ክልሉ ያለውን ፀጋ በአግባቡ ለይቶ በማልማት ከድህነት ጋር የኖርነው የፍቅር ጊዜ ማብቃት አለበት – አቶ ኡስማን ስሩር

ክልሉ ያለውን ፀጋ በአግባቡ ለይቶ በማልማት ከድህነት ጋር የኖርነው የፍቅር ጊዜ ማብቃት አለበት – አቶ ኡስማን ስሩር

ሀዋሳ፡ ግንቦት 22/2018 ዓ.ም (ደሬቴድ) ክልሉ ያለውን ፀጋ በአግባቡ ለይቶ በማልማት ከድህነት ጋር የኖርነው የፍቅር ጊዜ ማብቃት አለበት ሲሉ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር ተናገሩ።

አቶ ኡስማን ስሩር ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ ያላቸው የጃክፍሩት እና የአናናስ የፍራፍሬ ችግኞች ተከላ መርሐ ግብር በክልሉ ቀቤና ልዩ ወረዳ በፈረጀቴ ቀበሌ አስጀምረዋል።

በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የገጠር ክላስተር አስተባባሪ እና የማዕከላዊ ኢትዮጵያ ክልል ግብርና ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡስማን ስሩር በዚሁ ወቅት እንዳሉት፤ በየጊዜው ክልሉ ያለውን ፀጋ መነሻ ያደረጉ አዳዲስ ኢኒሼቲቮች ይተገበራሉ።

የ30- 40 – 30 የፍራፍሬ ልማት ኢኒሼቲቭም በአግባቡ ለምቶ ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መጀመሩን ገልጸዋል።

ስለሆነም ክልሉ ያሉትን ፀጋዎች በአግባቡ ለይቶ በማልማት ህብረተሰቡ ከድህነት ጋር የኖረውን የፍቅር ጊዜ ማብቃት አለበት ሲሉ አሳስበዋል።

ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና ስነ-ምህዳራዊ ፋይዳ ያለው ጃክፍሩት የድህነት ስር ማድረቂያ ነውም ብለዋል።

በአምስ አመት ጌዜ ውስጥ ለፍሬ የሚደርስ ሲሆን ከመቶ ዓመት በላይ ማፍራት ይችላል። በመሆኑም ሁሉም ሰው ጥቅሙን አውቆት በየአካባቢው ሊተክለው እንደሚገባ ገልጸዋል።

እንደ ጃክፍሩት ሁሉ ምርታማነቱና ጣፋጭነቱ የተረጋገጠው የአናናስ ችግኝን ያስተዋወቁት አቶ ኡስማን፤ በትንሽ መሬት ላይ ብዙ ምርት ማምጣት በሚችሉ ምርቶች ላይ ማተኮር ብልህነት ነው ብለዋል።

የቀቤና ልዩ ወረዳ ዋና አስተዳዳሪ አቶ መሀመድአሚን በደዊ በበኩላቸው፤ በአቅራቢያችን ኖሮ ጥቅሙን ግን በአግባቡ ተረድተን ያልተጠቀምንበት ጃክፍሩትን እንደ ልዩ ወረዳችን ለማስተዋወቅ በመምጣቱ እድለኞች ነን ብለዋል።

በልዩ ወረዳው ወደሚገኙ ሁሉም አርሶ አደሮች፣ የሃይማኖትና የትምህርት ተቋማት ተደራሽ ለማድረግ በቁርጠኝነት እንደሚሰሩም ተናግረዋል።

የፍራፍሬ ችግኞቹ በጓሮው የተተከለለት የፈረጀቴ ቀበሌ ነዋሪው ወጣቱ አርሶ አደር አብዱልዋሂድ ሸረፈዲን፤ ይህን እድል በማግኘቱ መደሰቱን ተናግሮ በአግባቡ ተንከባክቦ ለፍሬ እንደሚያበቃውም ቃል ገብቷል።

ዘጋቢ፡ ተረፈ ሀብቴ – ከወልቂጤ ጣቢያችን