክልሉ 4ቱም የክልል ማዕከላት የተጀመሩ የቢሮ ግንባታዎች የተወሰኑትን በበጀት ዓመቱ ለማጠናቀቅ ይሰራልም ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ባቀረቡት የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ላይ የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄዎችን አንስተዉ በርዕሰ መስተዳድሩ ምላሽ ተሰጥቶበት ዕቅዱ በምክር ቤቱ ፀድቋል፡፡

ዘጋቢ፡ ድልነሳው ታደሰ