ማሳቸውን ለመኸር እርሻ ደጋግማው በማረስ አለስልሰው በወቅቱ ለመዝራት መዘጋጀታቸውን በከምባታ ዞን ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ያነጋገርናቸው አንዳንድ አርሶአደሮች ተናገሩ

ማሳቸውን ለመኸር እርሻ ደጋግማው በማረስ አለስልሰው በወቅቱ ለመዝራት መዘጋጀታቸውን በከምባታ ዞን ቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ያነጋገርናቸው አንዳንድ አርሶአደሮች ተናገሩ

ለ2018/19 ዓ ም ምርት ዘመን በመኸር እርሻ 2 ሺ 9 መቶ 12 ሄክታር ማሳ በዘር ለመሸፈን አቅዶ እየሰራ መሆኑን በከምባታ ዞን የቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ግብርና ጽ/ቤት አስታዉቋል።

ያላቸውን ማሳ በዘር ለመሸፈን የቅድመ ዝግጅት ስራዎችን አጠናቀው ወቅቱን በመጠባበቅ ላይ መሆናቸውን የቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ አርሶአደሮች አስረድተዋል።

ከተለመደው አስተራረስ ዘዴ በመላቀቅ ስንዴና ጤፍን በኩታ ገጠም በክላስተር ለመዝራት የሚያስችል የማሳ ዝግጅት ማድረጋቸውን ተናግረዋል።

መንግስት የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት እና ዋጋው የአርሶ አደሩን አቅም ባገናዘበ መልኩ እንዲሆን መስራት እንዳለበት አርሶአደሮቹ ጠይቀዋል።

“የተቀናጀ ግብርና ትጋት ለላቀ ምርታማነት” በሚል መሪ ቃል የ2018 የምርት ዘመን የመኸር ወቅት የተቀናጀ ግብርና ልማት ሥራዎችን በንቅናቄ መምራት በሚያስችል ሁኔታ ላይ አርሶ አደሮችን፣ የግብርና ባለሙያዎችንና የሚመለከታቸውን በማሳተፍ የዘርፉን ውጤታማነት ለማሳደግ እየተሰራ መሆኑን የገለፁት የቀዲዳ ጋሜላ ወረዳ ምክትል አስተዳዳሪና የግብርና ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ዳዊት ማቴዎስ ናቸው።

በ2018/19 ምርት ዘመን 2 ሺ 912.5 ሄክታር ማሳ በዘር ለመሸፈን የሚያስችል የማሳ ዝግጅትና የግብዓት አቅርቦት ስራዎች እየተከናወኑ መሆናቸውን አስረድተዋል።

አርሶ አደሩ ዘመናዊ አስተራረስ ዘዴዎችን እንዲከተል ለማስቻል እየተሰራ መሆኑን የጠቆሙት አቶ ዳዊት፤ በክላስተር በኩታ ገጠም መዝራት ከአረም ቁጥጥር ባሻገር ምርትና ምርተማነትን ለማሳደግ ምቹ ሁኔተን ይፈጥራል ነው ያሉት።

29 የስንዴ እና 26 የጤፍ ክላስተር ተለይቶ መዘጋጀቱን የጠቆሙት ኃላፊው፤ የአፈር ማዳበሪያ አቅርቦት ላይ ከወትሮ የተለየ የዋጋ ለውጥ እንዳይኖር መሠራቱን አመላክተዋል።

ዘጋቢ: አለማየሁ ማተቦ – ከሆሳዕና ጣቢያችን